bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Numbers 32
Numbers 32
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እጅግ ብዙ የሆነ የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋዎች የነበሯቸው የሮቤልና የጋድ ነገዶች የኢያዜርና የገለዓድ ምድር ለከብት ምቹ ስፍራዎች መሆናቸውን አዩ።
2
ስለዚህ ወደ ሙሴ፣ ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛርና ወደ ማኅበረ ሰቡ መሪዎች መጥተው እንዲህ አሉ፤
3
“አጣሮት፣ ዲቦን፣ ኢያዜር፣ ኒምራ፣ ሐሴቦን፣ ኤልያሊ፣ ሴባማ፣ ናባውና፣ ባያን፣
4
እግዚአብሔር (ያህዌ) በእስራኤል ሕዝብ ፊት እንዲሸነፍ ያደረገው ይህ ሁሉ ምድር ለከብት ምቹ ነው፤ እኛ አገልጋዮችህም ከብቶች አሉን።
5
በፊትህ ሞገስ ያገኘን ከሆነ ይህ ምድር ለእኛ ለአገልጋዮችህ በርስትነት ይሰጠን፤ ዮርዳኖስንም እንድንሻገር አታድርገን።”
6
ሙሴም የጋድንና የሮቤልን ነገዶች እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እዚህ ተቀምጣችሁ ወገኖቻችሁ ወደ ጦርነት ይሂዱ?
7
እስራኤላውያን ተሻግረው እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ ተስፋ የምታስቈርጧቸው ለምንድን ነው?
8
አባቶቻችሁ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከቃዴስ በርኔ በላክኋቸው ጊዜም ያደረጉት ይህንኑ ነበር።
9
ወደ ኤሽኮል ሸለቆ ሄደው ምድሪቱን ካዩ በኋላ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ እስራኤላውያንን ተስፋ አስቈረጧቸው።
10
በዚያም ቀን የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ ነደደ፤ እንዲህም ሲል ማለ፤
11
‘በፍጹም ልባቸው ስላልተከተሉኝ ከግብፅ ከወጡት፣ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች አንዳቸውም ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ልሰጥ በመሐላ ቃል የገባሁላቸውን ምድር አያዩዋትም፤
12
እግዚአብሔርን (ያህዌ) በፍጹም ልባቸው ተከትለውታልና፣ ከቄኔዛዊው ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በስተቀር አንዳቸውም አያዩዋትም።’
13
የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ቍጣ በእስራኤል ላይ ስለ ነደደ፣ በፊቱ ክፉ ነገር ያደረገው ያ ትውልድ በሙሉ እስኪያልቅ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ እንዲንከራተቱ አደረጋቸው።
14
“እናንት የኀጢአተኞች ልጆች ይኸው በአባቶቻችሁ እግር ተተክታችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ) በእስራኤል ላይ ይበልጥ እንዲቈጣ ታደርጋላችሁ።
15
እርሱን ከመከተል ብትመለሱ አሁንም ይህን ሁሉ ሕዝብ በምድረ በዳ ይተወዋል፤ ለሚደርስበትም ጥፋት ምክንያቱ እናንተው ትሆናላችሁ።”
16
ከዚህ በኋላ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፤ “እዚህ ለከብቶቻችን በረቶች፣ ለሴቶቻችንና ለልጆቻችን ከተሞች መሥራት እንወድዳለን፤
17
ይሁን እንጂ ወደ ስፍራቸው እስክናገባቸው ድረስ ታጥቀንና በእስራኤላውያን ፊት ግንባር ቀደም ሆነን ለመሄድ ዝግጁ ነን፤ በዚህም ጊዜ ሴቶቻችንና ልጆቻችን በምድሪቱ ላይ ካሉት ነዋሪዎች እንዲጠበቁ በተመሸጉ ከተሞች ይኖራሉ።
18
እኛም እያንዳንዱ እስራኤላዊ ርስቱን እስኪወርስ ድረስ ወደየቤታችን አንመለስም።
19
ድርሻችንን ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ስላገኘን፣ ከዮርዳኖስ ማዶ ከእነርሱ ጋር የምንካፈለው አንዳችም ርስት አይኖርም።”
20
