bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
1 Chronicles 18
1 Chronicles 18
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከዚህ በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል መትቶ ተገዥ አደረጋቸው፤ ጌትንና በዙሪያዋም የሚገኙትን መንደሮች ከፍልስጥኤማውያን እጅ ወሰደ።
2
እንዲሁም ዳዊት ሞዓባውያንን ድል አደረጋቸው፤ እነርሱም ገባሮቹ ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት።
3
ከዚህም በላይ ዳዊት በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውን ግዛት ለመቈጣጠር በሄደ ጊዜ፣ የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን እስከ ሐማት ድረስ ዘልቆ ወጋው።
4
ዳዊትም አንድ ሺሕ ሠረገላ፣ ሰባት ሺሕ ፈረሰኛና ሃያ ሺሕ እግረኛ ወታደር ማረከ፤ አንድ መቶ የሠረገላ ፈረሶች ብቻ አስቀርቶ የቀሩትን ቋንጃቸውን ቈረጠ።
5
ሶርያውያንም የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ለመርዳት ከደማስቆ በመጡ ጊዜ፣ ከእነርሱ ሃያ ሁለት ሺሕ ሰው ገደለ።
6
ከዚያም በሶርያ ግዛት ውስጥ ባለችው በደማስቆ የጦር ሰፈር አቋቋመ፤ ሶርያውያንም ገባሮቹ ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት። እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ድል አጐናጸፈው።
7
ዳዊትም የአድርአዛር ጦር አለቆች ያነገቡትን የወርቅ ጋሻ ወሰደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጣው።
8
ዳዊት ከአድርአዛር ከተሞች ከጢብሐትና ከኩን እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ፤ ሰሎሞን የናሱን ባሕር፣ ዐምዶቹንና ልዩ ልዩ የናስ ዕቃዎቹን የሠራው በዚሁ ነበር።
9
የሐማት ንጉሥ ቶዑ፣ ዳዊት የሱባን ንጉሥ የአድርአዛርን ሰራዊት ሁሉ ድል እንደ መታ ሲሰማ፣
10
እጅ እንዲነሣውና ደስታውንም እንዲገልጥለት ልጁን አዶራምን ወደ ንጉሥ ዳዊት ላከው፤ ቶዑ ከአድርአዛር ጋር ብዙ ጊዜ ጦርነት ገጥሞ ነበር። አዶራምም ከወርቅ፣ ከብርና ከናስ የተሠሩ ልዩ ልዩ ዕቃዎች አመጣለት።
11
ንጉሥ ዳዊት ከኤዶም፣ ከሞዓብ፣ ከአሞናውያን፣ ከፍልስጥኤማውያንና ከአማሌቃውያን፣ ከእነዚህ ሁሉ መንግሥታት የማረከውን ወርቅና ብር ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ፣ እነዚህንም ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ቀደሰ።
12
የጽሩያ ልጅ አቢሳ በጨው ሸለቆ ዐሥራ ስምንት ሺሕ ኤዶማውያን ገደለ።
13
እርሱም በኤዶም የጦር ሰፈሮች አቋቋመ፤ ኤዶማውያንም ሁሉ ለንጉሥ ዳዊት ገባሮች ሆኑ። እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ድል አጐናጸፈው።
14
ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ፍትሕንና ጽድቅን አሰፈነላቸው።
15
የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የሰራዊቱ አዛዥ ነበረ፤ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ ደግሞ የቤተ መዛግብቱ ኀላፊ ነበረ።
16
የአኪጦብ ልጅ ሳዶቅና የአቤሜሌክ ልጅ አብያታር ካህናት ነበሩ፤ ሱሳ ደግሞ ጸሓፊ ነበረ።
17
የዮዳሄ ልጅ በናያስ የከሊታውያንና የፈሊታውያን አዛዥ ነበረ፤ የዳዊት ወንዶች ልጆቹ ደግሞ ከንጉሡ ቀጥሎ የበላይ ሹማምት ነበሩ።
← Chapter 17
Chapter 19 →