bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Psalms 119
Psalms 119
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
መንገዳቸው ነቀፋ የሌለበት፣ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው።
2
ምስክርነቱን የሚጠብቁ፣ በፍጹምም ልብ የሚሹት የተባረኩ ናቸው፤
3
ዐመፅን አያደርጉም፤ ነገር ግን በመንገዱ ይሄዳሉ።
4
ጠንቅቀን እንጠብቃት ዘንድ፣ አንተ ሥርዐትን አዝዘሃል።
5
ሥርዐትህን እጠብቅ ዘንድ፣ ምነው መንገዴ ጽኑ በሆነልኝ ኖሮ!
6
ወደ ትእዛዞችህ ስመለከት፣ በዚያን ጊዜ አላፍርም።
7
የጽድቅ ፍርድህን ስማር፣ በቅን ልብ ምስጋና አቀርብልሃለሁ።
8
ሥርዐትህን እጠብቃለሁ፤ ፈጽመህ አትተወኝ።
9
ጕልማሳ መንገዱን እንዴት ያነጻል? በቃልህ መሠረት በመኖር ነው።
10
በሙሉ ልቤ ፈለግሁህ፤ ከትእዛዞችህ ፈቀቅ እንዳልል አድርገኝ።
11
አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ።
12
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ።
13
ከአንደበትህ የሚወጣውን ደንብ ሁሉ፣ በከንፈሬ እናገራለሁ።
14
ሰው በሀብቱ ብዛት ደስ እንደሚለው፣ ምስክርነትህን በመከተል ደስ ይለኛል።
15
ድንጋጌህን አሰላስላለሁ፤ ልቤን በመንገድህ ላይ ጥያለሁ።
16
በሥርዐትህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልዘነጋም።
17
ሕያው እንድሆን፣ ቃልህንም እንድጠብቅ፣ ለአገልጋይህ መልካም አድርግ።
18
ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ ዐይኖቼን ክፈት።
19
እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝ፤ ትእዛዞችህን ከእኔ አትሰውር።
20
ዘወትር ደንብህን በመናፈቅ፣ ነፍሴ እጅግ ዛለች።
21
ከትእዛዞችህ የሳቱትን፣ እብሪተኞችንና ርጉሞችን ትገሥጻለህ።
22
ምስክርነትህን ጠብቄአለሁና፣ ስድብንና ንቀትን ከእኔ አርቅ።
23
ገዦች ተቀምጠው ቢዶልቱብኝ እንኳ፣ አገልጋይህ ሥርዐትህን ያሰላስላል።
24
ምስክርነትህ ለእኔ ደስታዬ ነው፤ መካሪዬም ነው።
25
ነፍሴ ከዐፈር ተጣበቀች፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ።
26
ስለ መንገዴ ገልጬ ነገርሁህ፤ አንተም መለስህልኝ፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ።
27
የድንጋጌህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፤ እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ።
28
ነፍሴ በሐዘን ተዝለፈለፈች፤ እንደ ቃልህ አበርታኝ።
29
የሽንገላን መንገድ ከእኔ አርቅ፤ ሕግህን በጸጋህ ስጠኝ።
30
የእውነትን መንገድ መርጫለሁ፤ ሕግህንም ፊት ለፊቴ አድርጌአለሁ።
31
እግዚአብሔር ሆይ፤ ከምስክርነትህ ጋር ተጣብቄአለሁ፤ አሳልፈህ ለውርደት አትስጠኝ።
32
ልቤን አስፍተህልኛልና፣ በትእዛዞችህ መንገድ እሮጣለሁ።
33
እግዚአብሔር ሆይ፤ የሥርዐትህን መንገድ አስተምረኝ፤ እኔም እስከ መጨረሻው እጠብቀዋለሁ።
34
ሕግህን እንድጠብቅ፣ በፍጹም ልቤም እንድታዘዘው፣ ማስተዋልን ስጠኝ።
35
በእርሷ ደስ ይለኛልና፣ በትእዛዝህ መንገድ ምራኝ።
36
ከራስ ጥቅም ይልቅ፣ ልቤን ወደ ምስክርነትህ አዘንብል።
37
ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ፤ በራስህ መንገድ እንደ ገና ሕያው አድርገኝ።
38
ትፈራ ዘንድ፣ ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ፈጽም።
39
የምፈራውን መዋረድ ከእኔ አርቅ፤ ደንብህ መልካም ነውና።
