bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
2 Samuel 15
2 Samuel 15
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ሠረገላና ፈረሶች እንዲሁም ፊት ፊቱ የሚሮጡ አምሳ ሰዎች ለራሱ አዘጋጀ።
2
አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ሆን ብሎ ይቆም ነበር። ማናቸውም ባለ ጕዳይ አቤቱታውን ለንጉሡ አቅርቦ ለማስወሰን በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ፣ አቤሴሎም ወደ እርሱ እየጠራ፣ “አንተ ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” በማለት ይጠይቀዋል፤ ያም ሰው፣ “አገልጋይህ ከአንዱ የእስራኤል ነገዶች ነው” ብሎ ይመልስለታል።
3
ከዚያም አቤሴሎም፣ “ተመልከት! ጕዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ የትኛው የንጉሥ እንደ ራሴ ነው ታዲያ የሚያይልህ?” ይለዋል።
4
ቀጠል አድርጎም፣ “ምነው ዳኛ ሆኜ በምድሪቱ ላይ በተሾምሁ አቤቱታ ወይም ክስ ያለበት ሁሉ ወደ እኔ እየመጣ ፍትሕ እንዲያገኝ አደርገው ነበር” ይል ነበር።
5
እንዲሁም ማናቸውም ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እጅ በሚነሣው ጊዜ፣ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር።
6
አቤሴሎም ፍትሕ ለማግኘት ወደ ንጉሡ የሚመጣውን እስራኤላዊ ሁሉ የሚቀርበው በዚህ መንገድ ስለ ነበር፣ የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።
7
ከአራት ዓመት በኋላም አቤሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “ ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ ወደ ኬብሮን እንድሄድ ፍቀድልኝ፤
8
እኔ አገልጋይህ በሶርያ ምድር በጌሹር ሳለሁ ‘ እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰኝ እንደ ሆነ፣ በኬብሮን ለእግዚአብሔር እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስያለሁ።”
9
ንጉሡም፣ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ስለዚህ አቤሴሎም ወደ ኬብሮን ሄደ።
10
ከዚያም አቤሴሎም፣ “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ፣ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ’ ” የሚሉ የምስጢር ሠራተኞችን በመላው የእስራኤል ነገዶች አሰማራ።
11
ከኢየሩሳሌምም ሁለት መቶ ሰዎች አብረውት ሄዱ፤ በእንግድነት ተጋብዘው በየዋህነት ከመሄዳቸው በስተቀር፣ ስለ ጕዳዩ የሚያውቁት አንዳችም ነገር አልነበረም።
12
አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ የሆነው ጊሎኣዊው አኪጦፌል ከአገሩ ከጊሎ ወደ እርሱ እንዲመጣ ላከበት፤ ስለዚህ ሤራው ጥንካሬ አገኘ፤ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቍጥር እየጨመረ መጣ።
13
መልእክተኛም መጥቶ፣ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኗል” ብሎ ለዳዊት ነገረው።
14
ከዚያም ዳዊት በኢየሩሳሌም ላሉት ሹማምቱ ሁሉ፣ “ተነሡ እንሽሽ፤ አለዚያ አንዳችንም ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ አሁኑኑ ከዚህ መውጣት አለብን፤ ካልሆነ ገሥግሦ መጥቶ ከያዘን እኛን ያጠፋናል፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ይመታታል” አላቸው።
15
የንጉሡ ሹማምትም፣ “ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ ለማድረግ እኛ አገልጋዮችህ ዝግጁ ነን” ብለው መለሱለት።
16
ንጉሡ ከመላው ቤተ ሰቡ ጋር ወጣ፤ ቤተ መንግሥቱንም እንዲጠብቁ ዐሥር ቁባቶች አስቀረ።
17
ስለዚህ ንጉሡ መላውን ሕዝብ አስከትሎ ወጣ፤ ጥቂት ርቀው ከሄዱ በኋላም በአንዲት ቦታ ቆሙ።
18
ሰዎቹ ሁሉ፣ ከሊታውያን፣ ፈሊታውያን እንዲሁም ከጌት አብረውት የመጡትን ስድስት መቶ ጌታውያንን ሁሉ ጨምሮ ተሰልፈው በንጉሡ ፊት ዐለፉ።
