bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Hosea 13
Hosea 13
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ኤፍሬም ሲናገር ሰዎች ተንቀጠቀጡ፤ በእስራኤልም የተከበረ ነበር፤ ነገር ግን በኣልን ስላመለከ በደለ፤ ሞተም።
2
አሁንም ኀጢአትን መሥራት አበዙ፤ ብራቸውን አቅልጠው ለራሳቸው ጣዖት ሠሩ፣ በጥበብ የተሠሩ ምስሎችን አበጁ፤ ሁሉም የባለ እጅ ሥራ ናቸው። ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ተብሏል፤ “ሰውን መሥዋዕት አድርገው ያቀርባሉ፤ የጥጃ ጣዖቶችንም ይስማሉ”
3
ስለዚህ እንደ ማለዳ ጉም፣ ፈጥኖ እንደሚጠፋ የጧት ጤዛ፣ ከዐውድማ እንደሚጠረግ እብቅ፣ በመስኮትም እንደሚወጣ ጢስ ይሆናሉ።
4
“እኔ ግን ከግብፅ ምድር ያወጣሁህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም፤ ከእኔም በቀር ሌላ አዳኝ የለም።
5
በምድረ በዳ፣ በሐሩር ምድርም ተንከባከብሁህ።
6
ካበላኋቸው በኋላ ጠገቡ፤ በጠገቡ ጊዜ ታበዩ፤ ከዚያም ረሱኝ።
7
ስለዚህ እንደ አንበሳ እመጣባቸዋለሁ፤ እንደ ነብርም በመንገድ አደባባቸዋለሁ።
8
ግልገሎቿን እንደ ተነጠቀች ድብ፣ እመታቸዋለሁ፤ እዘነጣጥላቸዋለሁ። እንደ አንበሳም ሰልቅጬ እውጣቸዋለሁ፤ የዱር አራዊትም ይገነጣጥላቸዋል።
9
“እስራኤል ሆይ፤ በእኔ ላይ ስለ ተነሣህ፣ ረዳትህንም ስለ ተቃወምህ ትጠፋለህ።
10
‘ንጉሥንና አለቆችን ስጠኝ፤’ ብለህ እንደ ጠየቅኸው፣ ያድንህ ዘንድ ንጉሥህ የት አለ? በከተሞችህ ሁሉ የነበሩ ገዦችህስ የት አሉ?
11
በቍጣዬ ንጉሥን ሰጠሁህ፤ በመዓቴም ሻርሁት።
12
የኤፍሬም በደል ተከማችቷል፤ ኀጢአቱም በመዝገብ ተይዟል።
13
በምጥ ላይ እንዳለች ሴት ጭንቅ ይመጣበታል፤ እርሱ ግን ጥበብ የሌለው ልጅ ነው፤ የሚወለድበት ጊዜ ሲደርስ፣ ከእናቱ ማሕፀን መውጣት የማይፈልግ ሕፃን ነው።
14
“ከመቃብር ኀይል እታደጋቸዋለሁ፤ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፤ መቅሠፍትህ የት አለ? መቃብር ሆይ፤ ማጥፋትህ የት አለ? “ከእንግዲህ ወዲህ አልራራለትም፤
15
በወንድሞቹ መካከል ቢበለጽግም እንኳ፣ የምሥራቅ ነፋስ ከምድረ በዳ እየነፈሰ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይመጣል፤ ምንጩ ይነጥፋል፤ የውሃ ጕድጓዱም ይደርቃል። የከበረው ሀብቱ ሁሉ፣ ከግምጃ ቤቱ ይበዘበዛል።
16
የሰማርያ ሰዎች በደላቸውን ይሸከማሉ፤ በአምላካቸው ላይ ዐምፀዋልና፤ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ሕፃኖቻቸውም በምድር ላይ ይፈጠፈጣሉ፤ የእርጉዝ ሴቶቻቸውም ሆድ ይቀደዳል።”
← Chapter 12
Chapter 14 →