40
እነሆ፤ ድንጋጌህን ናፈቅሁ፤ በጽድቅህ ሕያው አድርገኝ።
41
እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ወደ እኔ ይምጣ፤ ማዳንህም እንደ ቃልህ ይላክልኝ።
42
በቃልህ ታምኛለሁና፣ ለሚሰድቡኝ መልስ እሰጣለሁ።
43
ሕግህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣ የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ።
44
ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ ሕግህን ዘወትር እጠብቃለሁ።
45
ሥርዐትህን እሻለሁና፣ እንደ ልቤ ወዲያ ወዲህ እመላለሳለሁ።
46
ምስክርነትህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ ይህን በማድረግም ዕፍረት አይሰማኝም።
47
እኔ እወድደዋለሁና፣ በትእዛዝህ ደስ ይለኛል።
48
እጆቼን ወደምወዳቸው ትእዛዞችህ አነሣለሁ፤ ሥርዐትህንም አሰላስላለሁ።
49
ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ዐስብ፤ በዚያ ተስፋ ሰጥተኸዋልና።
50
ቃልህ ሕያው ያደርገኛልና፣ ይህች በመከራዬ መጽናኛዬ ናት።
51
እብሪተኞች እጅግ ተሣለቁብኝ፤ እኔ ግን ከሕግህ ንቅንቅ አልልም።
52
እግዚአብሔር ሆይ፤ ከጥንት የነበረውን ድንጋጌህን አሰብሁ፤ በዚህም ተጽናናሁ።
53
ሕግህን ከተዉ ክፉዎች የተነሣ፣ ቍጣ ወረረኝ።
54
በእንግድነቴ አገር፣ ሥርዐትህ መዝሙሬ ናት።
55
እግዚአብሔር ሆይ፤ ስምህን በሌሊት ዐስባለሁ፤ ሕግህንም እጠብቃለሁ።
56
ሥርዐትህን እከተላለሁ፤ ይህችም ተግባሬ ሆነች።
57
እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ ቃልህን ለመታዘዝ ቈርጫለሁ።
58
በፍጹም ልቤ ፊትህን ፈለግሁ፤ እንደ ቃልህ ቸርነትህን አሳየኝ።
59
መንገዴን ቃኘሁ፤ አካሄዴንም ወደ ምስክርህ አቀናሁ።
60
ትእዛዝህን ለመጠበቅ፣ ቸኰልሁ፤ አልዘገየሁምም።
61
የክፉዎች ገመድ ተተበተበብኝ፤ እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም።
62
ስለ ጻድቅ ሥርዐትህ፣ በእኩለ ሌሊት ላመሰግንህ እነሣለሁ።
63
እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፣ ሥርዐትህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ።
64
እግዚአብሔር ሆይ፤ ምድር በምሕረትህ ተሞላች፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ።
65
እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ፣ ለአገልጋይህ በጎ ውለሃል።
66
በትእዛዞችህ አምናለሁና፣ በጎ ማስተዋልንና ዕውቀትን አስተምረኝ።
67
እንዲያው ሳይቸግረኝ መንገድ ስቼ ሄድሁ፤ አሁን ግን ቃልህን እጠብቃለሁ።
68
አንተ መልካም ነህ፤ የምታደርገው መልካም ነው፤ እንግዲህ ሥርዐትህን አስተምረኝ።
69
እብሪተኞች ስሜን በሐሰት አጠፉ፤ እኔ ግን ትእዛዝህን በፍጹም ልብ እጠብቃለሁ።
70
ልባቸው የሠባና የደነደነ ነው፤ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል።
71
ሥርዐትህን እማር ዘንድ፣ በመከራ ውስጥ ማለፌ መልካም ሆነልኝ።
72
ከአእላፋት ብርና ወርቅ ይልቅ፣ ከአፍህ የሚወጣው ሕግ ይሻለኛል።
73
እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ።
74
ቃልህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣ የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይበላቸው።
75
እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍርድህ የጽድቅ ፍርድ፣ ያስጨነቅኸኝም በታማኝነት እንደ ሆነ ዐወቅሁ።
