bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Psalms 94
Psalms 94
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
የበቀል አምላክ፣ አንተ እግዚአብሔር ሆይ፤ የበቀል አምላክ ሆይ፤ ደምቀህ ተገለጥ።
2
አንተ የምድር ዳኛ ሆይ፤ ተነሥ፤ ለትዕቢተኞች የእጃቸውን ስጣቸው።
3
ክፉዎች እስከ መቼ እግዚአብሔር ሆይ፤ ክፉዎች እስከ መቼ ይፈነጫሉ?
4
የእብሪት ቃላት ያዥጐደጕዳሉ፤ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ጕራ ይነዛሉ።
5
እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብህን አደቀቁ፤ ርስትህንም አስጨነቁ።
6
መበለቲቱንና መጻተኛውን ገደሉ፤ የድኻ ዐደጉንም ነፍስ አጠፉ።
7
እነርሱም “ እግዚአብሔር አያይም፤ የያዕቆብም አምላክ አያስተውልም” አሉ።
8
እናንት በሕዝቡ መካከል ያላችሁ ደነዞች፤ ልብ በሉ፤ እናንት ቂሎች፤ ጥበበኞች የምትሆኑት መቼ ነው?
9
ጆሮን የተከለው እርሱ አይሰማምን? ዐይንንስ የሠራ እርሱ አያይምን?
10
ሕዝቦችን በተግሣጽ ወደ መንገድ የሚመልስ፣ ዕውቀትንስ ለሰው ልጆች የሚያስተምር አይቀጣምን?
11
እግዚአብሔር የሰው ሐሳብ መና፣ ከንቱም እንደ ሆነ ያውቃል።
12
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የምትገሥጸው፣ ከሕግህም የምታስተምረው ሰው ምስጉን ነው።
13
ለኀጢአተኞች ጕድጓድ እስኪማስላቸው ድረስ፣ እርሱን ከመከራ ታሳርፈዋለህ።
14
እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና፤ ርስቱንም አይተውም።
15
ፍርድ ተመልሶ በጽድቅ አሠራር ላይ ይመሠረታል፤ ልባቸውም ቀና የሆነ ሁሉ ይከተሉታል።
16
ክፉዎችን የሚቋቋምልኝ ማን ነው? ከክፉ አድራጊዎችስ ጋር የሚሟገትልኝ ማን ነው?
17
እግዚአብሔር ረዳቴ ባይሆን ኖሮ፣ ነፍሴ ወደ ዝምታው ዓለም ፈጥና በወረደች ነበር።
18
እኔ፣ “እግሬ አዳለጠኝ” ባልሁ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ደግፎ ያዘኝ።
19
የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።
20
ዐመፃን ሕጋዊ የሚያደርግ፣ የጥፋት ዙፋን ከአንተ ጋር ሊያብር ይችላልን?
21
በጻድቁ ላይ ተሰልፈው ይወጣሉ፤ በንጹሑም ላይ ሞት ይፈርዳሉ።
22
ለእኔ ግን እግዚአብሔር ምሽግ፣ አምላኬም መጠጊያ ዐለት ሆኖኛል።
23
በደላቸውን ወደ ራሳቸው ይመልሳል፤ በክፋታቸውም ያጠፋቸዋል፤ እግዚአብሔር አምላካችን ይደመስሳቸዋል።
← Chapter 93
Chapter 95 →