bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Joshua 18
Joshua 18
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
መላው የእስራኤላውያን ማኅበር በሴሎ ተሰበሰቡ፣ የመገናኛውንም ድንኳን እዚያው ተከሉ፤ ምድሪቱም ጸጥ ብላ ተገዛችላቸው።
2
ዳሩ ግን ርስት ገና ያልተሰጣቸው ሰባት የእስራኤል ነገዶች ነበሩ።
3
ስለዚህ ኢያሱ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፤ “የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ምድር ለመውረስ ቸል የምትሉት እስከ መቼ ነው?
4
አሁንም ከእያንዳንዱ ነገድ ሦስት ሦስት ሰው ምረጡ፤ እኔም ምድሪቱን ተዘዋውረው እንዲያጠኑና እያንዳንዱም ነገድ መውረስ የሚገባውን ድርሻ ዝርዝር መግለጫ ጽፈው እንዲያመጡ እልካቸዋለሁ፤ ከዚያም ወደ እኔ ይመለሳሉ።
5
ምድሪቱንም ሰባት ቦታ ይከፍሏታል፤ ይሁዳ በደቡብ፣ የዮሴፍ ዘሮች በሰሜን በኩል የተመደበላቸውን ርስት ይዘው ይኖራሉ።
6
የሰባቱን የመሬት ክፍፍል ዝርዝር መግለጫ ጽፋችሁ ወደ እኔ ታመጡና በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ እጥልላችኋለሁ።
7
ሌዋውያኑ ግን ለእግዚአብሔር የሚሰጡት የክህነት አገልግሎት ርስታቸው ስለሆነ በእናንተ መካከል ድርሻ አይኖራቸውም። ጋድ፣ ሮቤልና የምናሴ ነገድ እኩሌታም የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምሥራቅ ዮርዳኖስ የሰጣቸውን ርስት ቀደም አድርገው ወስደዋል።”
8
ሰዎቹ የምድሪቱን ሁኔታ ለማጥናትና ለመመዝገብ ጕዞ ሲጀምሩ ኢያሱ፣ “ሄዳችሁ የምድሪቱን ሁኔታ አጥኑና በዝርዝር ከጻፋችሁ በኋላ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም እዚሁ ሴሎ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ እጥልላችኋለሁ” አላቸው።
9
ስለዚህም ሰዎቹ ሄደው ምድሪቱን ተዘዋውረው አዩ፤ ከነ ከተሞቿም ሰባት ቦታ ከፍለው በጥቅልል ብራና ላይ በዝርዝር ጻፉ፤ ከዚያም በሴሎ ሰፈር ወዳለው ወደ ኢያሱ ተመለሱ።
10
ኢያሱም በሴሎ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ ጣለላቸው፤ ምድሪቱንም እንደየነገዱ ደልድሎ ለእስራኤላውያን አከፋፈላቸው።
11
ለብንያም ነገድ የሆነው የመጀመሪያው ዕጣ በየጐሣ በየጐሣው ወጣ። በዕጣ የደረሳቸውም ምድር የሚገኘው በይሁዳና በዮሴፍ ነገዶች ርስት መካከል ሲሆን እንደሚከተለው ነው፤
12
በሰሜን ያለው ድንበራቸው ከዮርዳኖስ ይነሣና የኢያሪኮን ሰሜናዊ ተረተር ዐልፎ፣ በስተ ምዕራብ ወዳለው ኰረብታማ ምድር በማምራት፣ እስከ ቤትአዌን ምድረ በዳ ይዘልቃል።
13
ከዚያ ደግሞ ወደ ደቡብ ሎዛ ማለት ወደ ቤቴል ተረተር ይሻገርና በታችኛው ቤትሖሮን በስተ ደቡብ ባለው ተራራ በኩል አድርጎ ወደ አጣሮት አዳር ይወርዳል።
14
በስተ ደቡብ ያለው ድንበር ከቤትሖሮን ትይዩ ካለው ኰረብታ ተነሥቶ፣ በምዕራብ በኩል ወደ ደቡብ በመታጠፍ፣ የይሁዳ ነገድ ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ቂርያትበኣል ማለት ወደ ቂርያትይዓሪም ያልፋል፤ ይህ እንግዲህ በምዕራብ በኩል ያለው ድንበር ነው።
15
በስተ ደቡብ ያለው ድንበር ደግሞ በምዕራብ በኩል ከቂርያትይዓሪም ጥግ ይነሣና እስከ ነፍቶ ውሃ ምንጭ ይዘልቃል፤
16
ይኸው ድንበር ከራፋይም ሸለቆ በስተ ሰሜን ባለው በሄኖም ሸለቆ ትይዩ ቍልቍል ወደ ኰረብታው ግርጌ ይወርዳል፤ ከዚያም ከኢያቡሳውያን ከተማ በደቡብ በኩል ባለው ተረተር አድርጎ ወደ ሄኖም ሸለቆ በመውረድ እስከ ዓይንሮጌል ይዘልቃል።
17
ደግሞም ወደ ሰሜን ይታጠፍና በቤትሳሚስ በኩል አድርጎ እስከ ጌሊሎት ይዘልቃል፤ ከዚያም በአዱሚም መተላለፊያ ትይዩ እስካለው እስከ ሮቤል ልጅ እስከ ቦሀን ድንጋይ ይወርዳል።
18
ወደ ቤትዓረባ ሰሜናዊ ተረተር በመቀጠል ቍልቍል ወደ ዓረባ ይወርዳል።
19
ከዚያም ሰሜናዊውን የቤትሖግላንን ተረተር ዐልፎ ይሄድና በስተ ደቡብ የዮርዳኖስ ወንዝ እስከሚገባበት እስከ ሙት የባሕር ወሽመጥ ይዘልቃል፤ ይህም ደቡባዊ ድንበሩ ነው።
20
በምሥራቅ በኩል ያለው ድንበር፣ ራሱ የዮርዳኖስ ወንዝ ነው። ይህ እንግዲህ የብንያም ነገድ ጐሣዎች በርስትነት የወረሷት ምድር ዳር ድንበሮቿ ሁሉ እነዚህ ነበሩ።
21
የብንያም ነገድ በየጐሣቸው የያዟቸው ከተሞች እነዚህ ናቸው፤ ኢያሪኮ፣ ቤትሖግላ፣ ዓመቀጺጽ፣
22
ቤትዓረባ፣ ዘማራይም፣ ቤቴል፣
23
ዓዊም፣ ፋራ፣ ኤፍራታ፣
24
ክፊርዓሞናይ፣ ዖፍኒ እንዲሁም ጋባ ናቸው፤ እነዚህም ከነ መንደሮቻቸው ዐሥራ ሁለት ከተሞች ናቸው።
25
ገባዖን፣ ራማ፣ ብኤሮት፣
26
ምጽጳ፣ ከፊራ፣ አሞቂ፣
27
ሬቄም፣ ይርጵኤል፣ ተርአላ፣
28
ጼላ፣ ኤሌፍ፣ የኢያቡሳውያን ከተማ ኢየሩሳሌም፣ ጊብዓ እንዲሁም ቂርያት ነበሩ፤ እነዚህም ከነ መንደሮቻቸው ዐሥራ አራት ከተሞች ናቸው። እንግዲህ የብንያም ነገድ በየጐሣቸው የወረሱት ይህ ነበር።
← Chapter 17
Chapter 19 →