76
ለአገልጋይህ በገባኸው ቃል መሠረት፣ ምሕረትህ ለመጽናናት ትሁነኝ።
77
ሕግህ ደስታዬ ነውና፣ በሕይወት እኖር ዘንድ ቸርነትህ ትምጣልኝ።
78
እብሪተኞች ያለ ምክንያት በደል አድርሰውብኛልና ይፈሩ፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አሰላስላለሁ።
79
አንተን የሚፈሩህ፣ ምስክርነትህንም የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ።
80
እኔ እንዳላፍር፣ ልቤ በሥርዐትህ ፍጹም ይሁን።
81
ነፍሴ ማዳንህን እጅግ ናፈቀች፤ ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ።
82
“መቼ ታጽናናኛለህ?” እያልሁ፣ ዐይኖቼ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ።
83
ጢስ የጠጣ የወይን አቍማዳ ብመስልም፣ ሥርዐትህን አልረሳሁም።
84
የባሪያህ ዕድሜ ስንት ቢሆን ነው? ታዲያ፣ በሚያሳድዱኝ ላይ የምትፈርደው መቼ ይሆን?
85
በሕግህ መሠረት የማይሄዱ እብሪተኞች ማጥመጃ ጕድጓድ ቈፈሩልኝ።
86
ትእዛዞችህ ሁሉ አስተማማኝ ናቸው፤ ሰዎች ያለ ምክንያት አሳድደውኛልና ርዳኝ።
87
ከምድር ላይ ሊያስወግዱኝ ጥቂት ቀራቸው፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አልተውሁም።
88
እንደ ምሕረትህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ፤ እኔም የአፍህን ምስክርነት እጠብቃለሁ።
89
እግዚአብሔር ሆይ፤ ቃልህ በሰማይ፣ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
90
ታማኝነትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሁሉ ይኖራል፤ ምድርን መሠረትሃት፤ እርሷም ጸንታ ትኖራለች።
91
ሁሉም አገልጋይህ ነውና፣ በሕግህ መሠረት እስከ ዛሬ ድረስ ጸንተው ይኖራሉ።
92
ሕግህ ደስታዬ ባይሆን ኖሮ፣ በመከራዬ ወቅት በጠፋሁ ነበር።
93
በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና፣ ትእዛዝህን ከቶ አልረሳም።
94
እኔ የአንተ ነኝ፤ እባክህ አድነኝ፤ ሕግህንም ፈልጌአለሁና።
95
ክፉዎች ሊያጠፉኝ አድብተዋል፤ እኔ ግን ምስክርነትህን አሰላስላለሁ።
96
ለፍጹምነት ሁሉ ዳርቻ እንዳለው አየሁ፤ ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው።
97
አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ።
98
ትእዛዞችህ ምንጊዜም ስለማይለዩኝ፣ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረጉኝ።
99
ምስክርነትህን አሰላስላለሁና፣ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የላቀ አስተዋይ ልብ አገኘሁ።
100
መመሪያህን ተከትዬ እሄዳለሁና፣ ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ ሆንሁ።
101
ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፣ እግሬን ከክፉ መንገድ ሁሉ ከለከልሁ።
102
አንተው ራስህ አስተምረኸኛልና፣ ከድንጋጌህ ዘወር አላልሁም።
103
ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው! ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው።
104
ከመመሪያህ ማስተዋልን አገኘሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ።
105
ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው።
106
የጽድቅ ሕግህን ለመጠበቅ፤ ምያለሁ፤ ይህንኑ አጸናለሁ።
