bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Job 12
Job 12
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፤
2
“በርግጥ ሰው ማለት እናንተ ናችኋ! ጥበብም ከእናንተ ጋር ትሞታለቻ!
3
ነገር ግን እኔም እንደ እናንተ አእምሮ አለኝ፤ ከእናንተ አላንስም፤ እንዲህ ያለውን ነገር የማያውቅ ማን ነው?
4
እግዚአብሔርን ጠርቼ የመለሰልኝ ሰው ብሆንም፣ ለባልንጀሮቼ መሣቂያ ሆኛለሁ፤ ጻድቅና ያለ ነቀፋ ሆኜ እያለሁ፣ መሣቂያ ሆኛለሁ።
5
የደላቸው በመከራ ያፌዛሉ፤ እግሩ የተንሸራተተውንም ይገፈትራሉ።
6
የቀማኞች ድንኳን አይታወክም፤ አምላካቸውን በእጃቸው ይዘው እየዞሩም፣ እግዚአብሔርንም እያስቈጡ በሰላም ይኖራሉ።
7
“እስቲ እንስሶችን ጠይቁ፤ ያስተምሯችኋል፤ የሰማይ ወፎችንም ጠይቁ፣ ይነግሯችኋል፤
8
ለምድር ተናገሩ፤ ታስተምራችኋለች፤ የባሕርም ዓሣ ይነግራችኋል።
9
የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ፣ ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው?
10
የፍጥረት ሁሉ ሕይወት፣ የሰውም ሁሉ መንፈስ በእጁ ናትና፤
11
ምላስ የምግብን ጣዕም እንደሚለይ፣ ጆሮ ቃላትን አይለይምን?
12
ጥበብ ያለው በአረጋውያን ዘንድ አይደለምን? ማስተዋልስ ረዥም ዕድሜ ባላቸው ዘንድ አይገኝምን?
13
“ጥበብና ኀይል የእግዚአብሔር ናቸው፤ ምክርና ማስተዋልም በእርሱ ዘንድ ይገኛሉ።
14
እርሱ ያፈረሰውን መልሶ የሚገነባ የለም፣ እርሱ ያሰረውን የሚፈታ አይገኝም።
15
እርሱ ውሃን ቢከለክል፣ ድርቅ ይሆናል፤ ቢለቅቀውም ውሃው ምድሪቱን ያጥለቀልቃል።
16
ብርታትና ድል ማድረግ በእርሱ ዘንድ ይገኛል፤ አታላዩም ተታላዩም በእርሱ እጅ ናቸው።
17
አማካሪዎችን ከጥበባቸው ያራቍታል፤ ፈራጆችንም ማስተዋል ይነሣል።
18
ነገሥታትን ድግ ያስፈታል፤ ገመድም በወገባቸው ያስራል።
19
ካህናትን ከክህነታቸው ያዋርዳል፤ ለዘመናት የተደላደሉትንም ይገለብጣል።
20
ዕውቅ መካሪዎችን ቋንቋ ያሳጣል፤ የሽማግሌዎችንም ማስተዋል ይወስዳል።
21
የተከበሩትን ውርደት ያከናንባል፤ ብርቱዎችንም ትጥቅ ያስፈታል።
22
የጨለማን ጥልቅ ነገሮች ይገልጣል፤ የሞትንም ጥላ ወደ ብርሃን ያወጣል።
23
ሕዝቦችን ታላቅ ያደርጋል፤ መልሶም ያጠፋቸዋል፤ ሕዝቦችን ያበዛል፤ ያፈልሳቸዋልም።
24
የዓለም መሪዎችን ማስተዋል ይነሣል፣ መንገድ በሌለበት በረሓም ያቅበዘብዛቸዋል፤
25
ብርሃን በሌለበት ጨለማ በዳበሳ ይሄዳሉ፤ እንደ ሰካራምም ይንገዳገዳሉ።
← Chapter 11
Chapter 13 →