bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
/
Psalms 119
Psalms 119
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
1
በአካሄዳቸው ነቀፋ የሌለባቸው፥ በእግዚአብሔር ሕግ መሠረት የሚኖሩ ሰዎች የተባረኩ ናቸው።
2
ትእዛዞቹን የሚጠብቁ፥ በሙሉ ልባቸውም የሚፈልጉት፥ የተባረኩ ናቸው።
3
የማይሳሳቱና በእግዚአብሔር መንገድ የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው።
4
እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ሕጎችህን ሰጥተኸናል፤ በታማኝነት እንድንታዘዛቸውም ነግረኸናል፤
5
ድንጋጌህን በመጠበቅ ታማኝ ለመሆን በብርቱ እመኛለሁ።
6
ትእዛዞችህን ሁሉ በጥንቃቄ ከአስተዋልኩ ኀፍረት ከቶ አይደርስብኝም።
7
የሕግህን ፍጹምነት ባወቅሁ መጠን በንጹሕ ልብ አመሰግንሃለሁ።
8
ሕግህን ስለምፈጽም ፈጽሞ አትተወኝ።
9
ወጣቶች ሕይወታቸውን በንጽሕና መጠበቅ የሚችሉት ትእዛዞችህን በመፈጸም ነው።
10
አንተን በሙሉ ልቤ ስለምፈልግህ ትእዛዞችህን እንዳላፈርስ ጠብቀኝ።
11
አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ አኖራለሁ።
12
እግዚአብሔር ሆይ! አመሰግንሃለሁ፤ የአንተን ሕግ አስተምረኝ።
13
አንተ የሰጠኸውን ሕግ ሁሉ መላልሼ አነባለሁ።
14
የአንተን ትእዛዝ መፈጸም ብዙ ሀብት የማግኘትን ያኽል ያስደስተኛል።
15
ሥርዓትህን አጠናለሁ፤ በምትመራኝ መንገድ ላይም አተኲራለሁ።
16
በሕግህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም።
17
በሕይወት እንድኖርና የቃልህን ትምህርት እንድጠብቅ ለእኔ ለአገልጋይህ መልካም ነገር አድርግልኝ።
18
በሕግህ ውስጥ ያለውን አስደናቂ እውነት ማየት እንድችል ዐይኖቼን ክፈትልኝ።
19
እኔ በምድር ላይ በእንግድነት የምኖረው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ስለዚህ ትእዛዞችህን አትሰውርብኝ።
20
ነፍሴ ሥርዓትህን ለማግኘት ሁልጊዜ በመናፈቅ ተጨነቀች።
21
የተረገሙትንና ከትእዛዞችህ የሚያፈነግጡትን ትዕቢተኞች ትገሥጻለህ።
22
እኔ ሕግህን ስለ ጠበቅሁ ስድባቸውንና ንቀታቸውን ከእኔ አርቅልኝ።
23
መሪዎች ተሰብስበው በእኔ ላይ ቢዶልቱም እንኳ እኔ አገልጋይህ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ።
24
ትእዛዞችህ ያስደስቱኛል፤ መካሪዎቼም እነርሱ ናቸው።
25
ተሸንፌ ትቢያ ላይ ወድቄአለሁ፤ በሰጠኸኝ የተስፋ ቃል መሠረት ሕይወቴን አድስልኝ።
26
አድራጎቴን ሁሉ ተናዘዝኩ፤ አንተም ሰማኸኝ፤ እንግዲህ ሕግህን አስተምረኝ።
27
ሕግህን እንዳስተውል እርዳኝ፤ እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ።
28
