bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
John 14
John 14
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
“ልባችሁ አይጨነቅ፤ በእግዚአብሔር እመኑ ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ።
2
በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ ይህ ባይሆንማ ኖሮ እነግራችሁ ነበር፤ የምሄደውም ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው።
3
ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ።
4
እኔ ወደምሄድበትም ስፍራ የሚያደርሰውን መንገድ ታውቃላችሁ።”
5
ቶማስም፣ “ጌታ ሆይ፤ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም፤ ታዲያ፣ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው።
6
ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።
7
እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር። ከአሁን ጀምሮ ግን ታውቁታላችሁ፤ አይታችሁታልም።”
8
ፊልጶስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው።
9
ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንተ ፊልጶስ! ይህን ያህል ጊዜ ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቷል፤ እንዴትስ፣ ‘አብን አሳየን’ ትላለህ?
10
እኔ በአብ እንዳለሁ፣ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? የምነግራችሁ ቃል ከራሴ አይደለም፤ ነገር ግን ሥራውን የሚሠራው በእኔ የሚኖረው አብ ነው።
11
እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ስነግራችሁ እመኑኝ፤ ሌላው ቢቀር ስለ ድንቅ ሥራዎቹ እንኳ እመኑ።
12
እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ፣ ከእነዚህም የሚበልጥ ያደርጋል።
13
አብ በወልድ እንዲከብር፣ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፤
14
ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትለምኑኝ፣ እኔ አደርገዋለሁ።
15
“ብትወድዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ።
16
እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤
17
እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም። እናንተ ግን፣ አብሯችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስለሚሆን ታውቁታላችሁ።
18
ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ።
19
ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ዓለም ከቶ አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ። እኔ ሕያው ስለሆንሁ እናንተም ሕያዋን ትሆናላችሁ።
20
እኔ በአባቴ እንዳለሁ፣ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ፣ እኔም ደግሞ በእናንተ እንዳለሁ በዚያ ቀን ትረዳላችሁ።
21
የሚወድደኝ ትእዛዜን ተቀብሎ የሚጠብቅ ነው፤ የሚወድደኝንም አባቴ ይወድደዋል፤ እኔም እወድደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።”
22
ከዚያም የአስቆሮቱ ያልሆነው ይሁዳ፣ “ጌታ ሆይ፤ ታዲያ፣ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ የምትገልጠው እንዴት ነው?” አለው።
23
ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “የሚወድደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወድደዋል፤ ወደ እርሱ እንመጣለን፤ ከእርሱም ጋር እንኖራለን።
24
የማይወድደኝ ቃሌን አይጠብቅም። ይህ የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም።
25
“አሁን ከእናንተ ጋር እያለሁ ይህን ሁሉ ነግሬአችኋለሁ፤
26
አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል።
27
ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም። ልባችሁ አይጨነቅ፤ አይፍራም።
28
“ ‘እሄዳለሁ፤ ተመልሼም ወደ እናንተ እመጣለሁ’ ማለቴን ሰምታችኋል፤ ብትወድዱኝስ አብ ከእኔ ስለሚበልጥ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤
29
የተናገርሁት ሲፈጸም እንድታምኑ፣ ከመሆኑ በፊት አሁን ነግሬአችኋለሁ።
30
የዚህ ዓለም ገዥ ስለሚመጣ ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም። እርሱም በእኔ ላይ ሥልጣን የለውም፤
31
ነገር ግን እኔ አብን እንደምወድድ፣ አባቴ ያዘዘኝንም እንደማደርግ ዓለም እንዲያውቅ ነው። “ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ።
← Chapter 13
Chapter 15 →