bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Proverbs 25
Proverbs 25
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እነዚህ የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ሰዎች የቀዷቸው ሌሎች የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው፦
2
ነገርን መሰወር ለእግዚአብሔር ክብሩ ነው፤ ነገርን ፈልፍሎ ማውጣት ግን ለነገሥታት ክብራቸው ነው።
3
ሰማያት ከፍ ያሉ እንደ ሆኑ፣ ምድርም ጥልቅ እንደ ሆነች ሁሉ፣ የነገሥታትም ልብ እንደዚሁ አይመረመርም።
4
ከብር ዝገትን አስወግድ፤ አንጥረኛውም ንጹሕ ነገር ያገኛል፤
5
ክፉን ከንጉሥ ፊት አርቅ፤ ዙፋኑም በጽድቅ ትጸናለች።
6
በንጉሥ ፊት ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ፤ በታላላቆች መካከል መገኘትም አይመርህ፤
7
በትልቅ ሰው ፊት ከሚያዋርድህ፣ ራሱ፣ “ወደዚህ ከፍ በል” ቢልህ ይሻላልና። በዐይንህ ያየኸውን ሁሉ፣
8
ወደ ፍርድ አደባባይ በችኰላ አታውጣው፤ ባልንጀራህ ካሳፈረህ፣ ኋላ ምን ይውጥሃል?
9
ስለ ራስህ ጕዳይ ከባልንጀራህ ጋር በምትከራከርበት ጊዜ፣ የሌላውን ሰው ምስጢር አታውጣ፤
10
ያለዚያ ይህን የሚሰማ ያሳፍርሃል፤ አንዴ የጠፋውን ስምህንም ፈጽሞ መመለስ አትችልም።
11
ባግባቡ የተነገረ ቃል፣ በብር መደብ ላይ እንደ ተቀረጸ የወርቅ እንኮይ ነው።
12
የጠቢብ ሰው ዘለፋ ለሚሰማ ጆሮ፣ እንደ ወርቅ ጕትቻ ወይም እንደ ጥሩ የወርቅ ጌጥ ነው።
13
በመከር ጊዜ የበረዶ ቅዝቃዜ ለሰስ እንደሚያደርግ ሁሉ፣ ታማኝ መልእክተኛም ለላኩት እንደዚሁ ነው፤ የጌቶቹን መንፈስ ያሳርፋልና።
14
የማይለግሰውን ስጦታ እቸራለሁ ብሎ ጕራ የሚነዛ ሰው፣ ዝናብ እንደሌለው ደመናና ነፋስ ነው።
15
በትዕግሥት ገዥን ማግባባት ይቻላል፤ ለስላሳ አንደበትም ዐጥንት ይሰብራል።
16
ማር ስታገኝ በልክ ብላ፤ ከበዛ ያስመልስሃል።
17
ወደ ባልንጀራህ ቤት እግር አታብዛ፤ ታሰለቸውና ይጠላሃል።
18
በባልንጀራው ላይ በሐሰት የሚመሰክር፣ እንደ ቈመጥ፣ እንደ ሰይፍና እንደ ተሳለ ፍላጻ ነው።
19
በመከራ ጊዜ በወስላታ ሰው መተማመን፣ በተበላሸ ጥርስና በሰለለ እግር እንደ መታመን ነው።
20
ላዘነ ልብ የሚዘምር፣ በብርድ ቀን ልብሱን እንደሚያወልቅ፣ ወይም በሶዳ ላይ እንደ ተጨመረ ሆምጣጤ ነው።
21
ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማም ውሃ አጠጣው።
22
ይህን በማድረግህም፣ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ፤ እግዚአብሔርም ዋጋህን ይከፍልሃል።
23
የሰሜን ነፋስ ዝናብ እንደሚያመጣ ሁሉ፣ ሐሜተኛ ምላስም ቍጡ ፊት ታስከትላለች።
24
ከጨቅጫቃ ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖር፣ በጣራ ማእዘን ላይ መኖር ይሻላል።
25
ከሩቅ የሚመጣ መልካም ዜና፣ የተጠማችን ነፍስ እንደሚያረካ ቀዝቃዛ ውሃ ነው።
26
ለክፉ ሰው የሚንበረከክ ጻድቅ፣ እንደ ደፈረሰ ምንጭ ወይም እንደ ተበከለ የጕድጓድ ውሃ ነው።
27
ከመጠን በላይ ማር መብላት ጥሩ አይደለም፤ የራስንም ክብር መሻት አያስከብርም።
28
ራሱን የማይቈጣጠር ሰው፣ ቅጥሯ እንደ ፈረሰ ከተማ ነው።
← Chapter 24
Chapter 26 →