ሐዘን በርትቶብኛል፤ በሰጠኸኝ የተስፋ ቃል መሠረት ኀይሌን አድስልኝ።
29
ሐሰትን ከእኔ አርቅልኝ፤ በቸርነትህም ሕግህን አስተምረኝ።
30
ታማኝ ለመሆንና ሕግህን ለመጠበቅ ወስኜአለሁ።
31
እግዚአብሔር ሆይ! በሕግህ ጸንቼአለሁ፤ እባክህ አታሳፍረኝ።
32
ብዙ ማስተዋልን ስለ ሰጠኸኝ፤ ትእዛዞችህን በትጋት እፈጽማለሁ።
33
እግዚአብሔር ሆይ! የሕግህን ትርጒም አስተምረኝ፤ እኔም ዘወትር እከተለዋለሁ።
34
ሕግህን ግለጥልኝ፤ እኔም አከብረዋለሁ፤ በሙሉ ልቤም እጠብቀዋለሁ።
35
ትእዛዞችህ ስለሚያስደስቱኝ እንድፈጽማቸው እርዳኝ።
36
ሀብት ለማግኘት ከመስገብገብ ይልቅ ሕግህን የመፈጸም ፍላጎት እንዲኖረኝ አድርግ።
37
ወደ ከንቱ ነገር ከማዘንበል ጠብቀኝ፤ በቃልህ መሠረት ሕይወቴን አድስልኝ።
38
ለእኔ ለአገልጋይህና ለሚፈሩህ ሁሉ የሰጠኸውን የተስፋ ቃል ፈጽም።
39
ፍርድህ ትክክል ስለ ሆነ ከምፈራው ውርደት ጠብቀኝ።
40
ትእዛዞችህን መጠበቅ እመኛለሁ፤ አንተ እውነተኛ ስለ ሆንክ ሕይወቴን አድስልኝ።
41
እግዚአብሔር ሆይ! ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ወደ እኔ ይድረስ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ።
42
በቃልህ ስለምተማመን ለሚሰድቡኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችላለሁ።
43
ተስፋ የማደርገው የአንተን ፍርድ ስለ ሆነ ዘወትር እውነት እንድናገር እርዳኝ።
44
ሕግህን ባለማቋረጥ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም እፈጽማለሁ።
45
ትእዛዝህን መፈጸም ስለምወድ በፍጹም ነጻነት እኖራለሁ።
46
ትእዛዞችህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ ከቶም አላፍርም።
47
በትእዛዞችህ የምደሰተው እነርሱን ስለምወዳቸው ነው።
48
የምወዳቸውን ትእዛዞችህን አከብራለሁ፤ ስለ ሥርዓትህም በተመስጦ አሰላስላለሁ።
49
ተስፋ የማደርገው በእርሱ ላይ ስለ ሆነ ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኸውን የተስፋ ቃል አስብ።
50
የተስፋ ቃልህ ሕይወቴን ስላደሰልኝ፥ በመከራዬ ጊዜ እንኳ እጽናናለሁ።
51
ትዕቢተኞች ዘወትር ያፌዙብኛል፤ እኔ ግን ከትእዛዞችህ አልርቅም።
52
እግዚአብሔር ሆይ! መጽናናትን የሚሰጠኝ ስለ ሆነ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን ሕግህን አስታውሳለሁ።
53
ክፉ ሰዎች ሕግህን ሲተላለፉ በማየቴ በብርቱ ተቈጣሁ።
54
በምኖርበት ቦታ ሁሉ ሕጎችህ የመዝሙሬ አዝማቾች ናቸው።
55
እግዚአብሔር ሆይ! በሌሊት ስምህን አስታውሳለሁ፤ በሕግህም ጸንቼ እኖራለሁ።
56
ትእዛዞችህን ዘወትር ስለማከብር፥ በረከትን አገኘሁ።
57
እግዚአብሔር ሆይ! እኔ የምፈልገው አንተን ብቻ ነው፤ ሕግህንም ለመጠበቅ ቃል እገባለሁ።
58
