bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
/
Luke 6
Luke 6
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
1
በሰንበት ቀን ኢየሱስ በእርሻ መካከል ሲያልፍ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ የስንዴ እሸት እየቀጠፉ በእጃቸው ማሸትና መብላት ጀመሩ፤
2
ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ደቀ መዛሙርቱን “በሰንበት ቀን ሊደረግ የማይገባውን ነገር ስለምን ታደርጋላችሁ?” አሉአቸው።
3
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እርሱና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ዳዊት ያደረገውን አላነበባችሁምን?
4
እርሱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ከካህናት በቀር ለሌሎች መብላት ያልተፈቀደውን የተቀደሰ የመባ ኅብስት አንሥቶ በላ፤ ከእርሱ ጋር ለነበሩትም ሰዎች ሰጣቸው።”
5
ቀጥሎም ኢየሱስ “የሰው ልጅ ለሰንበትም ጌታዋ ነው፤” አላቸው።
6
በሌላም ሰንበት ቀን ኢየሱስ ወደ ምኲራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ እዚያም ቀኝ እጁ ሽባ የሆነ አንድ ሰው ነበር።
7
የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያንም ኢየሱስን የሚከሱበት ወንጀል ለማግኘት ፈልገው፥ “እስቲ በሰንበት ቀን ይፈውሰው እንደ ሆነ እንይ፤” ብለው ይጠባበቁት ነበር።
8
ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እጀ ሽባውን “ተነሥና በመካከል ቁም!” አለው፤ ሽባውም ተነሣና በመካከል ቆመ።
9
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “እስቲ ልጠይቃችሁ፤ ለመሆኑ በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነውን? ወይስ ክፉ? ነፍስን ማዳን ነውን ወይስ ማጥፋት?” አላቸው።
10
ኢየሱስ በዙሪያው ወዳሉት ሰዎች ሁሉ ከተመለከተ በኋላ እጀ ሽባውን፥ “እጅህን ዘርጋ!” አለው። እርሱም እጁን በዘረጋው ጊዜ ዳነለትና እንደ ሌላው እጅ ደኅና ሆነ።
11
የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ግን በጣም ተቈጥተው በኢየሱስ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተመካከሩ።
12
አንድ ቀን ኢየሱስ ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጣ፤ እዚያ ሌሊቱን ሙሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ ዐደረ።
13
በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠራ፤ ከእነርሱም መካከል ዐሥራ ሁለቱን መርጦ “ሐዋርያት” ብሎ ሰየማቸው፤
14
እነርሱም ቀጥለው የሚገኙት ናቸው፦ ጴጥሮስ ብሎ የሠየመው፥ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስ፥ ፊልጶስና በርቶሎሜዎስ፥
15
ማቴዎስና ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና “ቀናተኛ” ተብሎ የሚጠራው ስምዖን፥
16
የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው አስቆሮታዊው ይሁዳ።
17
ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ከተራራው ወርዶ በሜዳ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ በዚያ ነበሩ፤ እንዲሁም ሊሰሙትና ከበሽታቸው ሊፈወሱ ፈልገው የመጡ፥ እጅግ ብዙ ሕዝብ ነበሩ። እነርሱም የመጡት ከይሁዳ ምድር ከኢየሩሳሌም ከተማ፥ በባሕር አጠገብ ከሚገኙት ከጢሮስና ከሲዶና ከተሞች ነበር።
18
በርኩሳን መናፍስት ተይዘው ይታወኩ የነበሩት ሰዎችም መጥተው ይፈወሱ ነበር።
19
የማዳን ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን ለመንካት ይፈልጉ ነበር።
20
ኢየሱስ ቀና ብሎ ወደ ደቀ መዛሙርቱ እየተመለከተ እንዲህ አላቸው፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፥ እናንተ ድኾች የተባረካችሁ ናችሁ!
21
እናንተ አሁን የምትራቡ፥ በኋላ ትጠግባላችሁና የተባረካችሁ ናችሁ! እናንተ አሁን የምታለቅሱ፥ በኋላ ትስቃላችሁና የተባረካችሁ ናችሁ፤
22
“በእኔ በሰው ልጅ ምክንያት ሰዎች ሲጠሉአችሁ፥ ሲለዩአችሁ፥ ሲያንቋሽሹአችሁና ስማችሁን ሲያጠፉ የተባረካችሁ ናችሁ!
23
በሰማይ ዋጋችሁ ትልቅ ነውና ይህ ሁሉ ሲደርስባችሁ የተባረካችሁ ናችሁ! ሐሴትም አድርጉ፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ እንዲህ ያለውን ክፋት አድርገውባቸው ነበር።
24
“እናንተ ሀብታሞች ግን ለምቾታችሁ የሚሆነውን ሁሉ አሁን አግኝታችኋልና ወዮላችሁ!
25
“እናንተ አሁን የጠገባችሁ፥ ኋላ ትራባላችሁና ወዮላችሁ! እናንተ አሁን የምትስቁ፥ ኋላ ስለምታዝኑና ስለምታለቅሱ ወዮላችሁ!
