bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Proverbs 12
Proverbs 12
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ተግሣጽን የሚወድድ ዕውቀትን ይወድዳል፤ መታረምን የሚጠላ ግን ደነዝ ነው።
2
መልካም ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ ያገኛል፤ ተንኰለኛውን ግን እግዚአብሔር ይፈርድበታል።
3
ሰው በክፋት ላይ ተመሥርቶ ሊጸና አይችልም፤ ጻድቃን ግን ከቦታቸው አይነቃነቁም።
4
መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ ናት፤ አሳፋሪ ሚስት ግን ዐጥንቱ ውስጥ እንዳለ ንቅዘት ናት።
5
የጻድቃን ሐሳብ ቀና ነው፤ የክፉዎች ምክር ግን ሸር አለበት።
6
የክፉዎች ቃል ደም ለማፍሰስ ታደባለች፤ የቅኖች ንግግር ግን ይታደጋቸዋል።
7
ክፉ ሰዎች ይገለበጣሉ፤ ድራሻቸውም ይጠፋል፤ የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል።
8
ሰው በጥበቡ ይመሰገናል፤ ጠማማ ልብ ያላቸው ግን የተናቁ ናቸው።
9
የሚበላው ሳይኖረው ከሚኵራራ ይልቅ፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ ሠራተኛ የሚያሳድር ይሻላል።
10
ጻድቅ ሰው ለእንስሳቱ ይራራል፤ ክፉዎች ራሩ ቢባል እንኳ ዞሮ ዞሮ ሥራቸው ጭካኔ ነው።
11
መሬቱን የሚያርስ የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤ ከንቱ ተስፋን የሚያሳድድ ግን ማመዛዘን ይጐድለዋል።
12
ኀጥኣን የክፉዎችን ምርኮ ይመኛሉ፤ የጻድቅ ሥር ግን ይንሰራፋል።
13
ክፉ ሰው በእኩይ ንግግሩ ይጠመዳል፤ ጻድቅ ሰው ግን ከመከራ ያመልጣል።
14
ሰው ከከንፈሩ ፍሬ የተነሣ በበጎ ነገር ይሞላል፤ እንደ እጁ ሥራም ተገቢውን ዋጋ ያገኛል።
15
ተላላ ሰው መንገዱ ትክክል መስሎ ይታየዋል፤ ጠቢብ ሰው ግን ምክር ይሰማል።
16
ተላላ ሰው ቍጣው ወዲያውኑ ይታወቅበታል፤ አስተዋይ ሰው ግን ስድብን ንቆ ይተዋል።
17
ሐቀኛ ምስክር በእውነት ይመሰክራል፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸት ይናገራል።
18
ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል።
19
እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ፤ ሐሰተኛ አንደበት ግን ለቅጽበት ያህል ብቻ ነው።
20
ክፋትን በሚያውጠነጥኑ ሰዎች ልብ አታላይነት አለ፤ ሰላምን የሚያራምዱ ግን ደስታ አላቸው።
21
ጻድቃን ጕዳት አያገኛቸውም፤ ክፉዎች ግን በመከራ የተሞሉ ናቸው።
22
እግዚአብሔር ሐሰተኛ ከንፈርን ይጸየፋል፤ በእውነተኞች ሰዎች ግን ደስ ይለዋል።
23
አስተዋይ ሰው ዕውቀቱን ይሰውራል፤ የተላሎች ልብ ግን ድንቍርናን ይነዛል።
24
ትጉህ እጆች ለገዥነት ሲያበቁ፣ የስንፍና ፍጻሜ ግን የባርነት ሥራ ነው።
25
ሥጉ ልብ ሰውን በሐዘን ይወጥራል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።
26
ጻድቅ ሰው ለወዳጁ መልካም ምክር ይሰጣል፤ የክፉዎች መንገድ ግን ወደ ስሕተት ይመራቸዋል።
27
ሰነፍ ዐድኖ ያመጣውን እንኳ አይጠብስም፤ ትጉህ ሰው ግን ለንብረቱ ዋጋ ይሰጣል።
28
በጽድቅ መንገድ ላይ ሕይወት አለ፤ በዚያ ጐዳና ላይ ሞት የለም።
← Chapter 11
Chapter 13 →