bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
/
2 Chronicles 17
2 Chronicles 17
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
1
ኢዮሣፍጥ በአባቱ በአሳ እግር ተተክቶ ነገሠ፤ እስራኤልንም ለመውጋት ኀይሉን አጠናከረ፤
2
በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞችና በየገጠሩ ሁሉ እንዲሁም አባቱ ንጉሥ አሳ ድል አድርጎ በያዛቸው በኤፍሬም ግዛት ባሉት ከተሞች ሁሉ ወታደሮቹን አሰፈረ፤
3
ኢዮሣፍጥ አባቱ በዘመነ መንግሥቱ መጀመሪያ ላይ የነበረውን የዳዊትን መልካም ምሳሌነት ስለ ተከተለና ባዓል ተብሎ የሚጠራውን ጣዖት ስላላመለከ እግዚአብሔር ባረከው፤
4
ኢዮሣፍጥ የአባቱን አምላክ የእግዚአብሔርን መመሪያ ተከተለ፤ ትእዛዞቹንም ጠበቀ፤ የእስራኤል ነገሥታት ያደርጉት የነበረውንም ዐይነት ክፉ ሥራ ከቶ አልፈጸመም፤
5
ስለዚህ እግዚአብሔር የኢዮሣፍጥ መንግሥት በይሁዳ ላይ እንዲጸና አደረገ፤ የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ልዩ ልዩ ገጸ በረከት ያመጡለት ስለ ነበረም እጅግ የበለጸገና የከበረ ሆነ፤
6
እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ አገለገለ፤ ከዚህም በላይ በኰረብቶች ላይ የሚገኙትን የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችንና በይሁዳ የነበሩትን አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስሎች ሁሉ ደመሰሰ።
7
ኢዮሣፍጥ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ቤንሐይል፥ አብድዩ፥ ዘካርያስ፥ ናትናኤልና ሚክያስ ተብለው የሚጠሩትን ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለሥልጣኖች በይሁዳ ከተሞች እንዲያስተምሩ ላካቸው።
8
ከእነርሱም ጋር ዘጠኝ ሌዋውያንና ሁለት ካህናት ነበሩ፤ ሌዋውያኑ ሸማዕያ፥ ነታንያ፥ ዘባድያ፥ ዐሣሄል፥ ሸሚራሞት፥ ይሖናታን፥ ኦዶኒያ፥ ጦቢያና ጦባዶኒያ ሲሆኑ ካህናቱ ደግሞ ኤሊሻማዕና ይሖራም ናቸው፤
9
እነርሱም የእግዚአብሔርን የሕግ መጽሐፍ ይዘው ወደ መላው የይሁዳ ከተሞች በመሄድ ለሕዝቡ ሁሉ አስተማሩ።
10
በይሁዳ ግዛት ዙሪያ የሚገኙ ነገሥታት በኢዮሣፍጥ ላይ ጦርነት ከማድረግ እንዲገቱ እግዚአብሔር ፍርሀት አሳደረባቸው፤
11
ከፍልስጥኤማውያን አንዳንዶቹ ብዙ ብርና ሌላም ዐይነት ስጦታ ለንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሲያበረክቱ፥ አንዳንድ ዐረቦች ደግሞ ሰባት ሺህ ሰባት መቶ በጎችና ሰባት ሺህ ሰባት መቶ ፍየሎች አመጡለት፤
12
ስለዚህ ኢዮሣፍጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ገናና እየሆነ ሄደ፤ በመላው ይሁዳ ምሽጎችንና፥ እጅግ የበዛ ስንቅና ትጥቅ የተከማቹባቸውን ከተማዎች ሠራ። በኢየሩሳሌምም የተለየ ችሎታ ያላቸውን ተዋጊዎች አኖረ፤
14
ከይሁዳ ነገድ ለተመለመሉት ወታደሮች አዛዥ ዐድና ተብሎ የሚጠራ የጦር መኰንን ነበር፤ በእርሱም ሥር ሦስት መቶ ሺህ ወታደሮች ነበሩ፤
15
ከእርሱም ቀጥሎ በማዕርግ ሁለተኛ የሆነው የሆሐናን ተብሎ የሚጠራ የጦር አዛዥ ነበር፤ በእርሱም ሥር ሁለት መቶ ሰማኒያ ሺህ ወታደሮች ነበሩ፤
16
ከይሆሐናን ቀጥሎ በማዕርግ ሦስተኛ የሆነው የጦር መኰንን የዚክሪ ልጅ ዐማሥያ ነበር፤ በእርሱም ሥር ሁለት መቶ ሺህ ወታደሮች ነበሩ፤ እርሱም በገዛ ፈቃዱ ራሱን ለእግዚአብሔር አገልግሎት የለየ የጦር አዛዥ ነበር፤
17
ከብንያም ነገድ ለተመለመሉት ወታደሮች ዋና አዛዥ ኤሊያዳዕ ተብሎ የሚጠራ ጀግና ወታደር ነበር፤ በእርሱም ሥር ጋሻና ቀስት የያዙ ሁለት መቶ ሺህ ወታደሮች ነበሩ፤
18
ከእርሱ ቀጥሎ በማዕርግ ሁለተኛ የሆነው የሆዛባድ ተብሎ የሚጠራ የጦር አዛዥ ነበር፤ በእርሱም ሥር ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ አንድ መቶ ሰማኒያ ሺህ ወታደሮች ነበሩ፤
19
እነዚህ ሁሉ ወታደሮች ንጉሥ ኢዮሣፍጥን በኢየሩሳሌም የሚያገለግሉ ሲሆኑ፥ በተጨማሪም ንጉሡ በሌሎቹ በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሌሎች ወታደሮችን አስፍሮ ነበር።
← Chapter 16
Chapter 18 →