bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic Bible (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
/
Isaiah 34
Isaiah 34
Amharic Bible (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
1
እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ቅረቡ፥ ስሙ፤ እናንተ ወገኖች ሆይ፥ አድምጡ፤ ምድርና ሙላዋ፥ ዓለምና ከእርስዋ የሚወጣ ሁሉ ይስሙ።
2
የእግዚአብሔር ቍጣ በአሕዛብ ሁሉ ላይ መዓቱም በሠራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ፈጽሞ አጠፋቸው፥ ለመታረድም አሳልፎ ሰጣቸው።
3
ከእነርሱም የተገደሉት ይጣላሉ፥ የሬሳቸውም ግማት ይሸታል፥ ተራሮችም ከደማቸው የተነሣ ይርሳሉ።
4
የሰማይም ሠራዊት ሁሉ ይበሰብሳሉ፥ ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ፥ ከወይንና ከበለስም ቅጠል እንደሚረግፍ ሠራዊታቸው ሁሉ ይረግፋል።
5
ሰይፌ በሰማይ ሆና እስክትረካ ድረስ ጠጥታለች፤ እነሆ፥ በኤዶምያስና በረገምሁት ሕዝብ ላይ ለፍርድ ትወርዳለች።
6
እግዚአብሔር መሥዋዕት በባሶራ፥ ታላቅም እርድ በኤዶምያስ ምድር አለውና የእግዚአብሔር ሰይፍ በደም ተሞልታለች፥ በስብም፥ በበግ ጠቦትና በፍየል ደምም፥ በአውራም በግ ኵላሊት ስብ ወፍራለች።
7
ጎሽ ከእነርሱ ጋር፥ ወይፈኖችም ከኮርማዎች ጋር ይወድቃሉ፤ ምድራቸውም በደም ትረካለች፥ አፈራቸውም በስብ ትወፍራለች።
8
የእግዚአብሔር የበቀሉ ቀን፥ ስለ ጽዮንም ክርክር የብድራት ዓመት ነው።
9
የኤዶምያስም ፈሳሾች ዝፍት ሆነው ይለወጣሉ፥ አፈርዋም ዲን ይሆናል፥ መሬትዋም የሚቀጠል ዝፍት ትሆናለች።
10
በሌሊትና በቀንም አትጠፋም፥ ጢስዋም ለዘላለም ይወጣል፤ ከትውልድ እስከ ትውልድም ድረስ ባድማ ሆና ትኖራለች፤ ለዘላለም ዓለም ማንም አያልፍባትም።
11
ጭልፊትና ጃርት ግን ይወርሱአታል፤ ጕጕትና ቍራም ይኖሩባታል፤ በላይዋም የመፍረስ ገመድና የባዶነት ቱንቢ ይዘረጋባታል።
12
መሳፍንቶችዋን ወደ መንግሥት ይጠራሉ፥ ነገር ግን ማንም አይገኝባትም፤ አለቆችዋም ሁሉ ምናምኖች ይሆናሉ።
13
በአዳራሾችዋም እሾህ በቅጥሮችዋም ሳማን አሜከላ ይበቅሉባታል፤ የቀበሮም ማደሪያና የሰጐን ስፍራ ትሆናለች።
14
የምድረ በዳም አራዊት ከተኵሎች ጋር ይገናኛሉ፥ አጋንንትም እርስ በርሳቸው ይጠራራሉ፤ ጅንም በዚያ ትኖራለች ለእርስዋም ማረፊያ ታገኛለች።
15
በዚያም ዋሊያ ቤትዋን ትሠራለች እንቍላልም ትጥላለች ትቀፈቅፈውማለች ልጆችዋንም በጥላዋ ትሰበስባለች፤ በዚያም ደግሞ አሞራዎች እያንዳንዳቸው ከባልንጀሮቻቸው ጋር ይሰበሰባሉ።
16
በእግዚአብሔር መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም፤ አፌ አዝዞአልና፥ መንፈሱም ሰብስቦአቸዋልና ከእነዚህ አንዲት አትጠፋም፥ ባልንጀራውንም የሚያጣ የለም።
17
እርሱም ዕጣ ጣለባቸው፥ እጁም በገመድ ከፈለችላቸው፤ ለዘላለም ይገዙአታል፥ ከትውልድም እስከ ትውልድ ድረስ ይቀመጡባታል።
← Chapter 33
Chapter 35 →