107
እጅግ ተቸግሬአለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ።
108
እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈቅጄ ያቀረብሁትን የአፌን የምስጋና መሥዋዕት ተቀበል፤ ሕግህንም አስተምረኝ።
109
ነፍሴ ዘወትር አደጋ ላይ ናት፤ ሕግህን ግን አልረሳሁም።
110
ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤ እኔ ግን መመሪያህን አልተላለፍሁም።
111
ምስክርነትህ የዘላለም ውርሴ ናት፤ ልቤ በዚህ ሐሤት ያደርጋልና።
112
ትእዛዝህን ለዘላለም፣ እስከ ወዲያኛው ለመፈጸም፣ ልቤን ወደዚያው አዘነበልሁ።
113
መንታ ልብ ያላቸውን ጠላሁ፤ ሕግህን ግን ወደድሁ።
114
አንተ መጠጊያዬና ጋሻዬ ነህ፤ ቃልህን በተስፋ እጠብቃለሁ።
115
የአምላኬን ትእዛዞች እጠብቅ ዘንድ፣ እናንት ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ራቁ።
116
እንደ ቃልህ ደግፈኝ፤ እኔም ሕያው እሆናለሁ፤ ተስፋዬም መና ቀርቶ አልፈር።
117
ያለ ሥጋት እቀመጥ ዘንድ ደግፈህ ያዘኝ፤ ሥርዐትህንም ዘወትር እመለከታለሁ።
118
መሠሪነታቸው በከንቱ ነውና፣ ከሥርዐትህ ውጭ የሚሄዱትን ሁሉ ወዲያ አስወገድሃቸው።
119
የምድርን ክፉዎች ሁሉ እንደ ጥራጊ አስወገድሃቸው፤ ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ።
120
ሥጋዬ አንተን በመፍራት ይንቀጠቀጣል፤ ፍርድህንም እፈራለሁ።
121
ፍትሕና ጽድቅ ያለበትን ሠርቻለሁ፤ ለሚጨቍኑኝ አሳልፈህ አትስጠኝ።
122
ለባሪያህ በጎነት ዋስትና ሁን፤ እብሪተኞች እንዲጨቍኑኝ አትፍቀድላቸው።
123
ዐይኖቼ ማዳንህን፣ የጽድቅ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ።
124
ለባሪያህ እንደ ምሕረትህ መጠን አድርግ፤ ሥርዐትህንም አስተምረኝ።
125
እኔ ባሪያህ ነኝ፤ ምስክርነትህን ዐውቅ ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ።
126
እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕግህ እየተጣሰ ነውና፣ ጊዜው አንተ የምትሠራበት ነው።
127
ስለዚህ ከወርቅ፣ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ፣ ትእዛዞችህን ወደድሁ።
128
መመሪያህ ሙሉ በሙሉ ልክ ነው አልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ።
129
ምስክርነትህ ሁሉ ድንቅ ነው፤ ስለዚህ ነፍሴ ትጠብቀዋለች።
130
የቃልህ ትርጓሜ ያበራል፤ አላዋቂዎችንም አስተዋዮች ያደርጋል።
131
ትእዛዝህን ናፍቄአለሁና፣ አፌን ከፈትሁ፤ አለከለክሁም።
132
ስምህን ለሚወድዱ ማድረግ ልማድህ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ወደ እኔ ተመልሰህ ምሕረት አድርግልኝ።
133
አካሄዴን እንደ ቃልህ ቀና አድርግልኝ፤ ኀጢአትም በላዬ እንዲሠለጥን አትፍቀድ።
134
ትእዛዝህን መጠበቅ እንድችል፣ ከሰዎች ጥቃት ታደገኝ።
135
በባሪያህ ላይ ፊትህን አብራ፤ ሥርዐትህንም አስተምረኝ።
136
ሕግህ ባለመከበሩ፤ እንባዬ እንደ ውሃ ይፈስሳል።
137
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ፍርድህም ትክክል ነው።
138
ምስክርነትህን በጽድቅ አዘዝህ፤ እጅግ አስተማማኝም ነው።
139
ጠላቶቼ ቃልህን ዘንግተዋልና፣ ቅናት አሳረረኝ።
140
ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፤ ባሪያህም ወደደው።
141
እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፤ ነገር ግን መመሪያህን አልዘነጋሁም።