በተስፋ ቃልህ መሠረት ምሕረት እንድታደርግልኝ ከልብ እለምንሃለሁ።
59
አካሄዴን መርምሬ የተረዳሁት ስለ ሆነ ሥርዓትህን ለመከተል ቃል እገባለሁ።
60
ያለ ማመንታት ትእዛዞችህን ለመፈጸም እተጋለሁ።
61
ክፉዎች ወጥመድ ቢዘረጉብኝም እኔ ግን ሕግህን አልረሳም።
62
ስለ ትክክለኛ ፍርድህ አንተን ለማመስገን በእኩለ ሌሊት እነሣለሁ።
63
አንተን የሚፈሩትንና ሕግህን የሚያከብሩትን ሁሉ እወዳቸዋለሁ።
64
እግዚአብሔር ሆይ! ምድር በዘለዓለማዊው ፍቅርህ የተሞላች ናት፤ ሕጎችህን አስተምረኝ።
65
እግዚአብሔር ሆይ! የተስፋ ቃልህን ጠብቀሃል፤ ለእኔም ለአገልጋይህ ቸር ሆነሃል።
66
በትእዛዞችህ ስለምተማመን አስተዋይነትንና ዕውቀትን ስጠኝ።
67
አንተ እኔን ከመቅጣትህ በፊት እሳሳት ነበር፤ አሁን ግን ለቃልህ እታዘዛለሁ።
68
አንተ ቸር ስለ ሆንክ ቸር የሆነውን ታደርጋለህ፤ ሕጎችህን አስተምረኝ።
69
ምንም እንኳ ትዕቢተኞች በሐሰት ስሜን ቢያጠፉ እኔ ትእዛዞችህን በሙሉ ልቤ እጠብቃለሁ።
70
እነርሱ ትዕቢተኞችና ስሜተ ቢሶች ናቸው፤ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል።
71
ሕግህን እንድማር ስላደረገኝ መቀጣቴ መልካም ሆነልኝ።
72
ከብዙ ወርቅና ከብዙ ብር ይልቅ ለእኔ እጅግ ዋጋ ያለው አንተ የምትሰጠው ሕግ ነው።
73
እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እማር ዘንድ አስተዋይነትን ስጠኝ።
74
በተስፋ ቃልህ ስለምታመን አንተን የሚያከብሩ ሁሉ እኔን በሚያዩበት ጊዜ ደስ ይበላቸው።
75
እግዚአብሔር ሆይ! ፍርድህ እውነተኛ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ የቀጣኸኝም እውነተኛ በመሆንህ ነው።
76
ለእኔ ለአገልጋይህ በሰጠኸው የተስፋ ቃል መሠረት ዘለዓለማዊው ፍቅርህ ያጽናናኝ።
77
በሕግህ ደስ ስለሚለኝ ሕያው ሆኜ ለመኖር እችል ዘንድ ርኅራኄ አድርግልኝ።
78
በሐሰት ያለምክንያት የሚከሱኝ ትዕቢተኞች ይዋረዱ፤ እኔ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ።
79
አንተን የሚፈሩ ትእዛዞችህን ያውቁ ዘንድ ወደ እኔ ይምጡ።
80
ኀፍረት እንዳይደርስብኝ ሕግህን በትክክል እንድፈጽም እርዳኝ።
81
የአንተን አዳኝነት በሙሉ ልቤ እመኛለሁ። እምነቴን በቃልህ ላይ አድርጌአለሁ።
82
“መቼ ታጽናናኝ ይሆን?” ብዬ የተስፋ ቃልህን በመጠባበቅ ዐይኖቼ ደከሙ።
83
ጢስ በሚጤስበት ቤት ተሰቅሎ እንደ ተጨማደደ የወይን ጠጅ አቊማዳ ከጥቅም ውጪ ሆኜአለሁ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ሕግህን አልረሳሁም።
84
እኔ አገልጋይህ እስከ መቼ ልቈይ? የሚያሳድዱኝንስ የምትቀጣቸው መቼ ነው?
85
ሕግህን የማይጠብቁ ትዕቢተኞች እኔን ለማጥመድ ጒድጓድ ቆፍረዋል።
86
ትእዛዞችህ ሁሉ የጸኑ ናቸው፤ ያለ ምክንያት ስለሚያሳድዱኝ እርዳኝ!
