bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Deuteronomy 5
Deuteronomy 5
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ሙሴ እስራኤልን ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ እስራኤል ሆይ፤ በዛሬዋ ዕለት በጆሯችሁ የምነግራችሁን ሥርዐትና ሕግ ስሙ፤ አጥኗቸው፤ በጥንቃቄም ጠብቋቸው።
2
አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በኮሬብ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል።
3
እግዚአብሔር ይህን ቃል ኪዳን የገባውም ከአባቶቻችን ጋር ሳይሆን፣ ዛሬ እዚህ በሕይወት ከምንገኘው ከእኛ ከሁላችን ጋር ነው።
4
እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ፊት ለፊት አነጋገራችሁ።
5
እናንተ ግን እሳቱን በመፍራት ወደ ተራራው ስላልወጣችሁ፣ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቃል ለእናንተ እነግራችሁ ዘንድ እኔ በእግዚአብሔርና (ያህዌ) በእናንተ መካከል ቆምሁ፤ እርሱም እንዲህ አለ፤
6
“ከባርነት ምድር፣ ከግብፅ ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እኔ ነኝ።
7
“ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ።
8
በላይ በሰማይ፣ በታች በምድር ላይ ባለው ወይም ከምድር በታች ውሃ ውስጥ በሚኖር በማንኛውም ዐይነት ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ፤
9
እኔ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፣ የሚጠሉኝን ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ ልጆቻቸውን የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። ለእነርሱ አትስገድላቸው ወይም አታምልካቸው።
10
ለሚወድዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ ግን እስከ ሺሕ ትውልድ ቸርነትንና ፍቅርን እገልጣለሁ።
11
እግዚአብሔር (ያህዌ) ስሙን በከንቱ የሚያነሣውን ሳይቀጣው አይቀርምና፣ የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ስም በከንቱ አታንሣ።
12
አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባዘዘህ መሠረት የሰንበትን ቀን ቀድሰህ አክብረው።
13
ስድስት ቀን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አከናውን።
14
ሰባተኛው ቀን ግን የአምላክህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሰንበት ነው። በዚህም ቀን አንተም ሆንህ ወንድ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ አገልጋይህም ሆነ ሴት አገልጋይህ በሬህ፣ አህያህ ወይም ማናቸውም እንስሳህ ወይም ደግሞ በደጅህ ያለ እንግዳ ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩ። ይህም አንተ እንዳረፍህ ሁሉ ወንድ አገልጋይህም ሆነ ሴት አገልጋይህ እንዲያርፉ ነው።
15
በግብፅ ሳለህ አንተም ባሪያ እንደ ነበርህ፣ ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ እንዳወጣህ አስታውስ፤ ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሰንበትን ቀን ታከብረው ዘንድ አዘዘህ።
16
አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝምና መልካም እንዲሆንልህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባዘዘህ መሠረት አባትህንና እናትህን አክብር።
17
አትግደል።
18
አታመንዝር።
19
አትስረቅ።
20
በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።
21
የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ። በባልንጀራህ ቤትም ሆነ በመሬቱ፣ በወንድ ሆነ በሴት አገልጋዩ፣ በበሬውም ሆነ በአህያው ወይም የእርሱ በሆነው ነገር ላይ ዐይንህን አትጣል።”
22
እግዚአብሔር (ያህዌ) በተራራው ላይ በእሳቱ፣ በደመናውና በድቅድቁ ጨለማ ውስጥ ለማኅበራችሁ ሁሉ በከፍተኛ ድምፅ የተናገራችሁ ትእዛዞቹ እነዚህ ናቸው፤ የጨመረውም ሌላ የለም፤ ትእዛዞቹንም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፎ ሰጠኝ።
23
ተራራው በእሳት ሲቃጠል፣ ከጨለማው ውስጥ ድምፁን በሰማችሁ ጊዜ፣ እናንተ የየነገዶቻችሁ አለቆችና ሽማግሌዎቻችሁም በሙሉ ወደ እኔ ዘንድ መጣችሁ፤
24
እንዲህም አላችሁ፤ “አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ክብሩንና ግርማውን አሳይቶናል፤ ከእሳቱም ውስጥ ድምፁን ሰምተናል። እግዚአብሔር አነጋግሮትም እንኳ፣ ሰው በሕይወት ሊኖር እንደሚችል በዛሬው ቀን አይተናል።
25
ከእንግዲህ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ድምፅ ብንሰማ እንሞታለን፤ ይህችም ታላቅ እሳት ፈጽማ ታጠፋናለች፤ ታዲያ ለምን እንሙት?
26
ለመሆኑ ከእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር እኛ እንደ ሰማነው ሁሉ፣ የሕያው እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ድምፅ ሰምቶ በሕይወት ለመኖር የቻለ ከሥጋ ለባሽ ማን አለ?
27
አንተ ቅረብ፤ አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚለውን ሁሉ አድምጥ፤ ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚነግርህን ሁሉ ንገረን፤ እኛም እንሰማለን፤ እናደርገዋለንም።”
28
ይህን ስትነግሩኝ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰማ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) አለኝ፤ “ይህ ሕዝብ ምን እንዳለህ ሰምቻለሁ፤ ያሉትም ሁሉ መልካም ነው።
29
ታዲያ ለእነርሱም ሆነ ለልጆቻቸው ለዘላለም መልካም እንዲሆንላቸው፣ እኔን እንዲፈሩና ሁልጊዜ ትእዛዞቼን ሁሉ እንዲጠብቁ እንደዚህ ያለ ልብ ቢኖራቸው ምናለ!
30
“ሄደህ ወደየድንኳናቸው እንዲመለሱ ንገራቸው።
31
አንተ ግን እንዲወርሷት በምሰጣቸው ምድር እንዲጠብቋቸው የምታስተምራቸውን ትእዛዞች፣ ሥርዐቶችና ሕጎች ሁሉ እንድሰጥህ እዚሁ ከእኔ ዘንድ ቈይ።
32
“እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ያዘዛችሁን ለመፈጸም ተጠንቀቁ፤ ቀኝም ግራም አትበሉ።
33
በምትወርሷት ምድር በሕይወት ለመኖር እንድትችሉ፣ መልካም እንዲሆንላችሁና ዕድሜያችሁም እንዲረዝም፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባዘዛችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ።”
← Chapter 4
Chapter 6 →