bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
/
1 Samuel 27
1 Samuel 27
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
1
ዳዊት በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፤ “አንድ ቀን ሳኦል እኔን ይገድለኛል፤ እንግዲህ ለእኔ የሚበጀኝ ነገር አምልጬ ወደ ፍልስጥኤም መሄድ ነው፤ ከዚያም በኋላ ሳኦል በእስራኤል ምድር እኔን መፈለጉን ስለሚተው ከእጁ አመልጣለሁ።”
2
ስለዚህም ዳዊትና ስድስት መቶ ተከታዮቹ ወዲያውኑ ተነሥተው የጋት ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ ማዖክ ልጅ ወደ አኪሽ ሄዱ፤
3
ዳዊትና ተከታዮቹም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በጋት ተቀመጡ፤ ከዳዊትም ጋር ሁለቱ ሚስቶቹ አብረው ነበሩ፤ እነርሱም የኢይዝራኤል ተወላጅ የሆነችው አሒኖዓምና የቀርሜሎሱ ተወላጅ ናባል አግብቶአት የነበረው አቢጌል ነበሩ፤
4
ሳኦልም ዳዊት ወደ ጋት ሸሽቶ መሄዱን በሰማ ጊዜ እርሱን ፈልጎ ለማግኘት ያደርገው የነበረውን ሙከራ ሁሉ አቆመ።
5
ዳዊትም ንጉሥ አኪሽን “የምትወደኝ ከሆንክ በአንድ ትንሽ ከተማ እንድኖር ፍቀድልኝ፤ ጌታዬ ሆይ፥ እኔ በመናገሻ ከተማ ከአንተ ጋር መኖር አይገባኝም” አለው።
6
ስለዚህም አኪሽ የጺቅላግን ከተማ ለዳዊት ሰጠው፤ በዚህም ምክንያት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጺቅላግ የይሁዳ ነገሥታት ይዞታ እንደ ሆነች ቀረች።
7
በዚህ ዐይነት ዳዊት በፍልስጥኤም አንድ ዓመት ከአራት ወር ተቀመጠ።
8
በዚያን ጊዜ ውስጥ ዳዊትና ተከታዮቹ በጌሪሹራውያን፥ በጌዛውያንና በአማሌቃውያን ላይ ዘመቱ፤ እነዚህም አገሮች ከቴሌኦም ጀምሮ ወደ ሱርና ወደ ምድረ ግብጽ የሚወስዱ እነርሱ የሚኖሩባቸው አገሮች ነበሩ።
9
ወንዶችንም ሴቶችንም ሁሉ እየገደለ፥ በጎችን የቀንድ ከብቶችን፥ አህዮችን፥ ግመሎችንና ልብሱንም ሁሉ ይወስድ ነበር፤ ከዚያም በኋላ ዳዊት ወደ አኪሽ ተመለሰ፤
10
አኪሽ “በዚህ ጊዜ ወረራ ያደረጋችኹት በየት በኩል ነው” ብሎ ሲጠይቀው ዳዊት “እኛ የዘመትነው ከይሁዳ በስተ ደቡብ ባለው ክፍል፥ እንደገናም በይራሕመኤል ነገድ ግዛትና ቄናውያን በሚኖሩበት ግዛት ነው” እያለ ይመልስለት ነበር።
11
ዳዊት ወንድንም ሆነ ሴትን ወደ ጋት ሳያመጣ ሁሉንም ገደለ። ይህንንም ያደረገው ዳዊት ይህንንና ይህንን አደረገ ብለው እንዳይነግሩበት ነው። በፍልስጥኤም አገር በኖረበት ዘመን ሁሉ ይህን የማድረግ ልማድ ነበረው።
12
አኪሽ ግን ዳዊትን ስለሚተማመንበት በልቡ “በወገኖቹ በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ የተጠላ ስለ ሆነ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ያገለግለኛል” በማለት ያስብ ነበር።
← Chapter 26
Chapter 28 →