bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Revelation 5
Revelation 5
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው በውስጥና በውጭ በኩል የተጻፈበት፣ በሰባት ማኅተም የታሸገ ጥቅልል መጽሐፍ በቀኝ እጁ ይዞ አየሁ።
2
አንድ ብርቱ መልአክ በታላቅ ድምፅ፣ “ማኅተሞቹን ለመፍታትና መጽሐፉን ለመክፈት የተገባው ማን ነው?” ብሎ ሲያውጅ አየሁ።
3
ነገር ግን በሰማይም ሆነ በምድር፣ ከምድርም በታች መጽሐፉን ለመክፈት ወይም ገልጦ ለመመልከት የሚችል ማንም አልነበረም።
4
እኔም መጽሐፉን ለመክፈት ወይም ገልጦ ለመመልከት የተገባው ማንም ባለመኖሩ እጅግ አለቀስሁ።
5
ከዚያም ከሽማግሌዎቹ አንዱ፣ “አታልቅስ፤ እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣ የዳዊት ሥር ድል ነሥቷል፤ እርሱ መጽሐፉን ሊከፍትና ሰባቱንም ማኅተሞች ሊፈታ ይችላል” አለኝ።
6
ከዚያም በዙፋኑና በአራቱ ሕያዋን ፍጡራን፣ በሽማግሌዎቹም መካከል የታረደ የሚመስል በግ ቆሞ አየሁ፤ በጉም ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዐይኖች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩት ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።
7
እርሱም መጥቶ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ቀኝ እጅ መጽሐፉን ወሰደ።
8
መጽሐፉን በወሰደ ጊዜ አራቱ ሕያዋን ፍጡራን፣ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችም በበጉ ፊት በግንባራቸው ተደፉ፤ እያንዳንዳቸውም የቅዱሳን ጸሎት የሆኑትን በገናና ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ሙዳይ ይዘው ነበር።
9
እንዲህም እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ፤ “መጽሐፉን ልትወስድ፣ ማኅተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ታርደሃል፤ በደምህም ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል።
10
ለአምላካችንም መንግሥትና ካህናት አድርገሃቸዋል፤ እነርሱም በምድር ላይ ይነግሣሉ።”
11
ከዚያም ተመለከትሁ፤ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም ሺሕ ጊዜ ሺሕና እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ። እነርሱም በዙፋኑና በሕያዋን ፍጡራኑ፣ በሽማግሌዎቹም ዙሪያ ከብበው ነበር፤
12
በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብለው ዘመሩ፤ “የታረደው በግ ኀይልና ባለጠግነት፣ ጥበብና ብርታት፣ ክብርና ሞገስ፣ ምስጋናም፣ ሊቀበል ይገባዋል።”
13
ከዚያም በሰማይና በምድር፣ ከምድር በታችና በባሕር፣ በእነርሱ ውስጥ ያሉ ፍጡራንም ሁሉ እንዲህ ብለው ሲዘምሩ ሰማሁ፤ “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለበጉ፣ ምስጋናና ሞገስ፣ ክብርና ኀይል፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን!”
14
አራቱ ሕያዋን ፍጡራንም፣ “አሜን!” አሉ፤ ሽማግሌዎቹም በግምባራቸው ተደፍተው ሰገዱ።
← Chapter 4
Chapter 6 →