bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
/
1 Kings 17
1 Kings 17
Amharic New Standard Translation (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 2005
1
በገለዓድ የምትገኘው የቱቢ ተወላጅ የሆነውና ኤልያስ ተብሎ የሚጠራው ነቢይ፤ ንጉሥ አክዓብን “በእኔ ቃል ካልሆነ በቀር በሚቀጥሉት ዓመቶች በምድር ላይ ጠል ወይም ዝናብ እንደማይኖር እኔ በማገለግለው በእስራኤል አምላክ፥ በሕያው እግዚአብሔር ስም እነግርሃለሁ” አለው።
2
ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ፤
3
“ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፤ እዚያም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ከሪት ተብሎ በሚጠራው ሸለቆ ተሸሸግ፤
4
የምትጠጣውንም ውሃ ከዚያው ወንዝ ታገኛለህ፤ ቊራዎችም ምግብ እንዲያመጡልህ አዝዣለሁ።”
5
ኤልያስም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ሄዶ በከሪት ሸለቆ ተቀመጠ፤
6
ከወንዙም ውሃ ጠጣ፤ ቊራዎችም ዘወትር ጧትና ማታ እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤
7
ዝናብ ጠፍቶ ድርቅ ከመሆኑ የተነሣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያ ወንዝ ደረቀ።
8
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ኤልያስን እንዲህ አለው፤
9
“እንግዲህ አሁን ከዚህ ተነሥተህ ሂድና በሲዶና በምትገኘው በስራጵታ ከተማ ተቀመጥ፤ እነሆ በዚያ የምትኖር አንዲት መበለት እንድትመግብህ አዝዣለሁ” አለው።
10
ስለዚህ ኤልያስ ወደ ሰራጵታ ሄደ፤ ወደ ከተማይቱም ቅጽር በር በደረሰ ጊዜ አንዲት ባልዋ የሞተባት ሴት እንጨት ስትለቅም አይቶ “እባክሽ የምጠጣው ውሃ አምጪልኝ” አላት።
11
ውሃም ልታመጣለት በመሄድ ላይ ሳለች ወዲያውኑ ጠርቶ “እባክሽ በተጨማሪ ትንሽ እንጀራ አምጪልኝ” አላት።
12
እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰችለት፤ “ምንም እንጀራ እንደሌለኝ በአምላክህ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ በዱቄት ዕቃዬ ውስጥ ካለችው ከአንድ እፍኝ ዱቄትና በማሰሮዬ ውስጥ ካለችው ከጥቂት የወይራ ዘይት በቀር ምንም የለኝም፤ ወደዚህ የመጣሁት ትንሽ እንጨት ለቃቅሜ ወደ ቤቴ በመመለስ ይህችኑ ያለችኝን ትንሽ ዱቄት ለልጄና ለእኔ ለመጋገር ነው፤ ይህችም የመጨረሻ ምግባችን ናት፤ ከዚያም በኋላ በራብ ከመሞት አንተርፍም።”
13
ኤልያስም እንዲህ አላት፤ “አይዞሽ አትጨነቂ! ሄደሽ ምግብሽን አዘጋጂ፤ አስቀድመሽ ግን ከዚያችው ካለችሽ ዱቄት ለእኔ ትንሽ እንጐቻ ጋግረሽ አምጪልኝ፤ የቀረውንም ለራስሽና ለልጅሽ ጋግሪው፤
14
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ‘እኔ እግዚአብሔር ዝናብን እስከማወርድ ድረስ ዱቄቱ ከማኖሪያው ዕቃ፥ ዘይቱም ከማሰሮው ከቶ አያልቅም’ ሲል ተናግሮአል።”
15
እርስዋም ሄዳ ኤልያስ እንደ ነገራት አደረገች፤ በዚህም ዐይነት እርስዋ፥ ቤተሰብዋና ኤልያስም ለብዙ ቀን የሚሆን በቂ ምግብ አገኙ።
16
እግዚአብሔር በኤልያስ አማካይነት በሰጠው ተስፋ መሠረት ዱቄቱ ከማኖሪያው ዕቃ፥ ዘይቱም ከማሰሮው አላለቀም።
17
ከጥቂት ጊዜም በኋላ የዚያች ባልዋ የሞተባት ሴት ልጅ ታመመ፤ ሕመሙም እየባሰበት ስለ ሄደ በመጨረሻ ሞተ፤
18
እርስዋም ኤልያስን “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ስለምን ይህን አደረግህብኝ? ወደዚህ የመጣኸው ኃጢአቴን አስታውሰህ ልጄ እንዲሞትብኝ ለማድረግ ነውን?” ስትል ጠየቀችው።
19
ኤልያስም “ልጅሽን ወደ እኔ አምጪው” አላት። ልጁንም ከዕቅፍዋ ወስዶ እርሱ ወደሚኖርበት ሰገነት አውጥቶ በአልጋው ላይ አጋደመው፤
20
ከዚህ በኋላ ኤልያስ ድምፁን ከፍ በማድረግ “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! ስለምን በዚህች ባልዋ በሞተባት ሴት ላይ ይህን የመሰለ አሠቃቂ ነገር አደረግህ? እርስዋ እኔን በማስተናገድ ታላቅ ቸርነት አድርጋልኛለች፤ ታዲያ አንተ ስለምን ልጅዋ እንዲሞት አደረግህ?” ሲል ጸለየ።
21
ከዚህ በኋላ ኤልያስ በልጁ ላይ ሦስት ጊዜ ተዘርሮ “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! እባክህ ይህን ልጅ ከሞት አስነሣው!” ሲል ጸለየ።
22
እግዚአብሔርም የኤልያስን ጸሎት ሰማ፤ የልጁም እስትንፋስ እንደገና ተመልሶለት ዳነ።
23
ኤልያስ ልጁን ከሰገነት ወደ ምድር ቤት አውርዶ ለእናቱ በመስጠት “ተመልከቺ፤ እነሆ ልጅሽ ከሞት ወደ ሕይወት ተመልሶአል!” አላት።
24
እርስዋም “እነሆ አንተ የእግዚአብሔር ሰው መሆንህንና እግዚአብሔርም በአንተ አማካይነት መናገሩን አሁን አረጋገጥኩ!” ስትል መለሰችለት።
← Chapter 16
Chapter 18 →