bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Proverbs 23
Proverbs 23
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከገዥ ጋር ለመብላት በምትቀመጥበት ጊዜ፣ በፊትህ ያለውን በሚገባ አስተውል፤
2
ስግብግብም ብትሆን እንኳ፣ በጕረሮህ ላይ ካራ አጋድምበት፤
3
የእርሱ ጣፋጭ መብል አያስጐምጅህ፤ ምግቡ አታላይ ነውና።
4
ሀብት ለማግኘት ስትል ራስህን አታድክም፤ ሐሳብህን የመግታት ጥበብ ይኑርህ።
5
በሀብት ላይ ዐይንህን ብትጥል፣ ወዲያው ይጠፋል፤ ወደ ሰማይ እንደሚበርር ንስር፣ በርግጥ ክንፍ አውጥቶ ይበርራል።
6
የሥሥታምን ምግብ አትብላ፤ ጣፋጭ መብሉም አያስጐምጅህ፤
7
ሁልጊዜ ስለ ዋጋ የሚያሰላ ሰው ነውና፤ “ብላ፣ ጠጣ” ይልሃል፤ ልቡ ግን ከአንተ ጋር አይደለም።
8
የበላሃት ትንሿ እንኳ ታስመልስሃለች፤ የምስጋና ቃልህንም ከንቱ ታደርጋለህ።
9
ከጅል ጋር አትነጋገር፤ የቃልህን ጥበብ ያንኳስሳልና።
10
የጥንቱን የወሰን ምልክት አታፋልስ፤ አባት የሌላቸውንም ልጆች መሬት አትግፋ፤
11
ታዳጊያቸው ብርቱ ነውና፤ እርሱ ይፋረድላቸዋል።
12
ልብህን ለምክር፣ ጆሮህንም ለዕውቀት ቃል ስጥ።
13
ልጅን ከመቅጣት ወደ ኋላ አትበል፤ በአርጩሜ ብትገርፈው አይሞትም።
14
በአርጩሜ ቅጣው፤ ነፍሱንም ከሞት አድናት።
15
ልጄ ሆይ፤ ልብህ ጠቢብ ቢሆን፣ የእኔም ልብ ሐሤት ያደርጋል፤
16
ከንፈሮችህ ትክክሉን ቢናገሩ፣ ውስጣዊ ሁለንተናዬ ሐሤት ያደርጋል።
17
ልብህ በኀጢአተኞች አይቅና፤ ነገር ግን ዘወትር እግዚአብሔርን ለመፍራት ትጋ።
18
ለነገ ርግጠኛ አለኝታ ይኖርሃል፤ ተስፋህም ከንቱ አይሆንም።
19
ልጄ ሆይ አድምጥ፤ ጠቢብም ሁን፤ ልብህም ከትክክለኛው መንገድ አይውጣ።
20
ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ፣ ሥጋ ከሚሰለቅጡ ጋር አትወዳጅ፤
21
ሰካራሞችና ሆዳሞች ድኾች ይሆናሉና፤ እንቅልፋምነትም ቡትቶ ያለብሳቸዋል።
22
የወለደህን አባትህን አድምጥ፤ እናትህንም ባረጀች ጊዜ አትናቃት።
23
እውነትን ግዛት እንጂ አትሽጣት፤ ጥበብን፣ ተግሣጽንና ማስተዋልን ገንዘብህ አድርግ።
24
የጻድቅ ሰው አባት እጅግ ደስ ይለዋል፤ ጠቢብ ልጅ ያለውም በእርሱ ሐሤት ያደርጋል።
25
አባት እናትህ ደስ ይበላቸው፤ ወላጅ እናትህም ሐሤት ታድርግ።
26
ልጄ ሆይ፤ ልብህን ስጠኝ፤ ዐይኖችህም ከመንገዴ አይውጡ፤
27
ዘልዛላ ሚስት ጠባብ ጕድጓድ፣ አመንዝራም ሴት ዐዘቅት ናትና፤
28
እንደ ወንበዴ ታደባለች፤ በሰዎችም መካከል ወስላቶችን ታበዛለች።
29
ዋይታ የማን ነው? ሐዘንስ የማን ነው? ጠብ የማን ነው? ብሶትስ የማን ነው? በከንቱ መቍሰል የማን ነው? የዐይን ቅላትስ የማን ነው?
30
የወይን ጠጅ በመጠጣት ጊዜያቸውን ለሚያባክኑ ነው፤ እየዞሩ ድብልቅ የወይን ጠጅ ለሚቀማምሱ ሰዎች ነው።
31
መልኩ ቀይ ሆኖ፣ በብርጭቆ ውስጥ ሲያንጸባርቅ፣ ሰተት ብሎ በሚወርድበትም ጊዜ፣ ወደ ወይን ጠጅ ትክ ብለህ አትመልከት።
32
በመጨረሻው እንደ እባብ ይነድፋል፤ እንደ እፉኝትም መርዙን ይረጫል።
33
ዐይኖችህ እንግዳ ነገር ያያሉ፤ አእምሮህም ይቀባዥራል።
34
በባሕር ላይ የተኛህ፣ በመርከብ ምሰሶ ጫፍ ላይ የተጋደምህ ትመስላለህ።
35
አንተም፣ “መቱኝ፤ አልተጐዳሁም፤ ደበደቡኝ፤ አልተሰማኝም፤ ታዲያ፣ ሌላ መጠጥ እንዳገኝ፣ መቼ ነው የምነቃው?” ትላለህ።
← Chapter 22
Chapter 24 →