bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
/
Exodus 24
Exodus 24
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
1
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንተ ራስህ፥ አሮን፥ ናዳብ፥ አቢሁና ከእስራኤል መሪዎች ሰባ የሚሆኑት ጭምር እኔ ወዳለሁበት ተራራ ውጡ፤ በሩቅ ሳላችሁም ተንበርክካችሁ ስገዱ፤
2
ሙሴ ብቻ ወደ እኔ ይቅረብ፤ እነርሱ ግን አይቅረቡ፤ ሕዝቡም ከአንተ ጋር አይውጣ።”
3
ሙሴም ሄዶ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሥርዓት ሁሉ ለሕዝቡ ነገረ፤ ሕዝቡም በአንድነት “እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ እናደርጋለን” ሲል መለሰ።
4
ሙሴም የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ሁሉ ጻፈ፤ በማግስቱም ጠዋት በማለዳ በተራራው ሥር መሠዊያ ሠራ፤ ለእያንዳንዱም የእስራኤል ነገድ አንድ የድንጋይ ዐምድ አኖረ፤
5
የሚቃጠል መሥዋዕት ወስደው ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡ ወጣቶች ወንዶችን ላከ፤ እነርሱም ወይፈኖችን የአንድነት መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ።
6
ሙሴም ከእንስሶቹ ደም ከፊሉን ወስዶ በገበቴ ውስጥ አኖረው፤ እኩሌታውንም በመሠዊያው ፊት ረጨው።
7
ከዚህ በኋላ የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ወስዶ ድምፁን ከፍ በማድረግ ለሕዝቡ አነበበ፤ ሕዝቡም “ለእግዚአብሔር እንታዘዛለን እርሱ ያዘዘውንም ሁሉ እንፈጽማለን” አሉ።
8
ከዚህ በኋላ ሙሴ በገበቴ ያለውን ደም ወስዶ በሕዝቡ ላይ በመርጨት “ይህ እንግዲህ እግዚአብሔር እነዚህን ሁሉ ትእዛዞች በሰጣችሁ ጊዜ ከእናንተ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የሚያጸናበት ደም ነው” አለ።
9
ሙሴ፥ አሮን፥ ናዳብ፥ አቢሁና ከእስራኤልም መሪዎች ሰባዎቹ ወደ ተራራው ወጡ፤
10
የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ በእግሮቹ ሥር ከብሩህ ሰንፔር የተሠራና የሚያበራ ሰማይ የሚመስል ወለል ነበር።
11
እግዚአብሔር የእስራኤል መሪዎች የሆኑትን እነዚህን አረጋውያን ሰዎች አልቀሠፈም፤ ይልቁንም እግዚአብሔርን አይተው በፊቱ በሉ፤ ጠጡም።
12
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እኔ ወዳለሁበት ወደ ተራራው ወጥተህ በዚያ ቈይ፤ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችንም እሰጥሃለሁ፤ በእነርሱም ላይ ለሕዝቡ መመሪያዎች ይሆኑ ዘንድ እኔ የጻፍኳቸው ትእዛዞችና ኅጎች ይገኛሉ።”
13
ሙሴና አገልጋዩ ኢያሱ ተዘጋጁ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ፤
14
ሙሴም ለመሪዎቹ “እንደገና ወደ እናንተ ተመልሰን እስክንመጣ በዚህ ቈዩን፤ አሮንና ሑርም እነሆ፥ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ ስለዚህም በመካከላችሁ ጥልና ክርክር ያለበት ሰው ቢኖር ወደ እነርሱ ይሂድ” አላቸው።
15
ሙሴም ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ ተራራውንም ደመና ሸፈነው፤
16
የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ዐረፈ፤ ደመናውም ተራራውን ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው።
17
በተራራው ጫፍ ላይ የተገለጠው የእግዚአብሔር ክብር በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ እንደሚባላ እሳት ይታይ ነበር።
18
ሙሴም ወጥቶ በተራራው ላይ ወዳለው ደመና ውስጥ ገባ፤ እዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየ።
← Chapter 23
Chapter 25 →