bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
2 Chronicles 12
2 Chronicles 12
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ሮብዓም መንግሥቱን ከመሠረተና ካጸና በኋላ፣ እርሱና እስራኤል ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ።
2
እግዚአብሔርን ከመበደላቸው የተነሣም፣ ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ።
3
ከግብፅ አብረውት የመጡትን ዐሥራ ሁለት ሺሕ ሠረገላዎች፣ ስድሳ ሺሕ ፈረሰኞችና ስፍር ቍጥር የሌላቸውን የሊቢያ፣ የሱኪምና የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዞ፣
4
የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች በቍጥጥሩ ሥር በማድረግ እስከ ኢየሩሳሌም ዘለቀ።
5
ከዚህ በኋላ ነቢዩ ሸማያ ወደ ሮብዓምና ሺሻቅን ፈርተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡት ወደ እስራኤል መሪዎች መጥቶ፣ “ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ ትታችሁኛል፤ ስለዚህ እኔም በሺሻቅ እጅ ትቼአችኋለሁ’ ” አላቸው።
6
የእስራኤል መሪዎችና ንጉሡ ራሳቸውን በማዋረድ፣ “ እግዚአብሔር ጻድቅ ነው” አሉ።
7
እግዚአብሔርም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሸማያ መጣ፤ “ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ስላዋረዱ እታደጋቸዋለሁ እንጂ አላጠፋቸውም፤ ቍጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም።
8
ይሁን እንጂ እኔን በማገልገልና የሌሎችን አገሮች ነገሥታት በማገልገል መካከል ያለውን ልዩነት ያውቁ ዘንድ፣ ለእርሱ ይገዛሉ።”
9
የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ንብረትና የቤተ መንግሥቱን ንብረት ዘርፎ ወሰደ፤ ሰሎሞን ያሠራው የወርቅ ጋሻ ሳይቀር፣ እንዳለ ሁሉንም አጋዘው።
10
ንጉሥ ሮብዓምም በተወሰዱት ፈንታ የናስ ጋሻዎች ሠርቶ፤ የቤተ መንግሥቱን ቅጥር በሮች ለሚጠብቁ የዘብ አለቆች በኀላፊነት ሰጠ።
11
ንጉሡ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ፣ ዘበኞቹ ጋሻዎቹን አንግበው ያጅቡት ነበር፤ ከዚያም በኋላ ጋሻዎቹን ወደ ዘበኞች ክፍል ይመልሱ ነበር።
12
ሮብዓም ራሱን ዝቅ አድርጎ ስላዋረደ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ ከእርሱ ተመለሰ፤ ፈጽሞም አላጠፋውም። በይሁዳም ደግሞ በጥቂቱም ቢሆን መልካም ነገር ተገኝቶ ነበር።
13
ንጉሥ ሮብዓም በሚገባ ተደላድሎ በኢየሩሳሌም በንጉሥነቱ ቀጠለ፣ ሲነግሥ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ እግዚአብሔር ስሙን በዚያ ለማኖር ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጣት በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀምጦም፣ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ናዕማ የምትባል አሞናዊት ነበረች።
14
እግዚአብሔርን ይሻ ዘንድ ልቡን ስላላዘጋጀ ክፉ ነገር አደረገ።
15
ሮብዓም በዘመነ መንግሥቱ ያከናወናቸው ተግባሮች ሁሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ነቢዩ ሸማያ በጻፈው የታሪክ መዝገብና ባለ ራእዩ አዶ በዘገበው የትውልድ ሐረግ ታሪክ የሚገኝ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር።
16
ሮብዓም እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁ አብያም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።
← Chapter 11
Chapter 13 →