87
እነርሱ ሊገድሉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን ችላ አላልኩም።
88
ሕግህን እጠብቅ ዘንድ በዘለዓለማዊ ፍቅርህ ሕይወትን ስጠኝ።
89
እግዚአብሔር ሆይ! ቃልህ ዘለዓለማዊ ነው፤ በሰማይም ጸንቶ ይኖራል።
90
ቃልህ በዘመናት ሁሉ ጸንቶ ይኖራል፤ ምድርን መሠረትካት፤ ጸንታም ትኖራለች።
91
ፍጥረቶች ሁሉ አገልጋዮችህ ስለ ሆኑ ትእዛዞችህ እስከ ዛሬ ጸንተው ቈይተዋል።
92
ሕግህ የደስታዬ ምንጭ ባይሆን ኖሮ ከሥቃዬ የተነሣ በሞትኩ ነበር።
93
በሕግህ አማካይነት በሕይወት እንድኖር ጠብቀኸኛልና ሕግህን ከቶ አልረሳም።
94
እኔ የአንተ ስለ ሆንኩ አድነኝ! ትእዛዞችህንም ለማክበር እፈልጋለሁ።
95
ክፉዎች እኔን ለመግደል ያደባሉ፤ እኔ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ።
96
የሁሉም ነገር ፍጹምነት ወሰን አለው፤ የትእዛዞችህ ፍጹምነት ግን ወሰን የለውም።
97
ሕግህን እጅግ እወዳለሁ፤ ስለ እርሱ ቀኑን ሙሉ አስባለሁ።
98
ትእዛዝህ መቼም ከአእምሮዬ ስለማይጠፋ፥ ከጠላቶቼ ሁሉ ይልቅ እኔን አስተዋይ ያደርገኛል።
99
ሕግህን ዘወትር ስለማሰላስል፥ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የበለጠ ጥበብ አለኝ።
100
ትእዛዞችህን ሁሉ ስለምፈጽም፥ ከሽማግሌዎች ሁሉ የበለጠ አስተዋይነት አለኝ።
101
ለቃልህ መታዘዝ ስለምፈልግ፥ መጥፎ ጠባይን ሁሉ አስወግጄአለሁ።
102
ያስተማርከኝ አንተ ስለ ሆንክ ከሕግህ ፈቀቅ አላልኩም።
103
ቃልህ እንዴት ጣፋጭ ነው! ከማር ወለላ ይልቅ ይጣፍጣል።
104
ከሕግህ ማስተዋልን አግኝቼአለሁ፤ ስለዚህ የሐሰት መንገድን ሁሉ እጠላለሁ።
105
ቃልህ እንደ መብራት ይመራኛል፤ ለመንገዴም ብርሃን ነው።
106
እውነተኛ ትእዛዞችህን ለመጠበቅ በመሐላ የገባሁትን ቃል አጸናለሁ።
107
እግዚአብሔር ሆይ! ሥቃዬ እጅግ ከባድ ስለ ሆነ በተስፋ ቃልህ መሠረት በሕይወት አኑረኝ።
108
እግዚአብሔር ሆይ! የምስጋና ጸሎቴን ተቀበል፤ ትእዛዞችህንም አስተምረኝ።
109
ሕይወቴ በአደጋ ላይ ቢሆንም እንኳ ሕግህን አልረሳም
110
ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤ እኔ ግን ከትእዛዞችህ ፈቀቅ አላልኩም።
111
ሕግህ ዘለዓለማዊ ሀብቴ ነው፤ የልቤም ደስታ እርሱ ነው።
112
እስከምሞትበት ቀን ድረስ ሕጎችህን ለመፈጸም ወስኜአለሁ፤
113
በፍጹም ልባቸው በአንተ የማይታመኑትን ወላዋዮች ሁሉ ጠላሁ፤ ሕግህን ግን ወደድኩ።
114
አንተ ጋሻዬና መሸሸጊያዬ ነህ፤ በቃልህ ተስፋ አደርጋለሁ።
115
እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ወዲያ ራቁ፤ እኔ የአምላኬን ትእዛዞች መጠበቅ እፈልጋለሁ።
116
በሕይወት እኖር ዘንድ በተስፋ ቃልህ መሠረት አበርታኝ! ተስፋዬንም አታጨልምብኝ!
