bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Joshua 17
Joshua 17
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ምናሴ የዮሴፍ የበኵር ልጅ እንደ መሆኑ መጠን፣ ለነገዱ የተመደበለት ድርሻ ይህ ነበር፤ የምናሴ የበኵር ልጅ ማኪር፣ የገለዓዳውያን አባት ብርቱ ጦረኛ ስለ ነበር ገለዓድና ባሳን ድርሻው ሆኑ።
2
ስለዚህ ይህ ርስት ለተቀሩት የምናሴ ዘሮች ማለትም ለአቢዔዝር፣ ለኬሌግ፣ ለአሥሪኤል፣ ለሴኬም፣ ለኦፌር፣ ለሸሚዳ ጐሣዎች የተሰጠ ነው፤ እነዚህ በየጐሣዎቻቸው የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ሌሎች ወንዶች ዝርያዎች ናቸው።
3
ሰለጰዓድ የአፌር ልጅ፣ የገለዓድ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣ የምናሴ ልጅ ነው። እርሱም ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም። የሴቶች ልጆቹም ስም ማህለህ፣ ኑዓ፣ ዔግላ፣ ሚልካ፣ ቲርጻ ይባላል።
4
እነርሱም ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር፣ ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱና ወደ መሪዎቹ ቀርበው፣ “ከወንድሞቻችን ጋር ርስት እንድንካፈል እግዚአብሔር ሙሴን አዝዞታል” አሏቸው። ስለዚህ ኢያሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ ከአባታቸው ወንድሞች ጋር ርስት ሰጣቸው።
5
ምናሴም ከገለዓድና ከባሳን ምድር ሌላ፣ ዐሥር ቦታ የሚደለደል የመሬት ክፍል በዮርዳኖስ ምሥራቅ ነበረው፤
6
የምናሴ ነገድ ሴት ልጆች ከወንዶቹ ጋር ርስት ተካፍለዋልና። የገለዓድ ምድር ግን ለቀሩት የምናሴ ዘሮች ተሰጠ።
7
የምናሴ ርስት ከአሴር አንሥቶ ከሴኬም በስተ ምሥራቅ እስካለችው እስከ ሚክምታት ይደርሳል፤ ድንበሩም ወደ ደቡብ በመዝለቅ በዓይንታጱዋ የሚኖረውን ሕዝብ ይጨምራል።
8
የታጱዋ ምድር የምናሴ ይዞታ ነበር፤ ይሁን እንጂ በድንበሩ ላይ የምትገኘው የታጱዋ ከተማ የኤፍሬም ዘሮች ይዞታ ነበረች።
9
ከዚያም በመቀጠል ድንበሩ በደቡብ በኩል ወደ ቃና ወንዝ ይደርሳል። በምናሴ ከተሞችም መካከል የኤፍሬም ከተሞች ነበሩ፤ ያም ሆኖ የምናሴ ድንበር የወንዙ ሰሜናዊ ክፍል ሲሆን፣ እስከ ባሕሩ ይዘልቃል።
10
በደቡብ በኩል ያለው ምድር የኤፍሬም ሲሆን፣ በሰሜን በኩል ያለው ደግሞ የምናሴ ነበር፤ የምናሴ ግዛት እስከ ባሕሩ የሚደርስ ሲሆን፣ ሰሜናዊ ድንበሩ አሴር፣ ምሥራቃዊ ድንበሩ ደግሞ ይሳኮር ነው።
11
እንዲሁም በይሳኮርና በአሴር ውስጥ ቤትሳን፣ ይብልዓም፣ የዶር ሕዝብ፣ ዐይን ዶር፣ ታዕናክና መጊዶ በዙሪያቸው ካሉ ሰፈሮቻቸው ጋር የምናሴ ነበሩ፤ ሦስተኛውም ናፎት ነው ።
12
ይሁን እንጂ የምናሴ ዘሮች እነዚህን ከተሞች መያዝ አልቻሉም፤ ከነዓናውያን የያዙትን ላለመልቀቅ ቍርጥ ሐሳብ አድርገው ነበርና።
13
እስራኤላውያን በበረቱ ጊዜ ግን ከነዓናውያንን የጕልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው እንጂ ከዚያ ፈጽመው አላባረሯቸውም ነበር።
14
የዮሴፍ ዘሮች ኢያሱን፣ “ቍጥራችን ብዙ ነው፤ እግዚአብሔርም አብዝቶ ባርኮናል፤ ታዲያ እንዴት ርስታችን አንድ ዕጣና አንድ ድርሻ ብቻ ሆነ?” አሉት።
15
ኢያሱም መልሶ፣ “ቍጥራችሁ ይህን ያህል በዝቶ ኰረብታማው የኤፍሬም ምድር እስከዚህ የሚጠባችሁ ከሆነ፣ ወደ ፌሪዛውያንና ወደ ራፋይም ምድር ወጥታችሁ ደኑን ለራሳችሁ መንጥሩ” አላቸው።
16
የዮሴፍም ዘሮች፣ “ኰረብታማው አገር አይበቃንም፤ ደግሞም በሜዳው ላይ ያሉት በቤትሳንና በሰፈሮቿ፣ እንዲሁም በኢይዝራኤል ሸለቆ የሚኖሩት ከነዓናውያን ሁሉ የብረት ሠረገሎች አሏቸው” አሉት።
17
ኢያሱ ግን ለዮሴፍ ዘሮች ለኤፍሬምና ለምናሴ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ቍጥራችሁ ብዙ፣ እጅግም ኀያል እንደ መሆናችሁ ድርሻችሁ አንድ ብቻ አይሆንም፤
18
ነገር ግን ደን የለበሰው ኰረብታማው አገር የእናንተ ነው፤ ሄዳችሁ መንጥሩት፣ ዳር ድንበሩ ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ከነዓናውያን የብረት ሠረገላ ቢኖራቸውና ብርቱዎች ቢሆኑም እንኳ ከዚያ ታስወጧቸዋላችሁ።”
← Chapter 16
Chapter 18 →