bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Proverbs 21
Proverbs 21
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
የንጉሥ ልብ በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ እርሱም እንደ ቦይ ውሃ ደስ ወዳሰኘው ይመራዋል።
2
ለሰው መንገዱ ሁሉ ቀና ይመስለዋል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ይመዝናል።
3
ከመሥዋዕት ይልቅ ጽድቅንና ፍትሕን ማድረግ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አለው።
4
ትዕቢተኛ ዐይን፣ እብሪተኛ ልብ፣ የክፉዎችም መብራት ኀጢአት ናቸው።
5
የትጉህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል፤ ችኰላም ወደ ድኽነት ያደርሳል።
6
በሐሰተኛ አንደበት የተገኘ ሀብት፣ በንኖ የሚጠፋ ተን፣ ለሞትም የሚያበቃ ወጥመድ ነው።
7
ክፉዎችን ዐመፃቸው ይጠራርጋቸዋል፤ ቅን ነገር ማድረግ አይወድዱምና።
8
የበደለኛ መንገድ ጠማማ ነው፤ የንጹሕ ሰው ጠባይ ግን ቀና ነው።
9
ከጨቅጫቃ ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖር፣ በጣራ ላይ ጥግ ይዞ መኖር ይሻላል።
10
ክፉ ሰው ክፋትን አጥብቆ ይመኛል፤ ባልንጀራውም ከእርሱ ዘንድ ርኅራኄን አያገኝም።
11
ፌዘኛ ሲቀጣ፣ አላዋቂ ጥበብን ያተርፋል፤ ጠቢብ ሰው ቢማር ዕውቀትን ያገኛል።
12
ጻድቁ የክፉዎችን ቤት ልብ ብሎ ይመለከታል፤ ክፉዎችንም ያጠፋቸዋል።
13
ሰው የድኾችን ጩኸት ላለመስማት ጆሮውን ቢዘጋ፣ እርሱም ይጮኻል፤ መልስም አያገኝም።
14
በስውር የተደረገ ስጦታ ቍጣን ያበርዳል፤ በጕያ የተሸሸገ እጅ መንሻም ታላቅ ቍጣን ጸጥ ያደርጋል።
15
ፍትሕ ሲሰፍን ጻድቁን ደስ ያሰኘዋል፤ ክፉ አድራጊዎችን ግን ያሸብራል።
16
የማስተዋልን መንገድ የሚስት ሰው፣ በሙታን ጉባኤ ያርፋል።
17
ቅንጦትን የሚወድድ ይደኸያል፤ የወይን ጠጅና ዘይት የሚወድድም ባለጠጋ አይሆንም።
18
ክፉ ሰው ለጻድቅ፣ ወስላታም ለቅን ሰው ወጆ ይሆናል።
19
ከጨቅጫቃና ከቍጡ ሚስት ጋር ከመኖር፣ በምድረ በዳ መኖር ይሻላል።
20
በጠቢብ ቤት ምርጥ ምግብና ዘይት ተከማችቶ ይገኛል፤ ተላላ ሰው ግን ያለ የሌለውን ያሟጥጣል።
21
ጽድቅንና ፍቅርን የሚከተል፤ ሕይወትን ብልጽግናንና ክብርን ያገኛል።
22
ጠቢብ የኀያላንን ከተማ ቅጥር ጥሶ ይገባል፤ መታመኛ ምሽጋቸውንም ያፈርሳል።
23
አንደበቱንና ምላሱን የሚቈጣጠር፣ ራሱን ከመቅሠፍት ይጠብቃል።
24
ትዕቢተኛና ኵሩ ሰው “ፌዘኛ” ይባላል፤ በጠባዩም እብሪተኛ ነው።
25
ታካችን የሚገድለው ምኞቱ ነው፤ እጆቹ መሥራት አይፈልጉምና።
26
ክፉ ሰው ቀኑን ሙሉ ይመኛል፤ ጻድቅ ግን አንዳች ሳያስቀር ይሰጣል።
27
የክፉ ሰው መሥዋዕት አስጸያፊ ነው፤ በክፉ ዐላማ ሲያቀርብማ የቱን ያህል አስከፊ ይሆን!
28
ሐሰተኛ ምስክር ይጠፋል፤ እውነቱን የሚናገር ግን ጸንቶ ይኖራል።
29
ክፉ ሰው በዐጕል ድፍረት ይቀርባል፤ ቅን ሰው ግን አደራረጉን ያስተውላል።
30
እግዚአብሔርን ለመቋቋም የሚያስችል፣ አንዳችም ጥበብ፣ ማስተዋልና ዕቅድ የለም።
31
ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፤ ድል ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
← Chapter 20
Chapter 22 →