bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Psalms 69
Psalms 69
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
አምላክ ሆይ፤ አድነኝ፤ ውሃ እስከ ዐንገቴ ደርሶብኛልና።
2
የእግር መቆሚያ በሌለው፣ በጥልቅ ረግረግ ውስጥ ሰጥሜአለሁ፤ ወደ ጥልቅ ውሃ ገባሁ፤ ሞገዱም አሰጠመኝ።
3
በጩኸት ደከምሁ፤ ጉረሮዬም ደረቀ፤ አምላኬን በመጠባበቅ፣ ዐይኖቼ ፈዘዙ።
4
ያለ ምክንያት የሚጠሉኝ፣ ከራሴ ጠጕር በዙ፤ ሕይወቴን ለማጥፋት የሚፈልጉ፣ በከንቱም የሚጠሉኝ ብዙዎች ሆኑ፤ ያልሰረቅሁትን ነገር፣ መልሰህ አምጣ ተባልሁ።
5
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሞኝነቴን ታውቃለህ፤ በደሌም ከአንተ የተሰወረ አይደለም።
6
ጌታ የሰራዊት አምላክ ሆይ፤ አንተን ተስፋ የሚያደርጉ፣ በእኔ ምክንያት አይፈሩ፤ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤ አንተን አጥብቀው የሚሹ፣ ከእኔ የተነሣ አይዋረዱ።
7
ስለ አንተ ስድብን ታግሻለሁና፤ ዕፍረትም ፊቴን ሸፍኗልና።
8
ለወንድሞቼ እንደ ባዕድ፣ ለእናቴም ልጆች እንደ እንግዳ ሆንሁባቸው።
9
የቤትህ ቅናት በላችኝ፤ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ዐርፏል።
10
ነፍሴን በጾም ባስመረርሁ ጊዜ፣ እነርሱ ሰደቡኝ።
11
ማቅ በለበስሁ ጊዜ፣ መተረቻ አደረጉኝ።
12
በቅጥሩ ደጅ ለሚቀመጡት የመነጋገሪያ ርእስ፣ ለሰካራሞችም መዝፈኛ ሆንሁ።
13
እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን በወደድኸው ሰዓት፣ ወደ አንተ እጸልያለሁ፤ አምላክ ሆይ፤ በታላቅ ምሕረትህ፣ በማዳንህም ርግጠኝነት መልስልኝ።
14
ከረግረግ አውጣኝ፤ እሰጥም ዘንድ አትተወኝ፤ ከጥልቅ ውሃ፣ ከእነዚያ ከሚጠሉኝ ታደገኝ።
15
ጐርፍ አያጥለቅልቀኝ፤ ጥልቅ ውሃም አይዋጠኝ፤ ጕድጓዱም ተደርምሶ አይዘጋብኝ።
16
እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ በጎ ናትና ስማኝ፤ እንደ ርኅራኄም ብዛት መለስ በልልኝ።
17
ፊትህን ከባሪያህ አትሰውር፤ ጭንቅ ውስጥ ነኝና ፈጥነህ መልስልኝ።
18
ወደ እኔ ቀርበህ ታደገኝ፤ ስለ ጠላቶቼም ተቤዠኝ።
19
የደረሰብኝን ስድብ፣ ዕፍረትና ውርደት ታውቃለህ፤ ጠላቶቼንም አንድ በአንድ ታውቃቸዋለህ።
20
ስድብ ልቤን ጐድቶታል፤ ተስፋዬም ተሟጥጧል፤ አስተዛዛኝ ፈለግሁ፤ አላገኘሁምም፤ አጽናኝም ፈለግሁ፤ አንድም አልነበረም።
21
ምግቤን ከሐሞት ቀላቀሉ፤ ለጥማቴም ሆምጣጤ ሰጡኝ።
22
የቀረበላቸው ማእድ ወጥመድ ይሁንባቸው፤ ለማኅበራቸውም አሽክላ ይሁን።
23
ዐይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፤ ጀርባቸውም ዘወትር ይጕበጥ።
24
መዓትህን በላያቸው አፍስስ፤ የቍጣህም መቅሠፍት ድንገት ይድረስባቸው።
25
ሰፈራቸው ባድማ ይሁን፤ በድንኳኖቻቸው የሚኖር አይገኝ፤
26
አንተ የመታሃቸውን አሳድደዋልና፤ ያቈሰልሃቸውንም ሥቃያቸውን አባብሰዋል።
27
በበደላቸው በደል ጨምርባቸው፤ ወደ ጽድቅህም አይግቡ።
28
ከሕይወት መጽሐፍ ይደምሰሱ፤ ከጻድቃንም ጋር አይጻፉ።
29
ነገር ግን እኔ በሥቃይና በጭንቅ ላይ እገኛለሁ፤ አምላክ ሆይ፤ ማዳንህ ደግፎ ይያዘኝ።
30
የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አወድሳለሁ፤ በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።
31
ከበሬ ይልቅ፣ ቀንድና ጥፍር ካበቀለ እንቦሳ ይልቅ ይህ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል።
32
ድኾች ይህን ያያሉ፤ ደስም ይላቸዋል፤ እናንተ እግዚአብሔርን የምትሹ ልባችሁ ይለምልም!
33
እግዚአብሔር ችግረኞችን ይሰማልና፤ በእስራት ያለውንም ሕዝቡን አይንቅም።
34
ሰማይና ምድር፣ ባሕርም፣ በውስጣቸውም የሚንቀሳቀስ ሁሉ ያመስግኑት።
35
እግዚአብሔር ጽዮንን ያድናታልና፤ የይሁዳንም ከተሞች መልሶ ይሠራቸዋልና፤ ሕዝቡም በዚያ ይሰፍራል፤ ይወርሳታልም።
36
የባሪያዎቹም ዘሮች ይወርሷታል፤ ስሙንም የሚወድዱ በዚያ ይኖራሉ።
← Chapter 68
Chapter 70 →