26
“ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩ ወዮላችሁ! አባቶቻቸውም ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ አድርገው ነበር።
27
“ለእናንተ ለምትሰሙኝ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም ነገር አድርጉ፤
28
የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚበድሉአችሁም ጸልዩላቸው፤
29
አንዱን ጒንጭህን በጥፊ ለሚመታህ፥ ሌላውንም ጒንጭህን እንዲመታ አዙርለት፤ ነጠላህን ለሚወስድብህ፥ እጀ ጠባብህንም ጨምረህ ስጠው፤
30
ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ንብረትህን የሚወስድብህን ሰው እንዲመልስ አትጠይቀው።
31
ሰዎች ለእናንተ ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ ለእነርሱ አድርጉላቸው።
32
“የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ብልጫ ታገኛላችሁ! ኃጢአተኞችም የሚወዱአቸውን ይወዳሉ፤
33
መልካም ነገር ለሚያደርጉላችሁ እናንተም መልካም ነገር ብታደርጉላቸው ምን ብልጫ ታገኛላችሁ! ኃጢአተኞችም እንዲሁ ያደርጋሉ፤
34
‘ይመልሱልናል’ ብላችሁ ለምታስቡአቸው ሰዎች ብታበድሩ ምን ብልጫ ታገኛላችሁ? ያንኑ ያበደሩትን መልሰው ለመቀበልማ ኃጢአተኞችም ለኃጢአተኞች ያበድራሉ።
35
እናንተ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ! መልካም ነገርም አድርጉላቸው፤ ‘ብድራችን ይመለስልናል’ ብላችሁ ተስፋ ሳታደርጉ አበድሩ፤ ይህን ብታደርጉ ዋጋችሁ ትልቅ ይሆናል፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጆችም ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለውለታ ቢሶችና ለክፉዎች እንኳ ሳይቀር ቸር ነው።
36
የሰማይ አባታችሁ መሓሪ እንደ ሆነ እናንተም እንዲሁ መሓሪዎች ሁኑ።
37
“በማንም ላይ አትፍረዱ፤ በእናንተም ላይ አይፈረድባችሁም፤ ሌሎችን አትንቀፉ፤ እናንተም አትነቀፉም፤ ይቅር በሉ፤ እናንተም ይቅርታ ታገኛላችሁ፤
38
ስጡ፤ ለእናንተም ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ እንዲሁ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም በጥሩ መስፈሪያ ታምቆና ተጠቅጥቆ እስኪትረፈረፍ ድረስ ተሰፍሮ ይሰጣችኋል።”
39
ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “ ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? እንዲህማ ቢያደርግ ሁለቱም ተያይዘው በጒድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ።
40
ተማሪ ከአስተማሪው አይበልጥም፤ ይሁን እንጂ ተማሪ ትምህርቱን በደንብ ከተማረ እንደ አስተማሪው ይሆናል።
41
“በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ ሳታይ ስለምን በወንድምህ ዐይን ያለውን ጒድፍ ትመለከታለህ?
42
ደግሞስ በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን ‘ወንድሜ ሆይ፥ እስቲ በዐይንህ ያለውን ጒድፍ ላውጣልህ፤’ ማለት እንዴት ትችላለህ? አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚህ በኋላ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጒድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ።
43
“መልካም ዛፍ መጥፎ ፍሬ አያፈራም፤ እንዲሁም መጥፎ ዛፍ መልካም ፍሬ አያፈራም።
44
ዛፍ ሁሉ በፍሬው ይታወቃል፤ ከእሾኽ የበለስ ፍሬ አይለቀምም፤ እንዲሁም ከእሾኻማ ቊጥቋጦ የወይን ፍሬ አይለቀምም።
45
ስለዚህ ደግ ሰው ከመልካም ልቡ መልካምን ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከመጥፎ ልቡ ክፉውን ነገር ያወጣል። ሰው በአፉ የሚናገረው ከልቡ ሞልቶ የተረፈውን ነው።
46
“እኔ የምነግራችሁን አትፈጽሙም፤ ታዲያ፥ ስለምን ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! እያላችሁ ትጠሩኛላችሁ?
47
ወደ እኔ የሚመጣና ቃሌንም ሰምቶ የሚፈጽም ማንን እንደሚመስል ልንገራችሁ፤
48
እርሱ በጥልቅ ቆፍሮ ቤቱን በጽኑ አለት ላይ የመሠረተውን ሰው ይመስላል፤ ጐርፍ መጥቶ ያንን ቤት ገፋው፤ ነገር ግን በጽኑ መሠረት ላይ ስለ ተሠራ ሊያነቃንቀው አልቻለም።
49
ቃሌን ሰምቶ የማይፈጽም ግን ያለ መሠረት ቤቱን በዐፈር ላይ የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍ መጥቶ ያንን ቤት በገፋው ጊዜ ወዲያውኑ ወደቀ፤ አወዳደቁም እጅግ ታላቅ ሆነ።”
← Chapter 5
Chapter 7 →