bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
/
Mark 11
Mark 11
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
1
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም በቀረቡ ጊዜ በቤተ ፋጌና በቢታንያ አድርገው ወደ ደብረ ዘይት ደረሱ፤ ከዚያም ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፦
2
“በፊታችሁ ወዳለው መንደር ቀድማችሁ ሂዱ፤ እዚያም እንደ ደረሳችሁ ወዲያውኑ ማንም ሰው ገና ያልተቀመጠበት የአህያ ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፍቱትና ወዲህ አምጡት።
3
ማንም ሰው ‘ለምን ይህን ታደርጋላችሁ?’ ቢላችሁ፥ ‘ጌታ ስለሚያስፈልገው ነው፤ ወዲያውኑ መልሶ ይልከዋል፤’ በሉት።”
4
እነርሱም ሄደው ውርንጫውን በመንገድ ዳር በቤት ደጃፍ ታስሮ አገኙትና ፈቱት።
5
በዚያም ጊዜ እዚያ ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ፦ “ውርንጫውን የምትፈቱት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው።
6
እነርሱም ኢየሱስ ያላቸውን ነገሩአቸው፤ ሰዎቹም ተዉአቸው።
7
ደቀ መዛሙርቱም የአህያውን ውርንጫ ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ ልብሳቸውን በውርንጫው ጀርባ ላይ አድርገው ኢየሱስ ተቀመጠበት።
8
ብዙ ሰዎች ሸማቸውን በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር፤ ሌሎችም ከዱር የዛፍ ዝንጣፊ እየቈረጡ በመንገድ ላይ ይጐዘጒዙ ነበር።
9
ከፊት የቀደሙትና ከኋላ የሚከተሉትም ሁሉ፥ “ሆሳዕና! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!
10
የምትመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፤ ሆሳዕና በአርያም!” እያሉ ይጮኹ ነበር።
11
ኢየሱስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዙሪያውም ያለውን ነገር ሁሉ ተመለከተ፤ ቀኑም መሽቶ ስለ ነበር ከዐሥራ ሁለቱ ጋር ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ወደ ቢታንያ ሄደ።
12
በማግስቱም ከቢታንያ ሲመለሱ ኢየሱስ ተራበ።
13
ቅጠልዋ የለመለመ የበለስ ዛፍም በሩቅ አይቶ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደ ሆነ በማለት ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ወደ እርስዋ በቀረበ ጊዜ በለስ የሚያፈራበት ወራት ስላልነበረ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም።
14
ስለዚህ ኢየሱስ የበለስዋን ዛፍ፥ “ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ!” አላት። ይህንንም ሲናገር ደቀ መዛሙርቱ ሰሙ።
15
ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በውስጡ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሰዎች ያስወጣ ጀመር፤ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠ፤
16
ማንም ሰው ምንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ እንዲተላለፍ አልፈቀደም።
17
እንዲህም ሲል አስተማራቸው፤ “ ‘ቤቴ ለሕዝብ ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል!’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት።”
18
የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ይህን ሲናገር ሰሙት፤ ሕዝቡም ሁሉ በትምህርቱ ይደነቁ ስለ ነበር ፈሩት፤ ስለዚህ እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት ዘዴ ይፈልጉ ነበር።
19
በመሸም ጊዜ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከከተማ ወጡ።
20
በማግስቱ ማለዳ በመንገድ ሲያልፉ የበለሲቱ ዛፍ ከነስርዋ ደርቃ አዩአት።
21
ጴጥሮስም ነገሩ ትዝ ብሎት ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ! እነሆ፥ የረገምሃት ዛፍ ደርቃለች” አለው።
22
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእግዚአብሔር እመኑ፤
23
በእውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ሰው በልቡ ሳይጠራጠር የሚፈልገው ነገር እንደሚፈጸምለት አምኖ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር፤’ ቢል ይሆንለታል።
24
ስለዚህ በጸሎት ማናቸውንም ነገር ብትለምኑ፥ እንደ ተፈጸመላችሁ አድርጋችሁ እመኑ፤ የምትለምኑትም ሁሉ ይሰጣችኋል።
25
በሰማይ ያለው አባታችሁ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲልላችሁ እናንተም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ ሰው በአንዳች ነገር አስቀይሞአችሁ ከሆነ ይቅርታ አድርጉለት።
26
እናንተ የሌሎችን በደል ይቅር ባትሉ ግን በሰማይ ያለው አባታችሁ የእናንተንም ኃጢአት ይቅር አይልላችሁም።”
27
እንደገናም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ኢየሱስም በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲዘዋወር ሳለ የካህናት አለቆች፥ የሕግ መምህራንና ሽማግሌዎች ወደ እርሱ መጡና
28
“እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ወይስ እነዚህን ነገሮች እንድታደርግ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።
29
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተ መልስ ከሰጣችሁኝ፥ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ።
30
የዮሐንስ ጥምቀት ከእግዚአብሔር ነበረ ወይስ ከሰው? እስቲ መልሱልኝ፤” አላቸው።
31
እነርሱም “እንግዲህ ምን እንበል?” በማለት እርስ በርሳቸው ተመካከሩ፤ “ ‘ከእግዚአብሔር ነው፥’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤
32
‘ከሰው ነው፥’ ብንልሳ?” ይህን እንዳይሉ ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን በእርግጥ ነቢይ ነው ይሉ ስለ ነበር ፈሩ።
33
ስለዚህ “እኛ አናውቅም።” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም “እንግዲያውስ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ አልነግራችሁም፤” አላቸው።
← Chapter 10
Chapter 12 →