bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Revelation 9
Revelation 9
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
አምስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ከሰማይ ወደ ምድር የወደቀውንም ኮከብ አየሁ፤ ኮከቡም የጥልቁ ጕድጓድ መክፈቻ ተሰጠው።
2
ጥልቁን ጕድጓድ በከፈተውም ጊዜ፣ ከውስጡ ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ያለ ጢስ ወጣ። ከጕድጓዱም በወጣው ጢስ ፀሓይና ሰማይ ጨለሙ።
3
ከጢሱም አንበጦች ወጥተው በምድር ላይ ወረዱ፤ እንደ ምድር ጊንጦች ሥልጣን ያለ ሥልጣን ተሰጣቸው።
4
እነርሱም የምድርን ሣር ወይም ማናቸውንም የለመለመ ተክል ወይም ዛፍ እንዳይጐዱ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ማኅተም በግምባራቸው ላይ የሌለባቸውን ሰዎች ብቻ እንዲጐዱ ተነገራቸው።
5
እነርሱንም አምስት ወር ብቻ እንዲያሠቃዩአቸው እንጂ እንዲገድሏቸው ሥልጣን አልተሰጣቸውም፤ የሚሠቃዩትም ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ሲነድፍ እንደሚሰማው ዐይነት ሥቃይ ነው።
6
በእነዚያ ቀኖች ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አያገኙትም፤ ለመሞትም ይመኛሉ፤ ነገር ግን ሞት ከእነርሱ ይሸሻል።
7
አንበጦቹ ለጦርነት የተዘጋጁ ፈረሶች ይመስሉ ነበር፤ በራሳቸውም ላይ የወርቅ አክሊል የመሰለ ነገር ደፍተዋል፤ ፊታቸውም የሰው ፊት ይመስል ነበር፤
8
ጠጕራቸው የሴት ጠጕር፣ ጥርሳቸውም የአንበሳ ጥርስ ይመስል ነበር።
9
የብረት ጥሩር የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የክንፎቻቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት የሚገሠግሡ የብዙ ፈረሶችና ሠረገሎች ድምፅ ይመስል ነበር።
10
እንደ ጊንጥም ያለ፣ ጅራትና መንደፊያ ነበራቸው፤ ደግሞም ሰዎችን አምስት ወር የሚያሠቃዩበት ኀይል በጅራታቸው ላይ ነበር።
11
በላያቸው ንጉሥ ነበራቸው፤ እርሱም የጥልቁ ጕድጓድ መልአክ ነው፤ ስሙም በዕብራይስጥ “አብዶን”፣ በግሪክ ደግሞ “አጶልዮን” ይባላል።
12
የመጀመሪያው ወዮ ዐልፏል፤ እነሆ፤ ከዚህ በኋላ ገና ሌላ ሁለት ወዮዎች ይመጣሉ።
13
ስድስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በእግዚአብሔር ፊት ካለው በወርቅ ከተሠራው መሠዊያ ቀንዶች ድምፅ ሲመጣ ሰማሁ፤
14
ድምፁም መለከት የያዘውን ስድስተኛውን መልአክ፣ “በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው” አለው።
15
ከሰው ዘር አንድ ሦስተኛውን እንዲገድሉ፣ ለዚህች ሰዓትና ዕለት እንዲሁም ለዚህች ወርና ዓመት ተዘጋጅተው የነበሩት አራቱ መላእክት ተፈቱ።
16
የፈረሰኛው ሰራዊት ብዛት ሁለት መቶ ሚሊዮን ነበር፤ ቍጥራቸውንም ሰማሁ።
17
በራእዬ ያየኋቸው ፈረሶችና በላያቸውም የተቀመጡት ይህን ይመስሉ ነበር፤ ጥሩራቸው እንደ እሳት ቀይ፣ እንደ ያክንት ሰማያዊና እንደ ዲን ብጫ ነበር፤ የፈረሶቹ ራስ የአንበሶችን ራስ ይመስል ነበር። ከአፋቸውም እሳትና ጢስ፣ ዲንም ይወጣ ነበር።
18
ከአፋቸው በወጡት፣ በሦስቱ መቅሠፍቶች፣ ማለት በእሳቱ፣ በጢሱና በዲኑ አንድ ሦስተኛው የሰው ዘር ተገደለ።
19
የፈረሶቹ ኀይል በአፋቸውና በጅራታቸው ላይ ነበር፤ ጅራታቸውም እባብ ይመስል ነበር፤ ራስ ስላላቸው ጕዳት የሚያደርሱት በእርሱ ነበር።
20
በእነዚህ መቅሠፍቶች ሳይገደሉ የቀሩት ሰዎች አሁንም ከእጃቸው ሥራ ንስሓ አልገቡም፤ አጋንንትን እንዲሁም ማየት ወይም መስማት ወይም መሄድ የማይችሉትን፣ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከናስ፣ ከድንጋይና ከዕንጨት የተሠሩትን ጣዖቶች ማምለክ አልተዉም፤
21
ደግሞም ከነፍስ ግድያቸው፣ ከጥንቈላ ሥራቸው፣ ከዝሙት ርኩሰታቸው ወይም ከስርቆት ተግባራቸው ንስሓ አልገቡም።
← Chapter 8
Chapter 10 →