bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
/
1 Samuel 11
1 Samuel 11
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
1
ከአንድ ወር በኋላ የዐሞን ንጉሥ ናዖስ በገለዓድ ግዛት በምትገኘው በያቤሽ ከተማ ላይ ሠራዊቱን በማዝመት ከበባት፤ የያቤሽም ሰዎች ናዖስን “ከእኛ ጋር የውል ስምምነት አድርግ፤ እኛም የአንተ አገልጋዮች እንሆናለን” አሉት።
2
ናዖስም “ከእናንተ ጋር የውል ስምምነት ማድረግ የምችልበት አንድ ዐይነት ግዴታ አለ፤ ይኸውም የእያንዳንዱን ሰው ቀኝ ዐይን በማውጣት በእስራኤላውያን ላይ አሳፋሪ ውርደት አመጣለሁ” ሲል መለሰላቸው።
3
የያቤሽ መሪዎችም “ወደ መላው የእስራኤል ምድር መልእክተኞች እስክንልክ ድረስ የሰባት ቀን ጊዜ ስጠን፤ እኛን የሚታደገን ካጣን ለአንተ እጃችንን እንሰጣለን” አሉት።
4
መልእክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ ደረሱ፤ ወሬውንም በተናገሩ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ።
5
ሳኦል በዚህ ጊዜ ጥንድ በሬዎቹን ይዞ ከዋለበት እርሻ በመመለስ ላይ ነበር፤ እርሱም “ምንድን ነው ነገሩ? ሰው ሁሉ የሚያለቅሰው ስለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ፤ እነርሱም ከያቤሽ የመጡ መልእክተኞች የሚሉትን ወሬ ነገሩት።
6
ሳኦልም ይህን በሰማ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ በኀይል ወረደ፤ የሳኦልም ቊጣ እጅግ ገነፈለ።
7
ጥንዱንም በሬዎች ወስዶ ቈራረጣቸው፤ የሥጋውንም ቊራጭ ሁሉ አስይዞ “ሳኦልንና ሳሙኤልን ተከትሎ ወደ ጦርነት የማይወጣ ሰው ቢኖር በሬዎቹ እንደዚህ ይቈራረጡበታል!” ከሚል ማስጠንቀቂያ ጋር መልእክተኞችን ወደ መላው የእስራኤል ምድር ላከ። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን ፈራ፤ አንድም ሰው ሳይቀር ሁሉም በአንድነት ወጡ።
8
ሳኦልም ቤዜቅ በተባለ ስፍራ ሰበሰባቸው፤ የቊጥራቸውም ብዛት ከእስራኤል የመጡት ሦስት መቶ ሺህ ሲሆን ከይሁዳ የመጡት ሠላሳ ሺህ ነበር።
9
ከያቤሽ የመጡትንም መልእክተኞች “ነገ ከቀትር በፊት የምናድናቸው መሆኑን ለሕዝባችሁ ንገሩ” አሉአቸው። መልእክቱንም ለያቤሽ ሰዎች በነገሩ ጊዜ የያቤሽ ሰዎች እጅግ ተደሰቱ።
10
የያቤሽም ሰዎች አሞናውያንን “ነገ እጃችንን ለእናንተ እንሰጣለን እናንተም በእኛ ላይ የምትፈልጉትን አድርጉ” አሉአቸው።
11
በማግስቱ ሳኦል ሕዝቡን በሦስት ከፈለ፤ ከማለዳ ጀምሮ ባለው ጊዜ በአሞናውያን ሰፈር ላይ አደጋ ጥለው ፀሐይ እስኪሞቅ ድረስ ፈጁአቸው፤ ከእልቂት የተረፉትም ተበታትነው ለየብቻቸው ሸሹ።
12
ከዚህ በኋላ ሕዝቡ ሳሙኤልን “ሳኦል በእኛ ላይ አይነግሥብንም ያሉት ሰዎች እነማን ናቸው? እነርሱን አሳልፈህ ስጠንና እንግደላቸው!” አሉት።
13
ሳኦል ግን “በዛሬው ቀን እግዚአብሔር እስራኤልን ስላዳነ ማንም ሰው መገደል የለበትም” አለ።
14
ሳሙኤልም “ሁላችንም ወደ ጌልጌላ እንሂድና ሳኦል ንጉሣችን መሆኑን እንደገና በይፋ እናረጋግጥ” አላቸው።
15
ሕዝቡም ሁሉ ወደ ጌልጌላ ሄደው በእግዚአብሔር ፊት የሳኦልን ንጉሥነት አጸደቁ፤ በእግዚአብሔርም ፊት የአንድነት መሥዋዕት አቀረቡ፤ በዓሉንም ሳኦልና መላው ሕዝብ በታላቅ ደስታ አከበሩት።
← Chapter 10
Chapter 12 →