bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
/
Deuteronomy 21
Deuteronomy 21
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
1
“እግዚአብሔር እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር በሜዳ ላይ ማን እንደ ገደለው ሳይታወቅ አንድ ሰው ተገድሎ ቢገኝ፤
2
በዚያን ጊዜ መሪዎችህና ዳኞችህ ሄደው አስከሬኑ ወድቆ ከተገኘበት ስፍራ አንሥተው ባቅራቢያ እስከምትገኘው እስከያንዳንዱ ከተማ ድረስ ርቀቱን ይለኩት፤
3
ከዚያም በኋላ አስከሬኑ ወድቆ ለተገኘበት ስፍራ ቅርብ ሆና የምትገኘው ከተማ መሪዎች ለሥራ ያልደረሰች፥ በጫንቃዋም ላይ ቀንበር ያልተጫነባት አንዲት ጊደር ይምረጡ፤
4
እርስዋንም ጨርሶ ወዳልታረሰና ምንም ተክል ወዳልተተከለበት፥ ወንዙም ወደማይደርቅበት ሸለቆ ይዘዋት ወርደው በዚያ አንገትዋን በመቈልመም ይስበሩት፤
5
እርሱን እንዲያገለግሉት፥ በእርሱ ስም እንዲባርኩ፥ የክርክርና የወንጀል ጉዳይ በእነርሱ እንዲወሰን አምላክህ እግዚአብሔር ካህናቱን የሌዊን ልጆች ስለ መረጣቸው ወደ አስከሬኑ ይቅረቡ።
6
ከዚህም በኋላ የተገደለው ሰው አስከሬን ወድቆ ለተገኘበት ስፍራ አቅራቢያ የሆነችው የዚያች ከተማ መሪዎች በጊደርዋ ላይ እጃቸውን ይታጠቡ፤
7
እንዲህም ብለው መግለጫ ይስጡ፦ ‘እኛ ይህን ሰው አልገደልንም፤ ማን እንደ ገደለውም አላየንም፤
8
እግዚአብሔር ሆይ፥ ከግብጽ ምድር ዋጅተህ ያወጣሃቸውን ሕዝብህን እስራኤልን ይቅር በል፤ እኛንም ይቅር በለን፤ ስለዚህም ስለ ፈሰሰው የንጹሕ ሰው ደም በኀላፊነት ተጠያቂዎች አታድርገን።’
9
በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛውን ነገር ስለምታደርግ ስለ ንጹሑ ሰው ግድያ ወንጀል ተጠያቂ አትሆንም።
10
“ጠላቶችህን ለመዋጋት ወጥተህ፥ እግዚአብሔር አምላክህ እነርሱን አሳልፎ ሲሰጥህና ስትማርካቸው
11
በእነርሱ መካከል ለጋብቻ የምትፈልጋት ውበት ያላት ሴት ታይ ይሆናል፤
12
ይህም ከሆነ፥ እርስዋን ወደ ቤትህ ወስደህ፥ ራስዋን ተላጭታ፥ ጥፍርዋን ተቈርጣ፥
13
ልብስዋን ትለውጥ፤ እርስዋም ከአንተ ጋር በቤትህ ተቀምጣ እስከ አንድ ወር ድረስ በጦርነት ስለሞቱት ወላጆችዋ ታልቅስ፤ ከዚያም በኋላ ሚስት አድርገህ ታገባታለህ።
14
በኋላ ግን የማትፈልጋት ከሆንህ ነጻ ልትለቃት ትችላለህ፤ ከአንተ ጋር የጋብቻ ግንኙነት እንድትፈጽም ያስገደድሃት ስለ ሆንክ ባሪያ አድርገህ ልትሸጣት አይገባም።
15
“አንድ ሰው ሁለት ሚስቶችን አግብቶ አንደኛይቱን አፍቅሮ ሌላይቱን ባያፈቅርና ሁለቱም ወንዶች ልጆችን ቢወልዱለት፥ ምናልባት የመጀመሪያው ልጅ የተወለደው ከማይወዳት ሚስቱ ቢሆን፥
16
ታዲያ፥ ያ ሰው ሀብቱንና ንብረቱን ለልጆቹ በሚያካፍልበት ጊዜ ለበኲር ልጁ ሊሰጥ የሚገባውን ድርሻ በተለይ ከሚያፈቅራት ሚስቱ ለተወለደው ልጁ በመስጠት አድልዎ ማድረግ አይገባውም፤
17
ከማያፈቅራት ሚስቱ የተወለደ ቢሆንም እንኳ ለበኲር ልጁ የሚሰጠው ድርሻ ከሌሎቹ የነፍስ ወከፍ ድርሻ በእጥፍ ከፍ ያለ መሆን አለበት፤ ስለዚህም ያ ሰው ልጁ በመጀመሪያ በመወለዱ በኲር መሆኑን ተረድቶ የብኲርና ድርሻውን ሊሰጠው ይገባል።
18
“አንድ ሰው ምንም ቢቀጡት የማይመለስ እልኸኛና ዐመፀኛ ሆኖ፥ ለወላጆቹ የማይታዘዝ ልጅ ይኖረው ይሆናል፤
19
ይህም ከሆነ ወላጆቹ በሚኖሩባት ከተማ አደባባይ ወዳሉት መሪዎች ዘንድ አምጥተው ለፍርድ ያቁሙት፤
20
በሚያስፈርዱበትም ጊዜ እንዲህ ይበሉ፥ ‘እነሆ፥ ይህ ልጃችን እልኸኛና ዐመፀኛ ነው፤ ለእኛ መታዘዝን እምቢ ብሎአል፤ ሰካራምና ገንዘብ አባካኝ ሆኖብናል፤’
21
የከተማይቱም ሰዎች ሁሉ በድንጋይ ወግረው ይግደሉት፤ በዚህም ዐይነት ይህን ክፉ ነገር ታስወግዳላችሁ፤ በእስራኤልም የሚኖር ሁሉ ይህን ሁኔታ ሰምቶ ይፈራል።
22
“አንድ ሰው በሠራው ከባድ ወንጀል ምክንያት በእንጨት በስቅላት ቢቀጣ፥
23
በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር የተረገመ ስለ ሆነ አስከሬኑ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ አይደር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በርስትነት የሚሰጥህን ምድር እንዳታረክስ አስከሬኑን በዚያኑ ዕለት ቅበረው።
← Chapter 20
Chapter 22 →