bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
/
Hebrews 8
Hebrews 8
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
1
እንግዲህ ከምንነጋገርባቸው ነገሮች ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማይ በልዑል እግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ የካህናት አለቃ አለን፤
2
እርሱ የሚያገለግለው እውነተኛ ድንኳን በሆነችው መቅደስ ነው፤ ይህች ድንኳን የተተከለችው በሰው እጅ ሳይሆን በጌታ ነው።
3
እያንዳንዱ የካህናት አለቃ የሚሾመው መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ ነው፤ ስለዚህ ይህም ካህን የሚያቀርበው አንድ ነገር ሊኖረው ያስፈልጋል።
4
በሕግ መሠረት መባን የሚያቀርቡ ካህናት ስላሉ እርሱ በምድር ቢሆን ኖሮ ካህን ባልሆነም ነበር፤
5
እነዚህ ካህናት የሚያገለግሉበት ድንኳን በሰማይ ለሚገኘው ምሳሌና ጥላ ብቻ ነው፤ ይህም የሆነው ሙሴ ድንኳኒቱን በሚሠራበት ጊዜ፤ እግዚአብሔር “በተራራው ላይ እንደ ተገለጠልህ ዐይነት ሁሉን ነገር በጥንቃቄ አድርግ” ብሎ ባዘዘው መሠረት ነው።
6
አሁን ግን ኢየሱስ አማካይ አስማሚ የሆነበት ቃል ኪዳን ከአሮጌው ቃል ኪዳን የበለጠና በተሻለ ተስፋ ላይ የተመሠረተ እንደ መሆኑ ለእርሱ የተሰጠው አገልግሎት የበለጠ ነው።
7
የመጀመሪያው ቃል ኪዳን ነቀፋ የሌለው ሆኖ ቢገኝ ኖሮ ሁለተኛው ቃል ኪዳን ባላስፈለገ ነበር።
8
እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ነቀፋ መኖሩን በማመልከት እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ ከእስራኤል ሕዝብና ከይሁዳ ሕዝብ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ጊዜ ይመጣል” ይላል ጌታ።
9
ይህም ቃል ኪዳን እጃቸውን ይዤ ከግብጽ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ቃል ኪዳን ያለ አይደለም፤ እነርሱ በቃል ኪዳኔ ስላልጸኑ እኔም ችላ አልኳቸው ይላል ጌታ።
10
“እነሆ፥ ከዚህ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን የሚከተለው ነው ይላል ጌታ፤ እኔ ሕጌን በአእምሮአቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።
11
‘ጌታን ዕወቅ’ ብሎ ጎረቤቱን ሆነ ወንድሙን የሚያስተምር ማንም አይኖርም፤ ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ ሁሉም ያውቀኛል፤
12
በደላቸውን ይቅር እልላቸዋለሁ፤ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስባቸውም።”
13
እንግዲህ “አዲስ ቃል ኪዳን” ሲል የፊተኛውን ቃል ኪዳን አሮጌ አድርጎታል ማለት ነው፤ ስለዚህ የተሠራበትና አሮጌው ነገር ሁሉ የሚጠፋበት ጊዜ ተቃርቧል።
← Chapter 7
Chapter 9 →