bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Exodus 7
Exodus 7
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ልብ በል፤ እኔ አንተን ለፈርዖን እንደ አምላክ (ኤሎሂም) አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህ አሮንም ያንተ ነቢይ ይሆናል።
2
እኔ የማዝህን ሁሉ ትናገራለህ፤ ወንድምህ አሮንም እስራኤላውያንን ከአገሩ እንዲወጡ ይለቅቃቸው ዘንድ ለፈርዖን ይነግረዋል።
3
እኔ ግን የፈርዖንን ልብ አደነድናለሁ፤ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቆችን በግብፅ ላይ በብዛት ባደርግም እንኳ፣ አይሰማችሁም።
4
ከዚያም እጄን በግብፅ ላይ አደርጋለሁ፤ በኀያል ፍርድም ሰራዊቴን፣ ሕዝቤን እስራኤላውያንን አወጣለሁ።
5
እጄን በግብፅ ላይ ስዘረጋና እስራኤላውያንንም ከዚያ ሳወጣ፣ ግብፃውያን እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኔን ያውቃሉ።”
6
ሙሴና አሮን እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ አዘዛቸው አደረጉ።
7
ፈርዖንን ባነጋገሩበት ጊዜ ሙሴ ዕድሜው ሰማንያ ዓመት፣ አሮን ደግሞ ሰማንያ ሦስት ነበር።
8
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፣
9
“ፈርዖን፣ ‘ታምር አሳዩኝ’ ባላችሁ ጊዜ፣ አሮንን እንዲህ በለው፤ ‘በትርህን ውሰድና በፈርዖን ፊት ጣላት፤’ ከዚያም እባብ ትሆናለች።”
10
ስለዚህ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዛቸው አደረጉ። አሮን በትሩን በፈርዖንና በሹማምቱ ፊት ጣላት፤ እባብም ሆነች።
11
ከዚያም ፈርዖን ጠቢባኑንና መተተኞቹን ጠራ፤ የግብፅ አስማተኞችም በድብቅ ጥበባቸው ያንኑ አደረጉ፤
12
እያንዳንዱ የያዛትን በትር ጣለ፤ እባብም ሆነች። ነገር ግን የአሮን በትር የእነርሱን በትሮች ዋጠች።
13
ሆኖም የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተናግሮ እንደ ነበረውም አላዳመጣቸውም።
14
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ሕዝቡን ለመልቀቅ አልፈቀደም።
15
ወደ ውሃው በሚሄድበት ጊዜ ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እንድታገኘውም በአባይ ዳር ተጠባበቅ፤ ወደ እባብ ተለውጣ የነበረችውንም በትር በእጅህ ያዝ።
16
ከዚያም እንዲህ በለው፤ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) “ሕዝቤ በምድረ በዳ ያመልኩኝ ዘንድ እንዲሄዱ ልቀቃቸው” ብዬ እንድነግርህ ላከኝ፤ አንተ ግን እስካሁን ድረስ እሺ አላልህም።
17
እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ “እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እይ በዚህች በእጄ በያዝኋት በትር የአባይን ውሃ እመታለሁ፤ ወደ ደምም ይለወጣል።
18
በአባይ ወንዝ ውስጥ ያለው ዓሣ ይሞታል፤ ወንዙ ይከረፋል፤ ግብፃውያንም ውሃውን መጠጣት አይችሉም።” ’ ”
19
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “አሮንን፣ ‘በትርህን ውሰድና በግብፅ ውሆች ላይ፣ ይኸውም በምንጮች፣ በቦዮች፣ በኵሬዎችና በውሃ ማጠራቀሚያዎች ላይ እጅህን ዘርጋ’ ብለህ ንገረው፤ ወደ ደምም ይለወጣሉ። ከዕንጨትና ከድንጋይ በተሠሩ ውሃ መያዣዎች ውስጥም ሳይቀር በግብፅ ምድር ደም በየቦታው ይሆናል።”
20
ሙሴና አሮን እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ አዘዛቸው አደረጉ። እርሱም በንጉሡና በሹማምንቱ ፊት በትሩን አንሥቶ የአባይን ወንዝ ውሃ መታ፤ ውሃውም በሙሉ ወደ ደም ተለወጠ።
21
በአባይ ያሉት ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ከመከርፋቱ የተነሣ ግብፃውያኑ ውሃውን ሊጠጡት አልቻሉም። በግብፅ ምድር ሁሉ ደም ነበረ።
22
የግብፅ አስማተኞች በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር አደረጉ፤ የፈርዖንም ልብ ደነደነ፤ ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም።
23
ተመልሶ ወደ ቤተ መንግሥቱ ገባ እንጂ ይህን ከቁም ነገር አልቈጠረውም።
24
ግብፃውያን ሁሉ የወንዙን ውሃ መጠጣት ባለመቻላቸው ውሃ ለማግኘት የአባይን ዳር ይዘው ጕድጓድ ቈፈሩ።
25
እግዚአብሔር (ያህዌ) አባይን ከመታ ሰባት ቀን ዐለፈ።
← Chapter 6
Chapter 8 →