bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic Bible (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
/
2 Chronicles 13
2 Chronicles 13
Amharic Bible (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
1
ንጉሡም ኢዮርብዓም በነገሠ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ።
2
ሦስት ዓመት በኢየሩሳሌም ነገሠ፤ የእናቱም ስም ሚካያ ነበረ፥ የገብዓ ሰው የኡርኤል ልጅ ነበረች።
3
በአብያና በኢዮርብዓም መካከልም ሰልፍ ነበረ። አብያም የተመረጡትን አራት መቶ ሺህ ኃያላን ሰልፈኞች ይዞ ወደ ሰልፍ ወጣ፤ ኢዮርብዓምም የተመረጡትን ስምንት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ይዞ በእርሱ ላይ ተሰለፈ።
4
አብያም በተራራማው በኤፍሬም አገር ባለው በጽማራይም ተራራ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ። ኢዮርብዓምና እስራኤል ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤
5
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ መንግሥትን ለዳዊትና ለልጆቹ በጨው ቃል ኪዳን ለዘላለም እንደ ሰጠ በውኑ አታውቁምን?
6
የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ባሪያ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ግን ተነሥቶ በጌታው ላይ ዐመፀ።
7
ክፉዎች ሰዎችና ምናምንቴዎችም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሮብዓም ሕፃንና ለጋ በነበረበት ጊዜ፥ ሊቋቋማቸውም ባልቻለበት ጊዜ፥ በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ላይ በረቱበት።
8
አሁንም በዳዊት ልጆች እጅ የሚሆነውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ልትቋቋሙ ታስባላችሁ። እናንተም እጅግ ታላቅ ሕዝብ ናችሁ፥ ኢዮርብዓምም አማልክት አድርጎ የሠራላችሁ የወርቅ እምቦሶች ከእናንተ ጋር ናቸው።
9
የአሮንን ልጆች የእግዚአብሔርን ካህናትና ሌዋውያን አላሳደዳችሁምን? እንደ ሌሎችም አሕዛብ ልማድ ካህናትን አላደረጋችሁምን? አንድ ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ይዞ ይቀድስ ዘንድ የሚመጣ ሁሉ አማልክት ላልሆኑት ለእነዚያ ካህን ይሆናል።
10
ለእኛ ግን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፥ አልተውነውም፤ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች የአሮን ልጆች ካህናቱ ሌዋውያኑም በሥራቸው ከእኛ ጋር ናቸው።
11
በየጥዋቱና በየማታውም ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ጣፋጩን ዕጣን ያሳርጋሉ፤ የገጹንም ኅብስት በንጹህ ገበታ ላይ፥ የወርቁን መቅረዝና ቀንዲሎቹንም ማታ ማታ እንዲያበሩ ያዘጋጃሉ፤ እኛም የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንጠብቃለን፥ እናንተ ግን ትታችሁታል።
12
እነሆም፥ እግዚአብሔር በእኛ ላይ አለቃ ነው፥ መለከቱንም የሚነፉ ካህናቱ ከእኛ ጋር ናቸው፥ በእናንተም ላይ ይጮኻሉ። የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አይበጃችሁምና ከአባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር አትዋጉ።
13
ኢዮርብዓም ግን ድብቅ ጦር በስተ ኋላቸው አዞረ፤ እነርሱ በይሁዳ ፊት ሆነው ድብቅ ጦሩ በስተ ኋላቸው ነበረ።
14
ይሁዳም ወደ ኋላው በተመለከተ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰልፉ በፊቱና በኋላው ነበረ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ፥ ካህናቱም መለከቱን ነፉ።
15
የይሁዳም ሰዎች ጮኹ፤ የይሁዳም ሰዎች በጮኹ ጊዜ እግዚአብሔር ኢዮርብዓምንና እስራኤልን ሁሉ በአብያና በይሁዳ ፊት መታቸው።
16
የእስራኤልም ልጆች ከይሁዳ ፊት ሸሹ፥ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው።
17
አብያና ሕዝቡ ታላቅ አመታት መቱአቸው፤ ከእስራኤልም አምስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች ተገድለው ወደቁ።
18
በዚያም ጊዜ የእስራኤል ልጆች ተዋረዱ፥ የይሁዳም ልጆች በአባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ታምነው ነበርና አሸነፉ።
19
አብያም ኢዮርብዓምን አሳደደው፥ ከእርሱም ከተሞቹን፥ ቤቴልንና መንደሮችዋን፥ ይሻናንና መንደሮችዋን፥ ዔፍሮንንና መንደሮችዋን ወሰደ።
20
ኢዮርብዓምም ከዚያ በኋላ በአብያ ዘመን አልበረታም፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው፥ ሞተም።
21
አብያም ጸና፥ አሥራ አራትም ሚስቶች አገባ፥ ሀያ ሁለትም ወንዶች ልጆችንና አሥራ ስድስት ሴቶች ልጆችን ወለደ።
22
የአብያም የቀረው ነገርና አካሄዱ የተናገራቸውም ቃሎች በነቢዩ በአዶ መጽሐፍ ተጽፈዋል።
← Chapter 12
Chapter 14 →