bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Numbers 31
Numbers 31
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣
2
“ለእስራኤላውያን ምድያማውያንን ተበቀልላቸው፤ ከዚያም ወደ ወገኖችህ ትከማቻለህ” አለው።
3
ስለዚህ ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “ምድያማውያንን ለመውጋት እንዲሄዱና ስለ እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲበቀሏቸው ከሰዎቻችሁ ጥቂቶቹን ለጦርነት አዘጋጁ።
4
ከእያንዳንዱም የእስራኤል ነገድ አንዳንድ ሺሕ ሰው ለጦርነቱ ላኩ።”
5
ስለዚህ ከእስራኤል ጐሣዎች ተወጣጥቶ ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ ሺሕ፣ በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ሺሕ ሰው ለጦርነት ተዘጋጀ።
6
ሙሴም የቤተ መቅደሱን ንዋየ ቅድሳትና ምልክት መስጫ የሆኑትን መለከቶች ከያዘው ከካህኑ ከአልዓዛር ልጅ ከፊንሐስ ጋር ከየነገዱ አንዳንድ ሺሕ ሰው ለጦርነት ላከ።
7
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት ከምድያም ጋር ተዋጉ፤ ወንዱንም በሙሉ ፈጁት፤
8
ከተገደሉትም መካከል አምስቱ የምድያም ነገሥታት ኤዊ፣ ሮቆም፣ ሱር፣ ሑርና ሪባ ይገኙባቸዋል፤ የቢዖርን ልጅ በለዓምንም በሰይፍ ገደሉት።
9
ከዚያም እስራኤላውያን የምድያማውያንን ሴቶችና ሕፃናት ማረኩ፤ የቀንድ ከብቶቻቸውን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻቸውን ሁሉ ነዱ፤ ሀብታቸውንም በሙሉ ወሰዱ።
10
ምድያማውያኑ የሚኖሩባቸውን ከተሞች ሁሉ ሰፈሮቻቸውንም በሙሉ አቃጠሉ።
11
ሰውና እንስሳትን ጨምሮ የማረኩትንና የዘረፉትን ሁሉ እንዳለ አጋዙት።
12
የማረኳቸውን ሰዎች፣ የነዷቸውን እንስሳትና የዘረፉትን ሀብት በሙሉ፣ ከኢያሪኮ ማዶ፣ በዮርዳኖስ አጠገብ፣ በሞዓብ ወዳለው፣ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር እንዲሁም መላው የእስራኤላውያን ማኅበር ወዳሉበት ሰፈራቸው አመጧቸው።
13
ሙሴ፣ ካህኑ አልዓዛርና የማኅበረ ሰቡ መሪዎች በሙሉ ሊቀበሏቸው ከሰፈር ወጡ።
14
ሙሴም ከጦርነት በተመለሱት በሰራዊቱ አዛዦች፣ ማለትም በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ።
15
እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ሴቶችን ሁሉ እንዴት በሕይወት ትተዉአቸዋላችሁ?”
16
የበለዓምን ምክር ተቀብለው በፌጎር በተፈጸመው ድርጊት እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲመለሱና የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ሕዝብ እንዲቀሠፍ ያደረጉት እነርሱ ናቸው።
17
አሁንም ወንዶቹን ልጆች ሁሉ፣ ወንድ ያወቍትንም ሴቶች በሙሉ ግደሏቸው፤
18
ነገር ግን ወንድ ያላወቁትን ልጃገረዶች ሁሉ ለራሳችሁ አስቀሯቸው።
19
“ከእናንተ መካከል ሰው የገደለ ወይም የተገደለውን የነካ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን ይቈይ። በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ራሳችሁንና ምርኮኞቻችሁን አንጹ።
20
ማናቸውንም ልብስ እንዲሁም ከቈዳ፣ ከፍየል ጠጕር ወይም ከዕንጨት የተሠራ ማንኛውንም ነገር አንጹ።”
21
ከዚያም ካህኑ አልዓዛር ወደ ጦርነት ሄደው የነበሩትን ወታደሮች እንዲህ አላቸው፤ “ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ የሰጠው የሕጉ ሥርዐት ይህ ነው፤
22
ወርቅ፣ ብር፣ ናስ፣ ብረት፣ ቈርቈሮ፣ እርሳስ
23
እንዲሁም እሳትን መቋቋም የሚችል ማንኛውም ነገር በእሳት ውስጥ ማለፍ አለበት፤ ከዚያም ንጹሕ ይሆናል፤ ይህም ሆኖ መንጻት አለበት። እሳትን መቋቋም የማይችል ማንኛውም ነገር በዚሁ ውሃ ውስጥ ማለፍ አለበት።
24
በሰባተኛው ቀን ልብሳችሁን ዕጠቡ፤ ትነጻላችሁም፤ ከዚያም ወደ ሰፈር መግባት ትችላላችሁ።”
25
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
26
“አንተ፣ ካህኑ አልዓዛርና በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ያሉት የየቤተ ሰቡ አለቆች ሆናችሁ የተማረከውን ሕዝብና እንስሳት ሁሉ ቍጠሩ።
27
