bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
John 13
John 13
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ጊዜው ልክ ከፋሲካ በዓል በፊት ነበረ፤ ኢየሱስም ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት ጊዜ እንደ ደረሰ ዐወቀ። በዓለም የነበሩትን፣ የራሱ የሆኑትን ወደዳቸው፤ በፍጹም ፍቅሩም ወደዳቸው።
2
እራትም ቀርቦ ሳለ፣ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ዲያብሎስ የስምዖንን ልጅ የአስቆሮቱን ይሁዳ ልብ አነሣሥቶ ነበር።
3
ኢየሱስም፣ አብ ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር እንዳደረገለት፣ ከእግዚአብሔር እንደ ተላከና ወደ እግዚአብሔርም እንደሚመለስ ዐውቆ፣
4
ከእራት ተነሣ፤ መጐናጸፊያውን አስቀመጠ፤ ወገቡንም በፎጣ ታጠቀ።
5
ከዚያም በመታጠቢያው ውሃ ጨምሮ የደቀ መዛሙርቱን እግር እያጠበ በታጠቀው ፎጣ ያብስ ጀመር።
6
ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ እግሬን ታጥባለህን?” አለው።
7
ኢየሱስም መልሶ፣ “የማደርገውን አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው።
8
ጴጥሮስም፣ “የለም፤ እግሬን ከቶ አታጥብም” አለው። ኢየሱስም፣ “ካላጠብሁህማ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም” አለው።
9
ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ እንግዲያውስ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንም ራሴንም ዕጠበኝ” አለው።
10
ኢየሱስም፣ “ገላውን የታጠበ ሰው የሚያስፈልገው እግሩን ብቻ መታጠብ ነው፤ የቀረው አካሉ ግን ንጹሕ ነው። ሁላችሁም ባትሆኑ፣ እናንተ ንጹሓን ናችሁ” አለው።
11
“ሁላችሁም ንጹሓን አይደላችሁም” ያለው አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደ ሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው።
12
እግራቸውን ዐጥቦ ካበቃ በኋላም፣ ልብሱን ለብሶ ተመልሶ በቦታው ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፤ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን?
13
እናንተ፣ ‘መምህርና፣ ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ ትክክል ነው፤ እንደምትሉኝ እንዲሁ ነኝና።
14
እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተም እንደዚሁ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል።
15
እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ ምሳሌ ትቼላችኋለሁ።
16
እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው፣ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም።
17
እንግዲህ እነዚህን ነገሮች ዐውቃችሁ ብትፈጽሙ ትባረካላችሁ።
18
“ስለ ሁላችሁ መናገሬ አይደለም፤ የመረጥኋቸውን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን፣ ‘እንጀራዬን አብሮኝ የቈረሰ ተረከዙን አነሣብኝ’ የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው።
19
“ሲፈጸም እኔ እንደ ሆንሁ ታምኑ ዘንድ፣ ይህ ከመሆኑ በፊት አሁን ነገርኋችሁ።
20
እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የላክሁትን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔን የተቀበለም የላከኝን ይቀበላል።”
21
ይህን ካለ በኋላም ኢየሱስ በመንፈሱ ታውኮ፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” ሲል በግልጽ ተናገረ።
22
ደቀ መዛሙርቱም ማንን ማለቱ እንደ ሆነ ግራ ተጋብተው እርስ በርሳቸው ተያዩ።
23
ከእነርሱ አንዱ፣ ኢየሱስ ይወድደው የነበረ ደቀ መዝሙር ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ ተቀምጦ ነበር።
24
ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ደቀ መዝሙር በምልክት ጠቅሶ “ማንን ማለቱ እንደ ሆነ ጠይቀው” አለው።
25
እርሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ደገፍ ብሎ፣ “ጌታ ሆይ፤ ማን ይሆን?” ብሎ ጠየቀው።
26
ኢየሱስም፣ “ይህን ቍራሽ እንጀራ ከወጭቱ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” አለው፤ ከዚያም ቍራሹን እንጀራ አጥቅሶ ለስምዖን ልጅ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ሰጠው።
27
ይሁዳም ቍራሹን እንጀራ እንደ ተቀበለ ወዲያው ሰይጣን ገባበት። ኢየሱስም፣ “የምታደርገውን ቶሎ አድርግ” አለው፤
28
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለምን እንዲህ እንዳለው ማንም አላወቀም ነበረ።
29
ይሁዳ ገንዘብ ያዥ ስለ ነበር፣ አንዳንዶቹ ለበዓሉ የሚያስፈልግ ነገር እንዲገዛ ወይም ለድኾች እንዲሰጥ ኢየሱስ የተናገረው መሰላቸው።
30
ይሁዳም ያን ቍራሽ እንጀራ እንደ ተቀበለ ወጥቶ ሄደ፤ ሌሊትም ነበረ።
31
ይሁዳ ከወጣ በኋላ፣ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ፤ በእርሱም እግዚአብሔር ከበረ።
32
እንግዲህ እግዚአብሔር በእርሱ ከከበረ ፣ እግዚአብሔር ልጁን በራሱ ዘንድ ያከብረዋል፤ ወዲያውም ያከብረዋል።
33
“ልጆቼ ሆይ፤ ከእናንተ ጋር የምቈየው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድ፣ ‘እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ እንዳልኋቸው፣ አሁንም ለእናንተ ይህንኑ እላችኋለሁ።
34
“አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።
35
እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”
36
ስምዖን ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ የምትሄደው ወዴት ነው?” አለው። ኢየሱስም፣ “ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፤ ኋላ ግን ትከተለኛለህ” ሲል መለሰለት።
37
ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አሁን ልከተልህ የማልችለው ለምንድን ነው? ስለ አንተ ሕይወቴንም ቢሆን አሳልፌ እሰጣለሁ” አለው።
38
ኢየሱስም፣ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሕይወትህን በርግጥ ለእኔ አሳልፈህ ትሰጣለህን? እውነት እልሃለሁ፤ ዶሮ ሳይጮኸ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ።
← Chapter 12
Chapter 14 →