bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Micah 7
Micah 7
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ለእኔ ወዮልኝ! የወይን ዕርሻ በሚቃረምበት ጊዜ፣ የበጋ ፍራፍሬ እንደሚለቅም ሰው ሆኛለሁ፤ የሚበላ የወይን ዘለላ የለም፤ የምንጓጓለት፣ ቶሎ የሚደርሰው በለስም አልተገኘም።
2
ፈሪሀ እግዚአብሔር ያደረበት ሰው ከምድር ጠፍቷል፤ አንድም እንኳ ቅን ሰው የለም፤ ሰው ሁሉ ደም ለማፍሰስ ያደባል፤ እያንዳንዱም ወንድሙን በመረብ ያጠምዳል።
3
እጆቹ ክፉ ለማድረግ ሠልጥነዋል፤ ገዥው እጅ መንሻ ይፈልጋል፤ ፈራጁ ጕቦ ይቀበላል፤ ኀይለኞች ያሻቸውን ያስፈጽማሉ፤ ሁሉም አንድ ላይ ያሤራሉ።
4
ከእነርሱ ይሻላል የተባለው እንደ አሜከላ፣ እጅግ ቀና የተባለውም እንደ ኵርንችት ነው፤ የጠባቂዎቻችሁ ቀን ደርሷል፤ የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን መጥቷል፤ የሚሸበሩበትም ጊዜ አሁን ደርሷል።
5
ባልንጀራህን አትመን፤ በጓደኛህም አትታመን፤ በዕቅፍህ ለምትተኛዋ እንኳ፣ ስለምትነግራት ቃል ተጠንቀቅ።
6
ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃል፤ ሴት ልጅ በእናቷ ላይ፣ ምራት በዐማቷ ላይ ትነሣለች፤ የሰው ጠላቶች የገዛ ቤተ ሰዎቹ ናቸውና።
7
እኔ ግን እግዚአብሔርን ተስፋ አደርጋለሁ፤ አዳኜ የሆነውን አምላክ እጠብቃለሁ፤ አምላኬ ይሰማኛል።
8
ጠላቴ ሆይ፤ በእኔ ላይ በደረሰው ደስ አይበልሽ! ብወድቅም እንኳ እነሣለሁ፤ በጨለማ ብቀመጥ እንኳ፣ እግዚአብሔር ብርሃኔ ይሆናል።
9
እርሱን ስለ በደልሁ፣ እስኪቆምልኝ እስኪፈርድልኝም ድረስ፣ የእግዚአብሔርን ቍጣ እቀበላለሁ፤ እርሱ ወደ ብርሃን ያወጣኛል፤ እኔም ጽድቁን አያለሁ።
10
ጠላቴም ታያለች፤ ኀፍረትንም ትከናነባለች፤ “አምላክህ እግዚአብሔር የት አለ?” ያለችኝን፣ ዐይኖቼ ውድቀቷን ያያሉ፤ አሁንም እንኳ፣ እንደ መንገድ ጭቃ ትረገጣለች።
11
ቅጥሮቻችሁን የምትሠሩበት፣ ድንበራችሁንም የምታሰፉበት ቀን ይመጣል።
12
በዚያ ቀን ሰዎች፣ ከአሦር እስከ ግብፅ ከተሞች፣ ከግብፅ እስከ ኤፍራጥስ፣ ከባሕር ወደ ባሕር፣ ከተራራ ወደ ተራራ ወደ እናንተ ይመጣሉ።
13
ከሥራቸው የተነሣ፣ በነዋሪዎቿ ምክንያት ምድር ባድማ ትሆናለች።
14
ብቻቸውን በዱር ውስጥ፣ በለመለመ መስክ የሚኖሩትን፣ የርስትህ መንጋ የሆኑትን፣ ሕዝብህን በበትርህ ጠብቅ፤ እንደ ቀድሞው ዘመን፣ በባሳንና በገለዓድ ይሰማሩ።
15
“ከግብፅ እንደ ወጣህበት ዘመን ሁሉ፣ ታምራቴን አሳያቸዋለሁ።”
16
አሕዛብ ያያሉ፣ ያፍራሉም፤ ኀይላቸውን ሁሉ ያጣሉ፤ አፋቸውን በእጃቸው ይይዛሉ፤ ጆሯቸውም ትደነቍራለች።
17
በደረታቸው እንደሚሳቡ ፍጥረታት፣ እንደ እባብም ትቢያ ይልሳሉ፤ ከዋሻቸው እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ፤ በፍርሀትም ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ይመለሳሉ፤ እናንተንም ይፈራሉ።
18
የርስቱን ትሩፍ ኀጢአት ይቅር የሚል፣ የሚምር እንደ አንተ ያለ አምላክ ማነው? ለዘላለም አትቈጣም፤ ነገር ግን ምሕረት በማድረግ ደስ ይልሃል።
19
ተመልሰህ ትራራልናለህ፤ ኀጢአታችንን በእግርህ ትረግጣለህ፤ በደላችንንም ሁሉ ወደ ጥልቁ ባሕር ትጥላለህ።
20
ከቀድሞ ዘመን ጀምሮ ለአባቶቻችን በመሐላ ቃል እንደ ገባህላቸው፣ ለያዕቆብ ታማኝነትን፣ ለአብርሃምም ምሕረትን ታደርጋለህ።
← Chapter 6