bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Romans 13
Romans 13
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምት መገዛት ይገባዋል፤ ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለሥልጣናት በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው።
2
ስለዚህ፣ በባለ ሥልጣን ላይ የሚያምፅ በእግዚአብሔር ሥርዐት ላይ ማመፁ ነው፤ ይህን የሚያደርጉትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ።
3
ገዦች ክፉ ለሚሠሩ እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና። ባለሥልጣንን እንዳትፈራ ትፈልጋለህን? እንግዲያስ መልካሙን አድርግ፤ እርሱም ያመሰግንሃል፤
4
እርሱ ለአንተ መልካሙን ለማድረግ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። ነገር ግን ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ምክንያቱም ሰይፉን በከንቱ አልታጠቀም፤ ክፉ የሚያደርገውን ለመቅጣት የቍጣ መሣሪያ የሆነ፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው።
5
ስለዚህም ቅጣትን በመፍራት ብቻ ሳይሆን፣ ለኅሊና ሲባል ለባለሥልጣናት መገዛት ተገቢ ነው።
6
ግብር የምትከፍሉትም ደግሞ ለዚህ ነው፤ ባለሥልጣናቱ፣ በዚሁ ተግባር ላይ የተሰማሩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና፤
7
ለእያንዳንዱ የሚገባውን ስጡ፤ ግብር ከሆነ ግብርን፣ ቀረጥ ከሆነም ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባውም ክብርን ስጡ።
8
እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር የማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ባልንጀራውን የሚወድድ እርሱ ሕግን ፈጽሟልና።
9
“አታመንዝር”፣ “አትግደል”፣ “አትስረቅ”፣ “አትመኝ” የሚሉትና ሌሎችም ትእዛዞች ቢኖሩም፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” በሚለው በዚህ በአንድ ሕግ ተጠቃልለዋል።
10
ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ መፈጸሚያ ነው።
11
ዘመኑን በማስተዋል ይህን አድርጉ፤ ከእንቅልፋችሁ የምትነቁበት ጊዜ አሁን ነው፤ መዳናችን መጀመሪያ ካመንበት ጊዜ ይልቅ አሁን ወደ እኛ ቀርቧልና።
12
ሌሊቱ ሊያልፍ፣ ቀኑም ሊጀምር ነው። ስለዚህ የጨለማን ሥራ ጥለን፣ የብርሃንን ጦር ዕቃ እንልበስ።
13
በቀን እንደምንመላለስ በአግባብ እንመላለስ። በጭፈራና በስካር አይሁን፤ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፤ በክርክርና በቅናትም አይሁን።
14
ይልቁንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም ይፈጽም ዘንድ ለሥጋ በዐሳባችሁ አትመቻቹለት።
← Chapter 12
Chapter 14 →