bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
2 Samuel 16
2 Samuel 16
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ዳዊት ከተራራው ጫፍ ባሻገር ጥቂት ዕልፍ ብሎ እንደ ሄደ፣ ሲባ የተባለው የሜምፊቦስቴ አገልጋይ፣ ሁለት መቶ እንጀራ፣ አንድ መቶ ጥፍጥፍ ዘቢብ፣ አንድ መቶ ጥፍጥፍ በለስና አንድ አቍማዳ የወይን ጠጅ የተጫኑ ሁለት አህዮች እየነዳ ሊገናኘው መጣ።
2
ንጉሡም ሲባን፣ “ይህን ሁሉ ያመጣኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ሲባም “አህዮቹን የንጉሡ ቤተ ሰዎች እንዲቀመጡባቸው፣ እንጀራውንና በለሱን ወጣቶቹ እንዲበሉት፣ የወይን ጠጁን ደግሞ በምድረ በዳ የደከሙት እንዲጠጡት ነው” አለው።
3
ከዚያም ንጉሡ፣ “የጌታህ ልጅ የት ነው?” ሲል ጠየቀው። ሲባም፣ “ ‘የእስራኤል ቤት ዛሬ የአባቴን መንግሥት ይመልስልኛል’ ብሎ ስለሚያስብ፣ በኢየሩሳሌም ተቀምጧል” አለው።
4
ከዚያም ንጉሡ ሲባን፣ “የሜምፊቦስቴ የነበረው ሁሉ ከእንግዲህ ያንተ ነው” አለው። ሲባም፣ “በታላቅ ትሕትና በግንባሬ ተደፍቼ እጅ እነሣለሁ፤ ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ ላግኝ” አለው።
5
ንጉሥ ዳዊት ወደ ብራቂም ሲደርስ፣ ከሳኦል ቤተ ሰብ ነገድ የሆነ አንድ ሰው ብቅ አለ፤ እርሱም የጌራ ልጅ ሳሚ ነው፤ እየተራገመም ወጣ።
6
የንጉሡ ወታደሮችና የክብር ዘቦቹ ሁሉ በዳዊት ግራና ቀኝ ቢኖሩም እንኳ፣ በዳዊትና በሹማምቱ ላይ ሁሉ ድንጋይ ይወረውርባቸው ነበር።
7
ሳሚም እንዲህ ብሎ ይራገም ነበር፤ “ውጣ! ከዚህ ውጣ! አንተ የደም ሰው፤ አንተ ክፉ ሰው፤
8
መንግሥቱን የወሰድህበትን የሳኦልን ቤተ ሰው ደም ሁሉ እግዚአብሔር ወደ አንተው እየመለሰው ነው። እግዚአብሔር መንግሥትህን ለልጅህ ለአቤሴሎም አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አንተ የደም ሰው ስለ ሆንህ እነሆ፣ መከራ መጥቶብሃል።”
9
ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ ንጉሡን፣ “ይህ የሞተ ውሻ፣ ንጉሥ ጌታዬን እንዴት ይራገማል? ልሻገርና ራሱን ልቍረጠው” አለ።
10
ንጉሡ ግን፣ “እናንት የጽሩያ ልጆች እናንተንና እኔን የሚያገናኘን ምን ነገር አለ? እግዚአብሔር ፣ ‘ዳዊትን ርገመው’ ብሎት የሚረግመኝ ከሆነ፣ ‘ይህን ለምን አደረግህ’ ብሎ ማን ሊጠይቀው ይችላል?” አለው።
11
ከዚያም ዳዊት አቢሳንና ሹማምቱን ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “ከአብራኬ የወጣው ልጄ ሕይወቴን ሊያጠፋት ከፈለገ፣ ይህ ብንያማዊ ቢያደርገው ምን ያስደንቃል? ስለዚህ ተዉት፤ እግዚአብሔር በል ብሎት ነውና ይራገም፤
12
ምናልባትም እግዚአብሔር ሐዘኔን አይቶ በዛሬውም ርግማን ፈንታ በጎ ነገር ያደርግልኝ ይሆናል።”
13
ስለዚህም ዳዊትና ሰዎቹ መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ሳሚም በአንጻሩ ባለው ኰረብታ ጥግ ጥግ እየሄደ ይራገም፣ ድንጋይ ይወረውርበትና ዐፈር ይበትንበት ነበር።
14
ንጉሡና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ለመሄድ ወዳሰቡበት ስፍራ ደረሱ፤ በጣም ደክሟቸው ስለ ነበር በዚያ ዐረፉ።
15
በዚህን ጊዜ አቤሴሎምና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ አኪጦፌልም አብሮት ነበር።
16
የዳዊት ወዳጅ አርካዊው ኩሲም ወደ አቤሴሎም መጥቶ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤ ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ” አለው።
17
አቤሴሎምም፣ ኩሲን፣ “ለወዳጅህ ያለህ ታማኝነት እስከዚህ ድረስ ነው? ለምን ከወዳጅህ ጋር አልሄድህም?” ሲል ጠየቀው።
18
ኩሲም፣ አቤሴሎምን እንዲህ አለው፤ “ይህንስ አላዳርገውም! እኔ በእግዚአብሔር ፣ በዚህ ሕዝብና በእስራኤል ሰዎች ሁሉ ለተመረጠው ለእርሱ እሆናለሁ፤ አብሬውም እኖራለሁ፤
19
እንግዲህ ልጁን ካላገለገልሁ ማንን ላገለግል ነው? አባትህን እንዳገለገልሁ ሁሉ፤ አንተንም አገለግላለሁ።”
20
አቤሴሎምም አኪጦፌልን፤ “እስቲ ምክር አምጣ፤ ምን እናድርግ?” አለው።
21
አኪጦፌልም መልሶ፣ “ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ አባትህ ከተዋቸው ቁባቶቹ ጋር ግባና ተኛ፤ ከዚያም አንተ፣ አባትህን እጅግ የጠላህ መሆንህን መላው እስራኤል ይሰማና አብሮህ ያለው ሁሉ ክንዱ ይበረታል” አለው።
22
ስለዚህ ለአቤሴሎም በሰገነቱ ላይ ድንኳን ተከሉለት፤ እዚያም መላው እስራኤል እያየው ከአባቱ ቁባቶች ጋር ተኛ።
23
በዚያም ጊዜ አኪጦፌል የሚሰጠው ምክር ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ መጠየቅ ይቈጠር ነበር፤ ዳዊትም ሆነ አቤሴሎም የአኪጦፌልን ምክር የሚቀበሉት በዚህ ሁኔታ ነበር።
← Chapter 15
Chapter 17 →