ምርኮውንም ለሁለት ከፍላችሁ በጦርነቱ ለተካፈሉት ወታደሮችና ለቀረው ማኅበረ ሰብ አከፋፍሉት።
28
በጦርነቱ ከተካፈሉት ወታደሮች ድርሻ ላይ፣ ከሰውም ሆነ ከቀንድ ከብት፣ ከአህያ፣ ከበግ ወይም ከፍየል ከየአምስት መቶው አንዱን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ግብር አውጣ።
29
ይህንም ግብር ከድርሻቸው ላይ ወስደህ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፈንታ በማድረግ ለካህኑ ለአልዓዛር ስጠው።
30
ከእስራኤላውያን እኩሌታ ድርሻ ደግሞ ከሰውም ይሁን ከቀንድ ከብት፣ ከአህያ፣ ከበግ፣ ከፍየል ወይም ከሌሎች እንስሳት ከየአምሳው አንዳንድ መርጠህ፣ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ማደሪያ ድንኳን በኀላፊነት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ስጣቸው።”
31
ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።
32
ወታደሮቹ ማርከው ከወሰዱለት ምርኮ ውስጥ የቀረው ይህ ነበር፤ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺሕ በግ፣
33
ሰባ ሁለት ሺሕ የቀንድ ከብት፣
34
ስድሳ አንድ ሺሕ አህያ
35
ወንድ ያላወቁ ሠላሳ ሁለት ሺሕ ሴቶች።
36
በጦርነቱ ላይ የነበሩት ወታደሮች እኩሌታ ድርሻ ይህ ነበር፤ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺሕ አምስት መቶ በግ፣
37
ከእነዚህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠ ግብር ስድስት መቶ ሰባ አምስት ነበር።
38
ሠላሳ ስድስት ሺሕ የቀንድ ከብት፣ ከእነዚህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠው ግብር ሰባ ሁለት ነበር።
39
ሠላሳ ሺሕ አምስት መቶ አህያ፣ ከእነዚህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠው ግብር ስድሳ አንድ ነበር።
40
ዐሥራ ስድስት ሺሕ ሰው፣ ከእነዚህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠው ግብር ሠላሳ ሁለት ነበር።
41
ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው የእግዚአብሔር (ያህዌ) ድርሻ የሆነውን ግብር ለአልዓዛር ሰጠው።
42
ሙሴ ከዘመቱት ሰዎች የለየው የእስራኤላውያን እኩሌታ ድርሻ ማለትም፣
43
የማኅበረ ሰቡ ድርሻ ይህ ነበር፤ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺሕ አምስት መቶ በግ፣
44
ሠላሳ ስድስት ሺሕ የቀንድ ከብት፣
45
ሠላሳ ሺሕ አምስት መቶ አህያ፣
46
ዐሥራ ስድስት ሺሕ ሰው።
47
ከእስራኤላውያን እኩሌታ ድርሻ ላይ፣ ሙሴ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው ከየአምሳው ሰውና እንስሳ አንዳንድ መርጦ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ማደሪያ ድንኳን በኀላፊነት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ሰጣቸው።
48
ከዚያም በኋላ በሰራዊቱ ክፍሎች ላይ የተሾሙት የሻለቆችና የመቶ አለቆች ወደ ሙሴ ቀርበው፣
49
እንዲህ አሉት፤ “እኛ አገልጋዮችህ በእጃችን ሥር ያሉትን ወታደሮች ቈጥረናል፤ አንድም የጐደለ የለም።
50
ስለዚህ እያንዳንዳችን ያገኘነውን የወርቅ ጌጣጌጥ፣ የእግር ዐልቦዎች፣ የእጅ አንባሮች፣ የጣት ቀለበቶች፣ የጆሮ ጕትቻዎችና የዐንገት ሐብሎች በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ማስተስረያ እንዲሆነን መባ አድርገን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አምጥተናል።”
51
ሙሴና ካህኑ አልዓዛር በጌጣጌጥ መልክ የተሠራውን ወርቅ ሁሉ ተቀበሏቸው።
52
ሙሴና አልዓዛር ከሻለቆቹና ከመቶ አለቆቹ በመቀበል ስጦታ አድርገው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቀረቡት ወርቅ ዐሥራ ስድስት ሺሕ ሰባት መቶ አምሳ ሰቅል መዘነ።
53
እያንዳንዱም ወታደር ለራሱ የወሰደው ምርኮ ነበረው።
54
ሙሴና ካህኑ አልዓዛር ወርቁን ከሻለቆቹና ከመቶ አለቆቹ ተቀብለው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለእስራኤላውያን መታሰቢያ እንዲሆን ወደ መገናኛው ድንኳን አመጡት።
← Chapter 30
Chapter 32 →