bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
2 Chronicles 13
2 Chronicles 13
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ አብያ በይሁዳ ነገሠ።
2
በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ዓመት ገዛ። እናቱ ሚካያ ትባላለች፤ እርሷም የገብዓ ተወላጅ የኡርኤል ልጅ ነበረች። በአብያና በኢዮርብዓምም መካከል ጦርነት ነበር።
3
አብያ አራት መቶ ሺሕ ብርቱ ተዋጊዎች ይዞ ዘመተ፤ ኢዮርብዓምም ስምንት መቶ ሺሕ ብርቱ ተዋጊዎች ይዞ በመውጣት ጠበቀው።
4
አብያ በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በጽማራይም ተራራ ላይ ቆሞ፣ እንዲህ አለ፤ “ኢዮርብዓምና እስራኤል ሁሉ አድምጡኝ!
5
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ዳዊትና ዘሮቹ በእስራኤል ላይ ለዘላለም እንዲነግሡ በጨው ኪዳን የሰጣቸው መሆኑን አታውቁምን?
6
የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ባሪያ የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ግን በጌታው ላይ ዐመፀ።
7
የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም ገና ሕፃን ሳለ፣ ምንም ማድረግ በማይችልበትና እነርሱንም ለመቋቋም ዐቅሙ በማይፈቅድለት ጊዜ የማይረቡ ጥቂት ወሮበሎች በዙሪያው ተሰበሰቡበት፣ በረቱበትም።
8
“አሁንም እናንተ በዳዊት ዘርዐ ትውልድ እጅ ያለውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ልትቋቋሙ አስባችኋል። በርግጥም በሰራዊት ረገድ እጅግ ብዙ ናችሁ፤ አማልክታችሁ ይሆኑ ዘንድ ኢዮርብዓም የሠራቸውንም የወርቅ ጥጆች ይዛችኋል።
9
ደግሞስ የአሮን ልጆች የሆኑትን የእግዚአብሔርን ካህናትና ሌዋውያንን አባርራችሁ፣ ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ እናንተም የራሳችሁን ካህናት አልሾማችሁምን? አንድ ኮርማና ሰባት አውራ በግ ይዞ ራሱን ለመቀደስ የሚመጣ ማናቸውም ሰው አማልክት ላልሆኑ ለእነዚያ ጣዖታት ካህን ይሆናል።
10
“ለእኛ ግን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱንም አልተውንም፤ እግዚአብሔርን በማገልገል ላይ ያሉት ካህናት የአሮን ልጆች ሲሆኑ፣ ረዳቶቻቸውም ሌዋውያኑ ናቸው።
11
እነርሱም በየጧቱና በየማታው የሚቃጠል መሥዋዕትና ሽታው ደስ የሚያሰኝ ዕጣን ለእግዚአብሔር ያቀርባሉ፤ የገጹን ኅብስት በሥርዐቱ መሠረት በነጻው ጠረጴዛ ላይ ያኖራሉ፤ በየማታውም በወርቁ መቅረዝ ላይ ያሉትን ቀንዲሎች ያበራሉ፤ እኛም የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንፈጽማለን፤ እናንተ ግን ትታችሁታል።
12
እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤ መሪያችንም እርሱ ነው። መለከት የያዙ ካህናቱም የጦርነቱን ድምፅ በእናንተ ላይ ያሰማሉ። እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ አይቀናችሁምና፣ ከአባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር አትዋጉ።”
13
በዚህ ጊዜ ኢዮርብዓም ከሰራዊቱ ከፊሉን ከይሁዳ ሰራዊት በስተ ጀርባ እንዲያደፍጡ ላከ፤ የቀረውም ሰራዊት ከእርሱ ጋር የይሁዳን ሰራዊት ፊት ለፊት እንዲገጥሙ አደረገ።
14
የይሁዳም ሰዎች ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከፊትና ከኋላ መከበባቸውን አዩ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ፤ ካህናቱም መለከታቸውን ነፉ።
15
የይሁዳም ሰዎች በፉከራ የጦርነት ድምፅ አሰሙ፤ እግዚአብሔር ኢዮርብዓምንና እስራኤልን ሁሉ በአብያና በይሁዳ ፊት ፊጽሞ መታቸው።
16
እስራኤላውያን ከይሁዳ ፊት ሸሹ፤ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው።
17
አብያና ሰዎቹም ከባድ ጕዳት አደረሱባቸው፤ ከዚህ የተነሣም ከእስራኤል ብርቱ ተዋጊዎች መካከል አምስት መቶ ሺሕ ሰዎች ተገደሉ።
18
በጦርነቱም የእስራኤል ሰዎች ተዋረዱ፣ የይሁዳ ሰዎች ግን በአባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ታምነዋልና ድል ነሡ።
19
አብያም ኢዮርብዓምን አሳድዶ የቤቴልን፣ የይሻናንና የዔፍሮንን ከተሞች ከነ መንደሮቻቸው ወሰደበት።
20
ኢዮርብዓም በአብያ ዘመን እንደ ገና ሊያንሠራራ አልቻለም፤ ከዚያም እግዚአብሔር ስለ ቀሠፈው ሞተ።
21
አብያ ግን ይበልጥ እየበረታ ሄደ፤ ዐሥራ አራት ሚስቶች አግብቶም ሃያ ሁለት ወንዶችና ዐሥራ ስድስት ሴቶች ልጆች ነበሩት።
22
በአብያ ዘመን የተከናወነው ተግባር፣ እርሱ የፈጸመውና የተናገረው ሁሉ በነቢዩ በአዶ የታሪክ መዛግብት ተጽፏል።
← Chapter 12
Chapter 14 →