117
እድን ዘንድ ደግፈኝ፤ ሁልጊዜም ሕጎችህን እፈጽማለሁ።
118
ዕቅዳቸው ተንኰልና ሐሰት የሞላበት በመሆኑ፥ ከሕግህ የሚያፈነግጡትን ሁሉ ታስወግዳቸዋለህ።
119
ክፉዎችን ሁሉ እንደ ቆሻሻ ነገር ታስወግዳቸዋለህ፤ ስለዚህ ሥርዓትህን እወዳለሁ።
120
አንተን ከመፍራቴ የተነሣ ሰውነቴ ተንቀጠቀጠ፤ ፍርድህንም እጅግ ፈራሁት።
121
ትክክልና መልካም የሆነውን ነገር አድርጌአለሁ፤ ስለዚህ ለሚጨቊኑኝ ጠላቶቼ አትተወኝ!
122
የእኔን የአገልጋይህን ደኅንነት አረጋግጥ፤ እብሪተኞች እንዲያጠቁኝ አታድርግ።
123
አዳኝነትህንና እውነተኛ ቃል ኪዳንህን በመጠባበቅ ዐይኖቼ ደከሙ።
124
ለእኔ ለአገልጋይህ ፍቅርህን አሳይ፤ ሕጎችህንም አስተምረኝ።
125
እኔ አገልጋይህ ነኝ፤ ሥርዓትህንም እንዳውቅ ማስተዋልን ስጠኝ።
126
እግዚአብሔር ሆይ! ሰዎች ሕግህን ስለ ጣሱ ፍርድህን የምትገልጥበት ጊዜው አሁን ነው።
127
ትእዛዞችህን ከወርቅ ይልቅ አብልጬ እወዳለሁ፤ አዎ፥ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ አብልጬ እወዳለሁ።
128
የአንተ ትእዛዞች ትክክል መሆናቸውን ስለማምን የሐሰትን መንገድ ሁሉ እጠላለሁ።
129
ሥርዓቶችህ አስደናቂዎች ናቸው፤ እኔም በሙሉ ልቤ እታዘዛቸዋለሁ።
130
የቃልህ ትርጒም ብርሃን ይሰጣል፤ ሞኞችን አስተዋዮች ያደርጋል።
131
ትእዛዞችህን በጣም ከመናፈቄ የተነሣ አፌን በጒጒት እከፍታለሁ።
132
ወደ እኔ ተመለስ፤ ለሚወዱህ ሁሉ እንደምታደርገውም ምሕረት አድርግልኝ።
133
በተስፋ ቃልህ መሠረት አካሄዴን አስተካክል፤ ስሕተትም እንዲሠለጥንብኝ አታድርግ።
134
ትእዛዞችህን መጠበቅ እንድችል ከሚጨቊኑኝ ሰዎች እጅ አድነኝ።
135
የፊትህን ብርሃን ለባሪያህ አብራለት፤ ሕግህንም አስተምረኝ።
136
ሰዎች ሕግህን ስለ ጣሱ እንባዬ እንደ ወንዝ ውሃ ይፈስሳል።
137
እግዚአብሔር ሆይ! አንተ እውነተኛ ነህ፤ ፍርድህም ቅን ነው።
138
ሕግህ በፍጹም እውነትና ትክክል ነው።
139
ጠላቶቼ ትእዛዞችህን አለመቀበላቸው በጣም ያበሳጨኛል።
140
የተስፋ ቃልህ እጅግ የታመነ ነው፤ እኔም በጣም እወደዋለሁ።
141
እኔ የማልጠቅምና የተናቅሁ ብሆንም እንኳ ሥርዓትህን አልዘነጋሁም።
142
ጽድቅህ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ ሕግህም ዘለዓለማዊ እውነት ነው።
143
ብዙ ችግርና ጭንቀት ደርሶብኛል፤ ትእዛዞችህ ግን ደስታን ይሰጡኛል።
144
ሥርዓትህ ዘወትር ትክክል ነው፤ በሕይወት ለመኖር እንድችል ማስተዋልን ስጠኝ።
145
እግዚአብሔር ሆይ! በሙሉ ልቤ፤ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ ስማኝ፤ እኔም ሕጎችህን እፈጽማለሁ።
146
ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ አድነኝም፤ እኔም ሕግህን እጠብቃለሁ።
147
ጎህ ከመቅደዱ በፊት ርዳታህን በመፈለግ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ በገባህልኝም ቃል ተስፋ አደርጋለሁ።
148
ቃልህን በማሰላሰል ለማጥናት ሌሊቱን ሙሉ እነቃለሁ።
149
እግዚአብሔር ሆይ! ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህ ስማኝ! በትእዛዝህ መሠረት ሕይወቴን ጠብቅ!
