bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Revelation 12
Revelation 12
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ታላቅና አስደናቂ ምልክት በሰማይ ታየ፤ ፀሓይን የለበሰች፣ ጨረቃን ከእግሮቿ በታች የረገጠችና በራሷም ላይ ዐሥራ ሁለት ከዋክብት ያሉት አክሊል የደፋች አንዲት ሴት ታየች።
2
እርሷም ነፍሰ ጡር ነበረች፤ ልትወልድ ስትል ምጥ ይዟት ተጨንቃ ጮኸች።
3
ከዚያም ሌላ ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆ፤ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች የነበሩት፣ በራሶቹም ላይ ሰባት አክሊል የደፋ ታላቅ ቀይ ዘንዶ ታየ።
4
ጅራቱ የከዋክብትን አንድ ሦስተኛ ከሰማይ ስቦ ወደ ምድር ጣላቸው፤ እርሷም በወለደች ጊዜ ልጇን ለመዋጥ ፈልጎ ዘንዶው ልትወልድ በተቃረበችው ሴት ፊት ቆመ።
5
ሕዝቦችን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጇም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።
6
ሴቲቱም አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ስድሳ ቀን ክብካቤ እንዲደረግላት እግዚአብሔር ወዳዘጋጀላት ስፍራ ወደ በረሓ ሸሸች።
7
በሰማይም ጦርነት ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም መልሰው ተዋጓቸው፤
8
ነገር ግን ድል ተመቱ፤ በሰማይም የነበራቸውን ስፍራ ዐጡ።
9
ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።
10
ከዚህ በኋላ ታላቅ ድምፅ በሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “አሁን የአምላካችን ማዳን፣ ኀይልና መንግሥት፣ የእርሱ ክርስቶስ ሥልጣንም መጥቷል። ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት ሲከስሳቸው የነበረው፣ የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሏልና።
11
እነርሱም በበጉ ደም፣ በምስክርነታቸውም ቃል፣ ድል ነሡት፤ እስከ ሞት ድረስ እንኳ፣ ለነፍሳቸው አልሳሱም።
12
ስለዚህ ሰማያት ሆይ፣ በውስጣቸውም የምትኖሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ፣ በታላቅ ቍጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።”
13
ዘንዶው ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ፣ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት።
14
ሴቲቱም በበረሓ ወደ ተዘጋጀላት ስፍራ በርራ መሄድ እንድትችል ሁለት የታላቁ ንስር ክንፎች ተሰጣት፤ ይህም የሆነው በዚያ ከእባቡ ፊት ርቃ ለአንድ ዘመን፣ ለዘመናትና ለዘመን እኩሌታ በክብካቤ እንድትኖር ነው።
15
እባቡም ሴቲቱ በጐርፍ እንድትወሰድ፣ እንደ ወንዝ ያለ ውሃ ከአፉ ተፋ።
16
ምድር ግን ሴቲቱን ረዳቻት፤ አፏንም ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠች።
17
ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጣ፤ ከቀሩት ልጆቿም ጋር ሊዋጋ ሄደ፤ እነርሱ የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው የያዙ ናቸው።
← Chapter 11
Chapter 13 →