bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Leviticus 19
Leviticus 19
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2
“ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ጉባኤ እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።
3
“ ‘ከእናንተ እያንዳንዱ እናቱንና አባቱን ያክብር፤ ሰንበታቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
4
“ ‘ወደ ጣዖታት ዘወር አትበሉ፤ ወይም ከቀለጠ ብረት ለራሳችሁ አማልክት አትሥሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
5
“ ‘የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁ አድርጋችሁ አቅርቡ።
6
መሥዋዕቱም ባቀረባችሁት ዕለት ወይም በማግስቱ ይበላ፤ እስከ ሦስተኛው ቀን የተረፈ ማንኛውም ነገር ይቃጠል።
7
በሦስተኛውም ቀን ቢበላ ርኩስ ነው፤ ተቀባይነትም የለውም።
8
ከመሥዋዕቱ የሚበላ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰውን ነገር አርክሷልና ይጠየቅበታል፤ ያም ሰው ከወገኑ ተለይቶ ይጥፋ።
9
“ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ በዕርሻችሁ ዳርና ዳር ያለውን አትጨዱ፤ ቃርሚያውንም አትልቀሙ።
10
የወይንህን ዕርሻ አትቃርም፤ የወደቀውንም አትልቀም፤ ለድኾችና ለመጻተኞች ተውላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
11
“ ‘አትስረቁ፤ “ ‘አትዋሹ፤ “ ‘ከእናንተ አንዱ ሌላውን አያታልል።
12
“ ‘በስሜ በሐሰት አትማሉ፤ በዚህም የአምላካችሁን (ኤሎሂም) ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
13
“ ‘ባልንጀራህን አታጭበርብር፤ አትቀማውም፤ “ ‘የሙያተኛውን ደመወዝ ሳትከፍል አታሳድር።
14
“ ‘ደንቈሮውን አትርገም፤ በዐይነ ስውሩም ፊት ዕንቅፋት አታኑር፤ ነገር ግን አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
15
“ ‘ፍርድ አታዛቡ፤ ለድኻው አታድላለት፤ ለትልቁም ሰው ልዩ አክብሮት አትስጥ፤ ለብርቱው አታዳላ፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በትክክል ፍረድ።
16
“ ‘በሕዝብህ መካከል ሐሜት አትንዛ፤ “ ‘የባልንጀራህን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ነገር አታድርግ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
17
“ ‘ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ የበደሉ ተካፋይ እንዳትሆን ባልንጀራህን በግልጽ ገሥጸው።
18
“ ‘ወገንህን አትበቀል፤ ወይም ምቀኛ አትሁንበት፤ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
19
“ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ፤ “ ‘የተለያዩ እንስሳትን አታዳቅል፤ “ ‘በዕርሻህ ላይ ሁለት ዐይነት ዘር አትዝራ፤ “ ‘ከሁለት ዐይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ።
20
“ ‘አንድ ሰው ለሌላ ከታጨች ሴት ባሪያ ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ሴቲቱም ያልተዋጀች ወይም ነጻ ያልወጣች ብትሆን ይቀጣል፤ ነገር ግን ሴቲቱ ነጻ ስላልወጣች አይገደሉም።
21
ሰውየውም ለበደል መሥዋዕት የሚሆን አንድ አውራ በግ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያምጣ።
22
ካህኑም በበደል መሥዋዕቱ አውራ በግ፣ ሰውየው ስለ ሠራው ኀጢአት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል።
23
“ ‘ወደ ምድሪቱ ገብታችሁ ማንኛውንም ዐይነት ፍሬ የሚሰጥ ዛፍ በምትተክሉበት ጊዜ፣ ፍሬው ለመብላት የተከለከለ መሆኑን ዕወቁ፤ ለሦስት ዓመትም የተከለከለ በመሆኑ አይበላ።
24
በአራተኛውም ዓመት ፍሬው ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ የምስጋና መሥዋዕት ይሆናል።
25
በአምስተኛው ዓመት ግን ፍሬውን ትበላላችሁ፤ በዚህም ሁኔታ ፍሬው ይበዛላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
26
“ ‘ደም ያለበትን ማንኛውንም ሥጋ አትብሉ፤ “ ‘ጥንቈላ ወይም አስማት አትሥሩ።
27
“ ‘የራስ ጠጕራችሁን ዙሪያ አትከርከሙ፤ ጢማችሁንም አሳጥራችሁ አትቍረጡ።
28
“ ‘ለሞተ ሰው ሰውነታችሁን አትንጩ፤ በሰውነታችሁም ላይ ንቅሳት አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
29
“ ‘ምድሪቱ ወደ ግልሙትና አዘንብላ በርኩሰት እንዳትሞላ፣ ሴት ልጅህ ጋለሞታ ትሆን ዘንድ አታዋርዳት።
30
“ ‘ሰንበታቴን ጠብቁ፤ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
31
“ ‘እንዳትረክሱባቸው ወደ ሙታን ጠሪዎች ዘወር አትበሉ፤ መናፍስት ጠሪዎችንም አትፈልጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
32
“ ‘ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት፤ ሽማግሌውን አክብር፤ አምላክህንም (ኤሎሂም) ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
33
“ ‘መጻተኛ በምድራችሁ ላይ አብሯችሁ በሚኖርበት ጊዜ አትበድሉት፤
34
አብሯችሁ የሚኖረው መጻተኛ እንደ ገዛ ወገናችሁ ይታይ፤ እንደ ራሳችሁም ውደዱት፤ እናንተም በግብፅ መጻተኞች ነበራችሁና፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
35
“ ‘በመስፈሪያ ወይም በሚዛን አታጭበርብሩ።
36
እውነተኛ መለኪያ፣ እውነተኛ መመዘኛ፣ እውነተኛ የኢፍ መስፈሪያ፣ እውነተኛ የኢን መስፈሪያም ይኑራችሁ። ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
37
“ ‘ሥርዐቴንና ሕጌን ሁሉ ጠብቁ፤ ተከተሏቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።’ ”
← Chapter 18
Chapter 20 →