bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
2 Samuel 24
2 Samuel 24
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እንደገናም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ዳዊትንም በእነርሱ ላይ በማስነሣት፣ “ሂድ እስራኤልንና ይሁዳን ቍጠር” አለው።
2
ስለዚህም ንጉሡ ኢዮአብንና አብረውት ያሉትን የጦር አዛዦች ፣ “ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ወዳሉት የእስራኤል ነገዶች ሁሉ ሂዱ፤ ብዛታቸው ምን ያህል እንደ ሆነ ለማወቅ እንድችልም ተዋጊዎቹን መዝግቡ” አላቸው።
3
ኢዮአብ ግን ንጉሡን፣ “አምላክህ እግዚአብሔር ሰራዊቱን መቶ ዕጥፍ ያድርገው፤ የጌታዬ የንጉሡ ዐይን ይህን ለማየት ይብቃ፤ ንጉሡ ጌታዬ ግን ይህን ለማድረግ የፈለገው ለምንድን ነው?” ሲል መለሰለት።
4
ሆኖም የንጉሡ ቃል ኢዮአብንና የሰራዊቱን አዛዦች ስላሸነፋቸው፣ የእስራኤልን ሰራዊት ለመመዝገብ ከፊቱ ወጥተው ሄዱ።
5
ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ፣ በሸለቆው ውስጥ ካለችው ከተማ በስተ ደቡብ በምትገኘው በአሮዔር አጠገብ ሰፈሩ፤ ከዚያም በጋድ በኩል አድርገው ወደ ኢያዜር ሄዱ፤
6
እንዲሁም ወደ ገለዓድና ወደ ተባሶን አዳሰይ፣ ቀጥሎም ወደ ዳንየዓን ከዚያም ዞረው ወደ ሲዶና ሄዱ።
7
ደግሞም ወደ ጢሮስ ምሽግ፣ ወደ ኤዊያውያንና ወደ ከነዓናውያን ከተሞች፣ በመጨረሻም በይሁዳ ደቡብ ወዳለችው ወደ ቤርሳቤህ ሄዱ።
8
ምድሪቱን ሁሉ ዞረው ከዘጠኝ ወር ከሃያ ቀን በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
9
ኢዮአብም የተዋጊዎቹን ጠቅላላ ቍጥር ለንጉሡ አሳወቀ፤ በእስራኤል ስምንት መቶ ሺሕ፣ በይሁዳ አምስት መቶ ሺሕ ሰይፍ መምዘዝ የሚችሉ ብቃት ያላቸው ሰዎች ተገኙ።
10
ዳዊት ተዋጊዎቹን ከቈጠረ በኋላ ኅሊናው ስለ ወቀሠው፣ “ባደረግሁት ነገር ታላቅ ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ አሁንም እግዚአብሔር ሆይ፤ የአገልጋይህን በደል እንድታርቅ እለምንሃለሁ፤ የፈጸምሁት ታላቅ የስንፍና ሥራ ነውና” አለ።
11
በማግስቱም ጧት ዳዊት ከመነሣቱ በፊት የእግዚአብሔር ቃል የዳዊት ባለ ራእይ ወደ ሆነው ወደ ነቢዩ ወደ ጋድ መጣ፤
12
እንዲህም አለው፤ “ሂድና ዳዊትን፣ ‘ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሦስት ነገሮችን ለምርጫ አቅርቤልሃለሁ፤ በአንተ ላይ አደርግብህ ዘንድ አንዱን ምረጥ’ በለው።”
13
ስለዚህም ጋድ ወደ ዳዊት ሄዶ፣ “በምድርህ የሦስት ዓመት ራብ ይምጣብህ? ወይስ ጠላቶችህ እያሳደዱህ ሦስት ወር ትሸሽ? ወይስ ደግሞ በምድርህ ላይ የሦስት ቀን ቸነፈር ይምጣ? እንግዲህ አሁን ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ ዐስበህበት ወስን” አለው።
14
ዳዊትም ጋድን፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ታላቅ ስለሆነ በእግዚአብሔር እጅ እንውደቅ፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ” አለው።
15
ስለዚህም እግዚአብሔር ከዚያች ዕለት ጧት አንሥቶ እስከ ተወሰነው ቀን ድረስ በእስራኤል ላይ ቸነፈር ላከ፤ በዚህም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሰባ ሺሕ ሰው ዐለቀ።
16
የእግዚአብሔር መልአክ ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት እጁን በዘረጋ ጊዜ፣ የደረሰው ጕዳት እግዚአብሔርን ስላሳዘነው፣ ሕዝቡን የሚቀሥፈውን መልአክ “በቃ! እጅህን መልስ” አለው። በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር።
17
ዳዊት ሕዝቡን የሚቀሥፈውን መልአክ ባየ ጊዜ እግዚአብሔርን ፣ “እነሆ ኀጢአት የሠራሁም የተሳሳትሁም እኔ ነኝ፤ እነዚህ ግን በጎች ናቸው፤ ምን አጠፉ? እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን” አለ።
18
በዚያን ቀን ጋድ ወደ ዳዊት ዘንድ ሄዶ፣ “ውጣና በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሥራ” አለው።
19
ስለዚህ ዳዊት፣ እግዚአብሔር በጋድ በኩል ባዘዘው መሠረት ወጣ።
20
ኦርናም ቍልቍል ሲመለከት፣ ንጉሡና ሰዎቹ ወደ እርሱ ሲመጡ አየ፤ ከዚያም ወጥቶ ወደ መሬት ለጥ ብሎ ለንጉሡ እጅ ነሣ።
21
ኦርናም፣ “ንጉሥ ጌታዬ ወደ አገልጋዩ የመጣው ለምንድን ነው?” አለ። ዳዊትም መልሶ፣ “መቅሠፍቱ ከሕዝቡ እንዲከለከል ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንድሠራ ዐውድማህን ልገዛ ነው” አለው።
22
ኦርናም ዳዊትን እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ጌታዬ ደስ ያለውን ወስዶ መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሬዎች አሉ፤ ለሚነድደውም ዕንጨት፣ የመውቂያው ዕቃና የበሬ ቀንበር አለ።
23
ንጉሥ ሆይ፣ ይህን ሁሉ ኦርና ለንጉሡ ይሰጣል።” እንዲሁም ኦርና፣ “ እግዚአብሔር አምላክህ ይቀበልህ” አለው።
24
ንጉሡ ግን ኦርናን፣ “እንዲህማ አይሆንም፤ ዋጋውን ላንተ መክፈል አለብኝ፤ ለአምላኬም ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ያለ ዋጋ አላቀርብም” አለው። ስለዚህም ዳዊት ዐውድማውንና በሬዎቹን በአምሳ ሰቅል ብር ገዛ፤
25
በዚያም ዳዊት ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረበ። ከዚያም እግዚአብሔር ስለ ምድሪቱ የቀረበውን ጸሎት ሰማ፤ በእስራኤል ላይ የመጣውም ቸነፈር ቆመ።
← Chapter 23