bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
/
Judges 10
Judges 10
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
1
አቤሜሌክ ከሞተ በኋላ የዶዶ የልጅ ልጅ የፑአ ልጅ ቶላዕ እስራኤልን ለማዳን ተነሣ፤ እርሱም ከይሳኮር ነገድ ሲሆን የሚኖረውም በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ሻሚር ተብላ በምትጠራ ስፍራ ነበር፤
2
ይህ ሰው ኻያ ሦስት ዓመት የእስራኤል መሪ ሆኖ ከቆየ በኋላ ሞተ፤ በሻሚርም ተቀበረ።
3
ከቶላዕ ቀጥሎ ገለዓዳዊው ያኢር ተነሣ፤ እርሱም ኻያ ሁለት ዓመት የእስራኤል መሪ ሆነ፤
4
በሠላሳ አህዮች ላይ ተቀምጠው የሚጋልቡ ሠላሳ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በገለዓድ ምድር ሠላሳ ከተሞች ነበሩአቸው፤ እነዚህም ከተሞች እስከ ዛሬ የያኢር መንደሮች ተብለው ይጠራሉ፤
5
ያኢር ሞተ፤ በቃሞንም ተቀበረ።
6
እስራኤላውያን ባዓልና ዐስታሮት የተባሉትን ባዕዳን አማልክት እንዲሁም የሶርያን፥ የሲዶናን፥ የሞአብን፥ የዐሞንንና የፍልስጥኤምን አማልክት በማምለክ እንደገና እግዚአብሔርን በደሉ፤ እርሱንም ማምለክ ተዉ፤
7
ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ ተቈጣ፤ ለፍልስጥኤማውያንና ለዐሞናውያን አሳልፎ ሰጣቸው።
8
አሞናውያንና ፍልስጥኤማውያንም ከዮርዳኖስ ማዶ በአሞራውያን ምድር በገለዓድ ውስጥ የሚኖሩትን እስራኤላውያንን ለዐሥራ ስምንት ዓመት አስጨንቀው ገዙአቸው።
9
ዐሞናውያን የይሁዳን፥ የብንያምንና የኤፍሬምን ነገዶች ለመውጋት ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ እስራኤላውያንም እጅግ ተጨነቁ።
10
ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን “አንተን አምላካችንን ትተን በዓል ተብለው የሚጠሩትን ባዕዳን አማልክት በመከተላችን በአንተ ላይ በደል ሠርተናል” በማለት ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
11
እግዚአብሔር እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ግብጻውያን፥ አሞራውያን፥ ዐሞናውያን፥ ፍልስጥኤማውያን፥ ሲዶናውያን፥ ዐማሌቃውያንና ማዖናውያን ከዚህ በፊት ጨቊነው በገዙአችሁ ጊዜ ወደ እኔ ጮኻችሁ ነበር፤ ታዲያ እኔስ ከእነርሱ ጭቈና በመታደግ አድኛችሁ አልነበረምን?
13
እናንተ ግን እስከ አሁን ድረስ እኔን ትታችሁ ለባዕዳን አማልክት ሰገዳችሁ፤ ስለዚህ እኔ እናንተን ዳግመኛ አልታደጋችሁም፤
14
ሂዱ፤ ወደ መረጣችኋቸው ባዕዳን አማልክትም ጩኹ፤ መከራ በሚደርስባችሁ ጊዜም እስቲ እነርሱ ራሳቸው ያድኑአችሁ።”
15
የእስራኤል ሕዝብ ግን እግዚአብሔርን “በእርግጥ በድለናል፤ አንተ በእኛ ላይ የፈለግኸውን አድርግብን፤ ብቻ እባክህ የዛሬን አድነን” አሉት።
16
ባዕዳን አማልክታቸውንም አስወግደው፥ እግዚአብሔርን አመለኩ፤ እግዚአብሔርም ስለ እስራኤል መከራ እጅግ አዘነ።
17
ከዚህ በኋላ የዐሞናውያን ሠራዊት ለጦርነት ተዘጋጅቶ በገለዓድ ሰፈረ፤ የእስራኤልም ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው በገለዓድ ምጽጳ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ሰፈሩ፤
18
በዚያም ሕዝቡና በገለዓድ የእስራኤላውያን የነገድ አለቆች ሁሉ “ዐሞናውያንን ስንወጋ መሪ የሚሆነን ማነው? ጦርነቱን የሚከፍት ሰው እርሱ በገለዓድ ለሚኖር ሰው ሁሉ መሪ ይሆናል” ተባባሉ።
← Chapter 9
Chapter 11 →