bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Proverbs 18
Proverbs 18
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ወዳጅነትን የማይፈልግ ሰው የራሱን ፍላጎት ብቻ ይከተላል፤ ቅን የሆነውንም ፍርድ ሁሉ ይቃወማል።
2
ተላላ ከማስተዋል ርካታን አያገኝም፤ የራሱን ሐሳብ በመግለጥ ግን ደስ ይለዋል።
3
ክፋት ስትመጣ ንቀት ትከተላለች፤ ከዕፍረትም ጋር ውርደት ትመጣለች።
4
ከሰው አፍ የሚወጡ ቃላት ጥልቅ ውሆች ናቸው፤ የጥበብም ምንጭ እንደሚንዶለዶል ፏፏቴ ነው።
5
ለክፉ ሰው ማድላት፣ ንጹሑንም ፍትሕ መንሣት ተገቢ አይደለም።
6
የተላላ ከንፈር ጠብ ያመጣበታል፤ አፉም በትር ይጋብዛል።
7
ተላላ ሰው አፉ መጥፊያው ነው፤ ከንፈሮቹም ለነፍሱ ወጥመድ ናቸው።
8
የሐሜተኛ ቃል እንደ ጣፋጭ ጕርሻ ነው፤ ወደ ሰው ውስጣዊ ክፍል ዘልቆ ይገባል።
9
ለሥራው ደንታ የሌለው ሰው፣ የአጥፊ ወንድም ነው።
10
የእግዚአብሔር ስም ጽኑ ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ በመሮጥ ተገን ያገኝበታል።
11
የባለጠጎች ሀብት የተመሸገ ከተማቸው ነው፤ እንደማይወጣ ረዥም ግንብም ይቈጥሩታል።
12
ከውድቀቱ በፊት ሰው ልቡ ይታበያል፤ ትሕትና ግን ክብርን ትቀድማለች።
13
ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስ፣ ቂልነትና ዕፍረት ይሆንበታል።
14
በሕመም ጊዜ፣ ሰውን መንፈሱ ትደግፈዋለች፤ የተሰበረውን መንፈስ ግን ማን ሊሸከም ይችላል?
15
የአስተዋይ ልብ ዕውቀትን ይገበያል፤ የጠቢብም ጆሮ አጥብቆ ይሻታል።
16
እጅ መንሻ ለሰጪው መንገድ ትከፍትለታለች፤ ታላላቅ ሰዎች ፊትም ታቀርበዋለች።
17
አስቀድሞ ጕዳዩን የሚያሰማ ትክክለኛ ይመስላል፤ ይኸውም ባላንጣው መጥቶ እስከሚመረመር ድረስ ነው።
18
ዕጣ መጣጣል ሙግትን ያስቆማል፤ ኀይለኛ ባላንጣዎችንም ይገላግላል።
19
የተበደለ ወንድም ከተመሸገ ከተማ ይበልጥ የማይበገር ነው፤ ጠቡም እንደ ጠንካራ የግንብ መዝጊያ ነው።
20
ሰው በአንደበቱ ፍሬ ሆዱ ይጠግባል፤ በከንፈሩም ምርት ይረካል።
21
አንደበት የሞትና የሕይወት ኀይል አላት፤ የሚወድዷትም ፍሬዋን ይበላሉ።
22
ሚስት የሚያገኝ መልካም ነገርን ያገኛል፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ሞገስን ይቀበላል።
23
ድኻ በመለማመጥ ምሕረት ይለምናል፤ ሀብታም ግን በማናለብኝነት ይመልሳል።
24
ወዳጅ የሚያበዛ ሰው ራሱን ለጥፋት ይዳርጋል፤ ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚቀርብ ጓደኛም አለ።
← Chapter 17
Chapter 19 →