ከዚያም ሙሴ እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ብታደርጉ ማለትም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ታጥቃችሁ ለጦርነት ብትዘጋጁ፣
21
እንዲሁም ጠላቶቹን ከፊቱ አሳድዶ እስኪያስወጣ ድረስ ሁላችሁም በእግዚአብሔር ፊት ለጦርነት ዝግጁ ሆናችሁ ዮርዳኖስን ብትሻገሩ፣
22
ምድሪቱ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከተገዛች በኋላ ልትመለሱ ትችላላችሁ፤ ለእግዚአብሔርና (ያህዌ) ለእስራኤል ካለባችሁም ግዴታ ነጻ ትሆናላችሁ፤ ይህችም ምድር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ርስታችሁ ትሆናለች።
23
“ይህን ባታደርጉ ግን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ትበድላላችሁ፤ ኀጢአታችሁ እንደሚያገኛችሁም ዕወቁ።
24
ለሴቶቻችሁና ለልጆቻችሁ ከተሞች፣ ለበግና ለፍየል መንጎቻችሁም ጕረኖች ሥሩላቸው፤ የገባችሁበትን የተስፋ ቃል ግን ፈጽሙ።”
25
የጋድና የሮቤል ሰዎች ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “እኛ አገልጋዮችህ ጌታችን ያዘዘንን እንፈጽማለን።
26
ልጆቻችንና ሚስቶቻችን፣ የበግና የፍየል እንዲሁም የከብት መንጎቻችን እዚሁ በገለዓድ ከተሞች ይቀራሉ፤
27
ባሮችህ ግን ልክ ጌታችን እንዳለው እያንዳንዱ ሰው ለጦርነት ዝግጁ ሆኖ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለመዋጋት እንሻገራለን።”
28
ከዚያም ሙሴ ለካህኑ ለአልዓዛር፣ ለነዌ ልጅ ለኢያሱና ለእስራኤል ነገድ ቤተ ሰብ አለቆች እነርሱን አስመልክቶ ትእዛዝ ሰጠ፤
29
እንዲህም አላቸው፤ “የጋድና የሮቤል ወንድ ሁሉ፣ እያንዳንዱ ለጦርነት በመዘጋጀት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ከእናንተ ጋር ዮርዳኖስን የሚሻገር ከሆነ፣ ምድሪቱም በእጃችሁ ስትገባ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ስጧቸው።
30
ለጦርነት ተዘጋጅተው ከእናንተ ጋር ካልተሻገሩ ግን፣ ርስታቸውን አብረዋችሁ በከነዓን መካፈል አለባቸው።”
31
የጋድና የሮቤል ሰዎች እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ባሪያዎችህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ያደርጋሉ፤
32
ለጦርነት ዝግጁ ሆነን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወደ ከነዓን እንሻገራለን፤ የምንወርሰው ርስት ግን ከዮርዳኖስ ወዲህ እዚሁ ይሆናል።”
33
ከዚያም ሙሴ፣ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛትና የባሳንን ንጉሥ የዐግን ግዛት፣ ማለትም ምድሪቱንና ከነከተሞቿ በዙሪያዋ ያለውን ግዛት በሙሉ ለጋድና ለሮቤል ነገዶች እንዲሁም ለዮሴፍ ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጣቸው።
34
የጋድ ልጆች፤ ዲቦንን፣ አጣሮትን፣ አሮዔርን፣
35
ዓጥሮትሾፋንን፣ ኢያዜርን፣ ዮግብሃን፣
36
ቤትነምራንና ቤትሃራንን የተመሸጉ ከተሞች አድርገው ሠሯቸው፤ እንዲሁም ለበግና ለፍየል መንጎቻቸው ጕረኖዎች አበጁላቸው።
37
የሮቤልም ልጆች ሐሴቦንን፣ ኤልያሊንና ቂርያታይምን
38
እንዲሁም ስማቸው የተለወጠውን ናባውን፣ በአልሜዎንን፣ ሴባማንን ዐደሱ፤ ላደሷቸውም ከተሞች ስም አወጡላቸው።
39
የምናሴ ልጅ የሆነው የማኪር ዘሮች ወደ ገለዓድ ሄደው ምድሪቱን በመያዝ፣ እዚያ የነበሩትን አሞራውያን አሳደዷቸው፤
40
ስለዚህ ሙሴ ገለዓድን የምናሴ ዘሮች ለሆኑት ለማኪራውያን ሰጣቸው፤ እነርሱም መኖሪያቸውን በዚያው አደረጉ።
41
ከምናሴ ነገድ የሆነው ኢያዕር መኖሪያቸውን ወስዶ፣ “የኢያዕር መንደሮች” ብሎ ሰየማቸው።
42
እንዲሁም ኖባህ ቄናትንና በዙሪያዋ ያሉትን መንደሮች በመያዝ በራሱ ስም፣ “ኖባህ” ብሎ ጠራቸው።
← Chapter 31
Chapter 33 →