bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Proverbs 10
Proverbs 10
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
የሰሎሞን ምሳሌዎች፤ ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ተላላ ልጅ ግን ለእናቱ ሐዘንን ያተርፋል።
2
ያላግባብ የተገኘ ሀብት አይጠቅምም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ይታደጋል።
3
እግዚአብሔር ጻድቁ እንዲራብ አያደርግም፤ የክፉዎችን ምኞት ግን ያጨናግፋል።
4
ሰነፍ እጆች ሰውን ያደኸያሉ፤ ትጉህ እጆች ግን ብልጽግናን ያመጣሉ።
5
ሰብሉን በበጋ የሚሰበስብ ጠቢብ ልጅ ነው፤ በመከር ጊዜ የሚተኛ ግን ውርደት ይከተለዋል።
6
በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ነው፤ መዓት ግን የክፉዎችን አፍ ይዘጋል።
7
የጻድቃን መታሰቢያቸው በረከት ነው፤ የክፉዎች ስም ግን እንደ ጠፋ ይቀራል።
8
በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝ ይቀበላል፤ ለፍላፊ ተላላ ግን ወደ ጥፋት ያመራል።
9
ሐቀኛ ሰው ያለ ሥጋት ይራመዳል፤ በጠማማ ጐዳና የሚሄድ ግን ይጋለጣል።
10
በተንኰለኛ ዐይን የሚጠቅስ ሐዘን ያስከትላል፤ ለፍላፊ ተላላም ወደ ጥፋት ያመራል።
11
የጻድቅ አንደበት የሕይወት ምንጭ ናት፤ መዓት ግን የክፉዎችን አፍ ይዘጋል።
12
ጥላቻ ጠብን ያነሣሣል፤ ፍቅር ግን ስሕተትን ሁሉ ይሸፍናል።
13
ጥበብ በአስተዋይ ሰው ከንፈር ትገኛለች፤ በትር ግን ማመዛዘን ለጐደለው ሰው ጀርባ ነው።
14
ጠቢባን ዕውቀት ያከማቻሉ፤ የተላላ አንደበት ግን ጥፋትን ይጋብዛል።
15
የባለጠጎች ሀብት የተመሸገ ከተማቸው ነው፤ ድኽነት ግን የድኾች መጥፊያ ናት።
16
የጻድቃን ደመወዝ ሕይወት ታስገኝላቸዋለች፤ የክፉዎች ትርፍ ግን ቅጣትን ታመጣባቸዋለች።
17
ተግሣጽን ነቅቶ የሚጠብቅ የሕይወትን መንገድ ያሳያል፤ ዕርምትን የማይቀበል ግን ሌሎችን ወደ ስሕተት ይመራል።
18
ጥላቻውን የሚሸሽግ ሐሰተኛ አንደበት ያለው ነው፤ ሐሜትን የሚዘራ ሁሉ ተላላ ነው።
19
ከቃላት ብዛት ኀጢአት አይታጣም፤ አንደበቱን የሚገታ ግን ጠቢብ ነው።
20
የጻድቅ አንደበት የነጠረ ብር ነው፤ የክፉ ሰው ልብ ግን ርባና የለውም።
21
የጻድቃን ከንፈሮች ብዙዎችን ያንጻሉ፤ ተላሎች ግን ከማመዛዘን ጕድለት ይሞታሉ።
22
የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም።
23
ተላላ ሰው በክፉ ተግባር ይደሰታል፤ አስተዋይ ሰው ግን በጥበብ ደስ ይለዋል።
24
ክፉ ሰው የፈራው ይደርስበታል፤ ጻድቅ የሚመኘው ይፈጸምለታል።
25
ዐውሎ ነፋስ ሲነሣ ክፉዎች ተጠራርገው ይወሰዳሉ፤ ጻድቃን ግን ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ።
26
ሆምጣጤ ጥርስን፣ ጢስ ዐይንን እንደሚጐዳ፣ ሰነፍም ለሚልኩት እንዲሁ ነው።
27
እግዚአብሔርን መፍራት ዕድሜን ያረዝማል፤ የክፉዎች ዕድሜ ግን በዐጭር ይቀጫል።
28
የጻድቃን አለኝታ ደስታ ነው፤ የክፉዎች ተስፋ ግን ከንቱ ሆኖ ይቀራል።
29
የእግዚአብሔር መንገድ ለጻድቃን መጠጊያ፣ ክፉ ለሚያደርጉ ግን መጥፊያቸው ነው።
30
ጻድቃን ፈጽሞ አይነቀሉም፤ ክፉዎች ግን በምድር አይኖሩም።
31
የጻድቃን አንደበት ጥበብን ያፈልቃል፤ ጠማማ ምላስ ግን ትቈረጣለች።
32
የጻድቃን ከንፈሮች ተገቢውን ነገር ያውቃሉ፤ የክፉዎች አንደበት ግን የሚያውቀው ጠማማውን ብቻ ነው።
← Chapter 9
Chapter 11 →