142
ጽድቅህ ዘላለማዊ ጽድቅ ነው፤ ሕግህም እውነት ነው።
143
መከራና ሥቃይ ደርሶብኛል፤ ነገር ግን ትእዛዝህ ደስታዬ ነው።
144
ምስክርነትህ ለዘላለም የጽድቅ ምስክርነት ነው፤ በሕይወት እኖር ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ።
145
እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ እጮኻለሁና መልስልኝ፤ ሥርዐትህንም እጠብቃለሁ።
146
ወደ አንተ እጣራለሁና አድነኝ፤ ምስክርነትህንም እጠብቃለሁ።
147
ትረዳኝ ዘንድ ጎሕ ሳይቀድድ ተነሥቼ እጮኻለሁ፤ ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ።
148
ቃልህን አሰላስል ዘንድ፣ ዐይኔ ሌሊቱን ሙሉ ሳይከደን ያድራል።
149
እንደ ቸርነትህ መጠን ድምፄን ስማ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ሕግህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ።
150
ደባ የሚያውጠነጥኑ ወደ እኔ ቀርበዋል፤ ከሕግህ ግን የራቁ ናቸው።
151
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ቅርብ ነህ፤ ትእዛዞችህም ሁሉ እውነት ናቸው።
152
ለዘላለም እንደ መሠረትሃቸው፣ ከጥንት ምስክርነትህ ተረድቻለሁ።
153
ሕግህን አልረሳሁምና፣ ሥቃዬን ተመልከት፤ ታደገኝም።
154
ተሟገትልኝ፤ አድነኝም፤ እንደ ቃልህም ሕያው አድርገኝ።
155
ሥርዐትህን ስለማይሹ፣ ድነት ከክፉዎች የራቀ ነው።
156
እግዚአብሔር ሆይ፤ ርኅራኄህ ታላቅ ነው፤ እንደ ሕግህ ሕያው አድርገኝ።
157
የሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ ብዙዎች ናቸው፤ እኔ ግን ከምስክርህ ዘወር አላልሁም።
158
ቃልህን አይጠብቁምና፣ ከዳተኞችን አይቼ አርቃቸዋለሁ።
159
መመሪያህን እንዴት እንደምወድድ ተመልከት፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ።
160
ቃልህ በሙሉ እውነት ነው፤ ጻድቅ የሆነው ሕግህም ዘላለማዊ ነው።
161
ገዦች ያለ ምክንያት አሳደዱኝ፤ ልቤ ግን ከቃልህ የተነሣ እጅግ ፈራ።
162
ትልቅ ምርኮ እንዳገኘ ሰው፣ በቃልህ ደስ አለኝ።
163
ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁ፤ ሕግህን ግን ወደድሁ።
164
ጻድቅ ስለ ሆነው ሕግህ፣ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ።
165
ሕግህን የሚወድዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ ዕንቅፋትም የለባቸውም።
166
እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ተስፋ አደርጋለሁ፤ ትእዛዝህንም እፈጽማለሁ።
167
ነፍሴ ምስክርነትህን ትጠብቃለች፤ እጅግ እወድደዋለሁና።
168
መንገዴ ሁሉ በፊትህ ግልጽ ነውና፣ ሕግህንና ምስክርነትህን እጠብቃለሁ።
169
እግዚአብሔር ሆይ፤ ጩኸቴ ከፊትህ ይድረስ፤ እንደ ቃልህም ማስተዋልን ስጠኝ።
170
ልመናዬ ከፊትህ ይድረስ፤ እንደ ቃልህም ታደገኝ።
171
ሥርዐትህን አስተምረኸኛልና፣ ከንፈሮቼ ምስጋናን አፈለቁ።
172
ትእዛዞችህ ሁሉ የጽድቅ ትእዛዞች ናቸውና፣ አንደበቴ ስለ ቃልህ ይዘምር።
173
ትእዛዝህን መርጫለሁና፣ እጅህ እኔን ለመርዳት ዝግጁ ይሁን።
174
እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ናፈቅሁ፤ ሕግህም ደስታዬ ነው።
175
አመሰግንህ ዘንድ በሕይወት ልኑር፤ ሕግህም ይርዳኝ።
176
እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፤ ትእዛዞችህን አልረሳሁምና፣ ባሪያህን ፈልገው።
← Chapter 118
Chapter 120 →