bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Exodus 8
Exodus 8
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “ወደ ፈርዖን ዘንድ ሄደህ፣ እንዲህ በለው፤ ‘ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ “እኔን ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።
2
እነርሱን ለመልቀቅ እንቢ ብትል አገርህን ሁሉ በጓጕንቸር መቅሠፍት እመታዋለሁ።
3
አባይ በጓጕንቸሮች ይሞላል፤ ወጥተውም ወደ ቤተ መንግሥትህና ወደ መኝታ ክፍልህ፣ ወደ ዐልጋህም ወደ ሹማምቶችህና ወደ ሕዝብህ ቤቶች፣ ወደ ምድጆችህና ወደ ቡሃቃዎችህ ይገባሉ።
4
ጓጕንቸሮቹ ወደ አንተና ወደ ሕዝብህ ወደ ሹማምትህም ሁሉ ይመጡባችኋል።” ’ ”
5
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፣ “አሮንን፣ ‘በትርህን ይዘህ በምንጮች፣ በቦዮችና በኵሬዎች ላይ እጅህን ዘርጋ፤ ጓጕንቸሮችም በግብፅ ምድር ላይ እንዲወጡ አድርግ’ ” በለው።
6
አሮንም በግብፅ ውሆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጕንቸሮችም ወጥተው ምድሪቱን ሸፈኑ።
7
ሆኖም ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር ሠሩ፤ እነርሱም በግብፅ ምድር ላይ ጓጕንቸሮች እንዲወጡ አደረጉ።
8
ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ ጓጕንቸሮቹን ከእኔና ከሕዝቤ ያርቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸልዩልኝ፤ ከዚያም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕትን ትሠዉ ዘንድ ሕዝቡ እንዲሄዱ እፈቅዳለሁ።
9
ሙሴም ፈርዖንን፣ “በአባይ ወንዝ ካሉት በቀር ከአንተና ከቤቶችህ ጓጕንቸሮቹ እንዲወገዱ ለአንተ፣ ለሹማምትህና ለሕዝብህ የምንጸልይበትን ጊዜ እንድትወስን ለአንተ ትቸዋለሁ” አለው።
10
ፈርዖንም፣ “ነገ ይሁን” አለው። ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ አንተ እንዳልኸው ይሆናል።
11
ጓጕንቸሮቹም ከአንተና ከቤቶችህ፣ ከሹማምትህና ከሕዝብህ ተወግደው በአባይ ወንዝ ብቻ ይወሰናሉ።”
12
ሙሴና አሮን ከፈርዖን ዘንድ ከተመለሱ በኋላ፣ በፈርዖን ላይ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስላመጣቸው ጓጕንቸሮች ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ።
13
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴ እንደ ለመነው አደረገ፤ ጓጕንቸሮቹም በየቤቱ ውስጥ፣ በየዐጥር ግቢውና በየሜዳው ሞቱ።
14
በአንድ ላይ ሰብስበው ከመሯቸው፤ ምድሪቱም ከረፋች።
15
ፈርዖን ችግሩ ጋብ ማለቱን ባየ ጊዜ ግን ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው ልቡን በማደንደን ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም።
16
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “አሮንን ‘በትርህን ሰንዝረህ የምድርን ትቢያ ምታ’ በለው፤ ከዚያም በግብፅ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ይሆናል” አለው።
17
እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፣ አሮን በትሩን እንደ ያዘ እጁን ሲዘረጋና የምድሩን ትቢያ ሲመታ፣ በግብፅ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ሆነ። ሰውንም ሆነ እንስሳውን ተናካሽ ትንኝ ወረረው።
18
ነገር ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተናካሽ ትንኞችን ለመፍጠር ሲሞክሩ አልቻሉም። ተናካሽ ትንኞቹም ከሰውና ከእንስሳው ላይ አልወረዱም ነበር።
19
አስማተኞቹም ፈርዖንን፣ “ይህ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ጣት ነው” አሉት፤ ነገር ግን የፈርዖን ልብ ደንድኖ ስለ ነበር፣ ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው አልሰማቸው አለ።
20
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በጧት ተነሥተህ ፈርዖን ወደ ውሃ በሚወርድበት ጊዜ ከፊቱ ቀርበህ እንዲህ በለው፤ ‘ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።
21
ሕዝቤ እንዲሄዱ ባትለቅቃቸው፣ በአንተና በሹማምትህ ላይ፣ በሕዝብህና በቤቶችህ ላይ የዝንብ መንጋ እሰድዳለሁ። ያረፉበት መሬት እንኳ ሳይቀር፣ የግብፃውያን ቤቶች ሁሉ ዝንብ ብቻ ይሆናሉ።
22
“ ‘በዚያች ዕለት ግን ሕዝቤ የሚኖርባትን የጌሤምን ምድር የተለየች አደርጋታለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚህች ምድር እንዳለሁ ታውቅ ዘንድ የዝንብ መንጋ በዚያ አይኖርም።
23
በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል ልዩነት አደርጋለሁ፤ ይህ ታምራዊ ምልክት ነገ ይሆናል ።’ ”
24
እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲሁ አደረገ፤ አስጨናቂ የዝንብ መንጋ በፈርዖን ቤተ መንግሥትና በሹማምቱ ቤቶች ላይ ወረደ፤ መላው የግብፅ ምድር ከዝንቡ የተነሣ ተበላሽቶ ነበር።
25
ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ፣ “ሂዱና በዚሁ ምድር ለአምላካችሁ ሠዉ” አላቸው።
26
ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “ይህ ትክክል አይሆንም፤ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የምናቀርበው መሥዋዕት በግብፃውያን ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ ታዲያ በእነርሱ ዐይን አስጸያፊ የሆነውን መሥዋዕት ብናቀርብ አይወግሩንምን?
27
ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እርሱ እንዳዘዘን መሥዋዕት ለመሠዋት ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ መሄድ አለብን።”
28
ፈርዖንም፣ “ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በምድረ በዳ መሥዋዕት እንድትሠዉ እፈቅድላችኋለሁ፤ ነገር ግን ርቃችሁ እንዳትሄዱ። ለእኔም ጸልዩልኝ” አላቸው።
29
ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ከአንተ እንደ ተለየሁ ወዲያውኑ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) እጸልያለሁ፤ ነገም ዝንቡ ሁሉ ከፈርዖን፣ ከሹማምቱና ከሕዝቡ ይወገዳል። ብቻ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት እንዲሠዉ ባለመፍቀድ ከዚህ ቀደም ፈርዖን አታልሎ እንዳደረገው አሁንም እንዳያደርግ ርግጠኛ ይሁን።”
30
ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ተለይቶ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ።
31
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴ የለመነውን አደረገ። የዝንቡም መንጋ ከፈርዖን፣ ከሹማምቱና ከሕዝቡ ተወገደ፤ አንድም ዝንብ እንኳ አልቀረም።
32
በዚህም ጊዜ እንኳ ፈርዖን ልቡን አደነደነ እንጂ፣ ሕዝቡን አልለቀቀም።
← Chapter 7
Chapter 9 →