bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Leviticus 20
Leviticus 20
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2
“ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘ከልጆቹ አንዱን ለሞሎክ የሚሰጥ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር መጻተኛ ይገደል፤ እርሱንም የአገሩ ሕዝብ በድንጋይ ይውገረው።
3
ልጁን ለሞሎክ በመስጠት መቅደሴን አርክሷልና፣ ቅዱሱን ስሜንም አቃልሏልና፣ በዚያ ሰው ላይ ጠላት እሆንበታለሁ፤ ከወገኖቹም ለይቼ አጠፋዋለሁ።
4
የአገሩ ሕዝብ፣ ሰውየው ልጁን ለሞሎክ ሲሰጥ አይተው ቸል ቢሉ፣ ባይገድሉትም፣
5
በዚያ ሰውና በቤተ ሰቡ ላይ ጠላት እሆናለሁ፤ እርሱንና ከሞሎክ ጋር በማመንዘር እርሱን የተከተሉትን ሁሉ ከሕዝባቸው መካከል ለይቼ አጠፋቸዋለሁ።
6
“ ‘ወደ ሙታን ጠሪዎችና ጠንቋዮች ዘወር በማለት፣ በሚከተላቸውና ከእነርሱም ጋር በሚያመነዝር ሰው ላይ ጠላት እሆንበታለሁ፤ ከወገኖቹም ለይቼ አጠፋዋለሁ።
7
“ ‘ራሳችሁን ቀድሱ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝና።
8
ሥርዐቴን ጠብቁ፤ አድርጉትም፤ የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
9
“ ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚረግም ማንኛውም ሰው ይገደል፤ አባቱን ወይም እናቱን ረግሟልና ደሙ በራሱ ላይ ነው።
10
“ ‘አንድ ሰው ከባልንጀራው ሚስት ጋር ቢያመነዝር፣ አመንዝራውና አመንዝራዪቱ ይገደሉ።
11
“ ‘አንድ ሰው ከአባቱ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም አባቱን አዋርዷል፤ ሰውየውና ሴትየዋ ይገደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።
12
“ ‘አንድ ሰው ከልጁ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ሁለቱም ይገደሉ፤ ነውር አድርገዋልና ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።
13
“ ‘አንድ ወንድ ከሴት ጋር ግብረ ሥጋ እንደሚፈጽም ሁሉ ከወንድ ጋር ቢፈጽም፣ ሁለቱም አስጸያፊ ድርጊት ፈጽመዋልና ይገደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።
14
“ ‘አንድ ሰው አንዲትን ሴትና እናቷን ቢያገባ፣ አድራጎቱ ጸያፍ ነው፤ በመካከላችሁ እንዲህ ዐይነት ርኩሰት እንዳይገኝ ሰውየውና ሴቶቹ በእሳት ይቃጠሉ።
15
“ ‘ማንኛውም ሰው ከእንስሳ ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ይገደል፤ እንስሳዪቱንም ግደሏት።
16
“ ‘አንዲት ሴት ወደ እንስሳ ቀርባ ግብረ ሥጋ ብትፈጽም፣ ሴቲቱንና እንስሳውን ግደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።
17
“ ‘አንድ ሰው የአባቱ ወይም የእናቱ ልጅ የሆነችውን እኅቱን አግብቶ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ አድራጎቱ አሳፋሪ ነው፤ በሕዝባቸው ፊት ከሕዝባቸው ተለይተው ይጥፉ። ሰውየው እኅቱን አዋርዷልና ይጠየቅበታል።
18
“ ‘ማንኛውም ሰው በወር አበባዋ ጊዜ ከሴት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ የፈሳሿን ምንጭ ገልጧልና፣ እርሷም የፈሳሿን ምንጭ ገልጣለችና ሁለቱም ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ።
19
“ ‘ከእናትህም ሆነ ከአባትህ እኅት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ የሥጋ ዝምድናን ማቃለል ስለሆነ ሁለታችሁም ትጠየቁበታላችሁ።
20
“ ‘ማንኛውም ሰው ከአጎቱ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ አጎቱን አዋርዷልና ሁለቱም ይጠየቁበታል፤ ያለ ልጅም ይሞታሉ።
21
“ ‘ማንኛውም ሰው የወንድሙን ሚስት ቢያገባ አድራጎቱ ርኩሰት ነው፤ ወንድሙን አዋርዷልና፣ ያለ ልጅም ይቀራሉ።
22
“ ‘እንድትኖሩባት እናንተን የማስገባባት ምድር እንዳትተፋችሁ ሥርዐቴንና ሕጌን ጠብቁ፤ አድርጉም።
23
ከፊታችሁ የማሳድዳቸውን አሕዛብ ልማድ አትከተሉ፤ እነዚህን ሁሉ በማድረጋቸው ተጸየፍኋቸው።
24
እናንተ ግን፣ “ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ ማርና ወተት የምታፈስሰውን አገር ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ” አልኋችሁ፤ ከአሕዛብ የለየኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
25
“ ‘ንጹሕ በሆኑትና ንጹሕ ባልሆኑት እንስሳት እንዲሁም ንጹሕ በሆኑትና ንጹሕ ባልሆኑት ወፎች መካከል ልዩነት አድርጉ። ርኩስ ነው ብዬ በለየሁት በማንኛውም እንስሳ ወይም ወፍ ወይም በምድር ላይ በሚንቀሳቀስ በማንኛውም ነገር ራሳችሁን አታርክሱ።
26
እናንተ ለእኔ ቅዱሳን ትሆኑልኛላችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ቅዱስ ነኝና፤ የእኔ ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ መካከል ለይቻችኋለሁ።
27
“ ‘ከመካከላችሁ ሙታን ጠሪ ወይም መናፍስት ጠሪ የሆነ ማንኛውም ወንድ ወይም ሴት ይገደል፤ በድንጋይም ይወገሩ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።’ ”
← Chapter 19
Chapter 21 →