bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
1 Chronicles 17
1 Chronicles 17
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ዳዊት በቤተ መንግሥቱ ተደላድሎ በተቀመጠበት ጊዜ፣ ነቢዩ ናታንን “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው።
2
ናታንም ለዳዊት፣ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ስለሆነ፣ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” ሲል መለሰለት።
3
በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጥቶ እንዲህ አለው፤
4
“ሂድና ለባሪያዬ ለዳዊት እንዲህ ብለህ ንገረው፤ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘እኔ የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም።
5
እስራኤልን ከግብፅ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ከአንዱ ድንኳን ወደ ሌላው ድንኳን፣ ከአንዱ ማደሪያ ወደ ሌላው ማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ፣ በቤት ውስጥ አልኖርሁም።
6
ከእስራኤላውያን ጋር በሄድሁባቸው ቦታዎች ሁሉ፣ ሕዝቤን እንዲጠብቁ ላዘዝኋቸው መሪዎቻቸው ከቶ፣ “ለምን ከዝግባ ዕንጨት ቤት አልሠራችሁልኝም” ያልሁበት ጊዜ አለን?’
7
“እንግዲህ አሁንም ለባሪያዬ ለዳዊት እንዲህ ብለህ ንገረው፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘የሕዝቤ የእስራኤል ገዥ እንድትሆን በጎችን ከመጠበቅና ከመከተል አንሥቼ ወሰድሁህ።
8
በሄድህበት ሁሉ ከአንተ አልተለየሁም፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ፤ አሁንም ስምህን እንደ ምድር ታላላቅ ሰዎች ስም ገናና አደርገዋለሁ።
9
ለሕዝቤ ለእስራኤል መኖሪያ ስፍራ እሰጠዋለሁ፤ የራሳቸውም መኖሪያ ስፍራ እንዲኖራቸው፣ ከእንግዲህም በኋላ እንዳይናወጡ አደርጋቸዋለሁ። ክፉ ሰዎች በመጀመሪያ እንዳደረጉት ሁሉ፣ ከእንግዲህ አይጨቍኗቸውም፤
10
ከዚህ ቀደም በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪዎች በሾምሁ ጊዜ ጨቋኞቹ ያደረጉትን ዛሬ አያደርጉትም፤ ጠላቶቻችሁን ሁሉ አዋርዳቸዋለሁ። “ ‘ እግዚአብሔር ቤት እንደሚሠራልህ በግልጽ እነግርሃለሁ፤
11
ዘመንህን ጨርሰህ ወደ አባቶችህ በምትሄድበት ጊዜ፣ ከአብራክህ ከተከፈሉት ልጆችህ አንዱ በእግርህ እንዲተካ አደርጋለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለታለሁ፤
12
ቤት የሚሠራልኝም እርሱ ነው፤ እኔም ዙፋኑን ለዘላለም አጸናለሁ።
13
አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ጽኑ ፍቅሬን ከአንተ በፊት ከነበረው ላይ እንደ ወሰድሁ፣ ከእርሱ ላይ ከቶ አልወስድም።
14
በቤቴና በመንግሥቴ ላይ ለዘላለም አኖረዋለሁ፤ ዙፋኑም ለዘላለም ይጸናል።’ ”
15
ናታንም የዚህን ሁሉ ራእይ ቃል ለዳዊት ነገረው።
16
ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦም እንዲህ አለ፤ “ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ለመሆኑ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤተ ሰቤስ ምንድን ነው?
17
አምላክ ሆይ፤ ይህ በፊትህ በቂ እንዳልሆነ ቈጥረህ ስለ ወደ ፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ እኔንም ከሰዎች ሁሉ እጅግ የከበረ ሰው አድርገህ ተመለከትኸኝ።
18
“ባሪያህን ስላከበርኸው፣ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ማለት ይችላል? ባሪያህን እኮ ታውቀዋለህ፤
19
እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ባሪያህ ብለህና እንደ ፈቃድህም መሠረት ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ እነዚህም ታላላቅ ተስፋዎች ሁሉ እንዲታወቁ አደረግህ።
20
“አቤቱ፤ እንደ አንተ ያለ የለም፤ በጆሯችን እንደ ሰማነው ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም።
21
ከግብፅ ተቤዥተህ እንዳወጣኸው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ማን አለ? እነርሱ እግዚአብሔር ለራሱ ሊቤዣቸው ከምድር ሕዝቦች መካከል የመረጣቸው ናቸው፤ በሕዝብህም ፊት ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን በማድረግ መንግሥታትን በፊታቸው አሳደድህ።
22
ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘላለም የራስህ ሕዝብ አደረግኸው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆንህለት።
23
“ እግዚአብሔር ሆይ፤ አሁንም ስለ ባሪያህና ስለ ቤቱ የሰጠኸው ተስፋ ለዘላለም የጸና ይሁን፤ የሰጠኸውንም ተስፋ ፈጽም፤
24
ይህም ስምህ ጸንቶ እንዲኖርና ለዘላለምም ታላቅ እንዲሆን ነው። ከዚያም ሰዎች ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእውነት የእስራኤል አምላክ ነው!’ ይላሉ፤ የባሪያህ የዳዊትም ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል።
25
“አምላኬ ሆይ፤ ቤት እንደምትሠራለት ለባሪያህ ገልጸህለታል፤ ስለዚህ ባሪያህ ወደ አንተ ለመጸለይ ድፍረት አገኘ።
26
እግዚአብሔር ሆይ፤ በእውነት አንተ አምላክ ነህ፤ ይህንም መልካም ተስፋ ለባሪያህ ሰጥተሃል።
27
በፊትህ ለዘላለም እንዲኖር አሁንም የባሪያህን ቤት ልትባርክ ወድደሃል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የባረክኸው አንተ ስለ ሆንህ፣ ለዘላለም የተባረከ ይሆናል።”
← Chapter 16
Chapter 18 →