19
ንጉሡም ጌታዊውን ኢታይን እንዲህ አለው፤ “ከእኛ ጋር የመጣኸው ለምንድን ነው? ተመለስና ከንጉሡ ከአቤሴሎም ጋር ተቀመጥ፤ አንተ ለራስህ ከአገርህ ተወስደህ የመጣህ እንግዳ ነህ፤
20
የመጣኸውም ገና ትናንት ነው፤ ታዲያ የት እንደምሄድ የማላውቅ ሰው እንዴት ዛሬ ከእኛ ጋር እንድትንከራተት ላድርግ? በል አሁንም ሰዎችህን ይዘህ ተመለስ፤ በጎነትና ታማኝነትም ከአንተ ጋር ይሁን” አለው።
21
ኢታይን ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፤ ሕይወትም ይሁን ሞት በየትም ቦታ ንጉሥ ጌታዬ የሚሆነውን ሁሉ አገልጋይህም እንደዚያው ይሆናል” ብሎ መለሰለት።
22
ዳዊትም ኢታይን፣ “በል እንግዲያው ቅደምና ሂድ” አለው። ስለዚህ ጌታዊው ኢታይን ሰዎቹን ሁሉና አብረውት የነበሩትን ቤተ ሰቦቹን ይዞ ሄደ።
23
ሕዝቡ ሁሉ በሚያልፍበትም ጊዜ ባላገሩ በሙሉ እየጮኸ አለቀሰ፤ ንጉሡም የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሻግሮ ወደ ምድረ በዳው ተጓዘ።
24
ሳዶቅም በዚያ ነበር፤ አብረውት የነበሩትም ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ነበር። እነርሱም የእግዚአብሔርን ታቦት ዐሳረፉ፤ አብያታርም ሕዝቡ በሙሉ ከከተማዪቱ ለቅቆ እስኪወጣ ድረስ መሥዋዕት አቀረበ ።
25
ከዚያም ንጉሡ ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማዪቱ ይዘህ ተመለስ፤ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ እርሱ እኔንም መልሶ ታቦቱንና ማደሪያውን እንደ ገና ለማየት ያበቃኛል፤
26
ነገር ግን እርሱ፣ ‘ባንተ አልተደሰትሁም’ የሚል ከሆነ፣ መልካም መስሎ የታየውን ነገር ያድርግብኝ፤ እኔም ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።”
27
እንዲሁም ንጉሡ ካህኑን ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ ነቢይ አይደለህምን? እንግዲህ አንተም ልጅህን አኪማአስን፣ የአብያታርን ልጅ ዮናታንን ይዘህ በሰላም ወደ ከተማዪቱ ተመለስ። አንተና አብያታር ሁለቱን ልጆቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ።
28
እኔም ከአንተ ዘንድ ወሬ እስካገኝ ድረስ በምድረ በዳው በሚገኘው በወንዙ መሻገሪያ እቈያለሁ”
29
ስለዚህ ሳዶቅና አብያታር የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም በመመለስ እዚያው ቈዩ።
30
ዳዊት ግን እያለቀሰ የደብረ ዘይትን ተራራ ሽቅብ ወጣ፤ ራሱን ተከናንቦ፣ ባዶ እግሩን ነበር፤ አብሮት ያለውም ሕዝብ ሁሉ እንደዚሁ ራሱን ተከናንቦ እያለቀሰ ሽቅብ ይወጣ ነበር።
31
በዚህ ጊዜ፣ “ከአቤሴሎም ጋር ካሤሩት መካከል አንዱ አኪጦፌል ነው” ብለው ለዳዊት ነገሩት። ስለዚህ ዳዊት፣ “ እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህን የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት ለውጠው” ብሎ ጸለየ።
32
ዳዊትም ሕዝቡ እግዚአብሔርን ወደሚያመልክበት ወደ ተራራው ጫፍ ሲደርስ፣ አርካዊው ኩሲ ልብሱን ቀድዶ ትቢያ በራሱ ላይ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ።
33
ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለው፤ “አብረኸኝ ብትሄድ ሸክም ትሆንብኛለህ፤
34
ነገር ግን ወደ ከተማዪቱ ተመልሰህ አቤሴሎምን፣ ‘ንጉሥ ሆይ፤ አገልጋይህ እሆናለሁ፤ ቀድሞ የአባትህ አገልጋይ እንደ ነበርሁ ሁሉ፣ ዛሬም አንተን አገለግልሃለሁ’ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር በማፍረስ ትረዳኛለህ።
35
ካህናቱ ሳዶቅና አብያታር እዚያው ከአንተው ጋር ይሆኑ የለምን? ከቤተ መንግሥቱ የምትሰማትን ሁሉ ንገራቸው።
36
የሳዶቅ ልጅ አኪማአስና የአብያታር ልጅ ዮናታን፣ ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው እዚያው አብረዋቸው ይገኛሉ። የምትሰማትን ሁሉ በእነርሱ ላክልኝ።”
37
ስለዚህ የዳዊት ወዳጅ ኩሲ ልክ አቤሴሎም ኢየሩሳሌም በገባበት ሰዓት እዚያው ደረሰ።
← Chapter 14
Chapter 16 →