150
ሕግህን የማያከብሩ፥ ክፉ ዕቅድ ዐቅደው የሚያሳድዱኝ ሰዎች ወደ እኔ ቀርበዋል።
151
እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን ለእኔ ቅርብ ነህ፤ ትእዛዞችህ ሁሉ እውነተኞች ናቸው።
152
ሕጎችህን በማጥናት ለዘለዓለም እንዲጸኑ ያደረግሃቸው መሆናቸውን ከብዙ ጊዜ በፊት ተረድቼአለሁ።
153
እኔ ሕግህን አልረሳሁም፤ ስለዚህ ችግሬን ተመልክተህ አድነኝ።
154
ስለ መብቴ ተከራከርልኝ፤ አድነኝ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት በሕይወት አኑረኝ።
155
ሕግህን ስለማይፈልጉ ክፉዎች የመዳን ተስፋ የላቸውም።
156
እግዚአብሔር ሆይ! ርኅራኄህ ታላቅ ነው፤ በትእዛዝህ መሠረት በሕይወት አኑረኝ!
157
የሚጠሉኝና የሚያሳድዱኝ ብዙዎች ናቸው፤ እኔ ግን ከሕግህ ፈቀቅ አላልኩም።
158
ቃልህን ስለማይጠብቁ፥ ከሐዲዎችን አይቼ ተጸየፍኳቸው።
159
እግዚአብሔር ሆይ! ትእዛዞችህን እንደምወድ ተመልከት፤ ስለዚህ በዘለዓለማዊ ፍቅርህ በሕይወት አኑረኝ!
160
ቃልህ በጽኑ መሠረት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ትክክለኛ ፍርድህም ዘለዓለማዊ ነው።
161
ባለሥልጣኖች ያለ ምክንያት ያሳድዱኛል፤ እኔ ግን ቃልህን በፍርሃት አከብራለሁ።
162
ብዙ ምርኮ አግኝቶ እንደሚደሰት ሰው በተስፋ ቃልህ እጅግ ደስ ይለኛል።
163
ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁም፤ ሕግህን ግን እወዳለሁ።
164
ስለ እውነተኛ ፍርድህ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ።
165
ሕግህን የሚወዱ ፍጹም የሆነ ሰላም አላቸው፤ ከቶ ምንም ነገር ሊያሰናክላቸው አይችልም።
166
እግዚአብሔር ሆይ! አዳኝነትህን በተስፋ እጠባበቃለሁ፤ ትእዛዞችህንም እፈጽማለሁ።
167
ትእዛዞችህን እጠብቃለሁ፤ በሙሉ ልቤም እወዳቸዋለሁ።
168
ትእዛዞችህንና ሕግህን አከብራለሁ፤ የምሠራውንም ሁሉ አንተ ታያለህ።
169
እግዚአብሔር ሆይ! ርዳታህን ለማግኘት ወደ አንተ ስጮኽ ስማኝ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት ማስተዋልን ስጠኝ።
170
ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ።
171
ሕግህን ስለምታስተምረኝ ዘወትር አመሰግንሃለሁ።
172
ትእዛዞችህ ሁሉ ትክክለኞች ስለ ሆኑ፥ ስለ ቃልህ እዘምራለሁ።
173
ትእዛዞችህን ስለ መረጥኩ፥ እኔን ለመርዳት ዘወትር ዝግጁ ሁን።
174
እግዚአብሔር ሆይ! አዳኝነትህን እናፍቃለሁ፤ በሕግህም ደስ ይለኛል።
175
አንተን ለማመስገን እንድችል ዕድሜዬን አርዝምልኝ፤ ሥርዓትህም ረዳቴ ይሁን።
176
እንደ ጠፋ በግ ተቅበዝብዤአለሁ፤ ነገር ግን ትእዛዞችህን ስላልረሳሁ፥ እኔን አገልጋይህን ፈልገኝ።
← Chapter 118
Chapter 120 →