bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Numbers 19
Numbers 19
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤
2
“ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው፣ ሕጉ የሚጠይቀው ሥርዐት ይህ ነው፤ እንከን ወይም ነውር የሌለባትንና ቀንበር ተጭኖባት የማያውቅ አንዲት ቀይ ጊደር እንዲያመጡልህ ለእስራኤላውያን ንገራቸው።
3
ለካህኑ ለአልዓዛርም ስጠው፤ ከሰፈሩ አውጥተውም በፊቱ ይረዷት።
4
ከዚያም ካህኑ አልዓዛር ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ፣ ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት አቅጣጫ ሰባት ጊዜ ይርጨው።
5
እርሱ እየተመለከተም ጊደሯን ያቃጥሏት፤ ቈዳዋም፣ ሥጋዋም፣ ደሟም፣ ፈርሷም ጭምር ይቃጠል።
6
ካህኑ የዝግባ ዕንጨት፣ ሂሶጵና ብሩህ ቀይ ክር ወስዶ ጊደሪቱ በምትቃጠልበት እሳት ውስጥ ይጨምር።
7
ከዚህ በኋላ ካህኑ ልብሱን በውሃ ማጠብ፣ ሰውነቱንም መታጠብ አለበት፤ ከዚያም ወደ ሰፈሩ ሊመለስ ይችላል፤ ይሁን እንጂ በሥርዐቱ መሠረት እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል።
8
የሚያቃጥለውም ሰው እንደዚሁ ልብሱን ማጠብ፣ ሰውነቱንም በውሃ መታጠብ አለበት፤ እርሱም ደግሞ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል።
9
“ንጹሕ የሆነ ሰው የጊደሯን ዐመድ ዐፍሦ ከሰፈሩ ውጭ በመውሰድ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ በሆነ ስፍራ ያኑረው፤ ይህም ለመንጻቱ ውሃ እንዲውል በእስራኤል ማኅበረ ሰብ የሚጠበቅ ይሆናል፤ ከኀጢአትም ለመንጻት ይጠቅማል።
10
የጊደሯን ዐመድ የሚያፈስሰውም ሰው እንደዚሁ ልብሱን ማጠብ አለበት፤ ያም ሰው እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤላውያን እንዲሁም በመካከላቸው ለሚኖሩ መጻተኞች የሚሆን ዘላለማዊ ሥርዐት ነው።
11
“የሞተን ሰው በድን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን የረከሰ ይሆናል።
12
በሦስተኛውና በሰባተኛውም ቀን ሁለመናውን በውሃው ያንጻ፤ ንጹሕም ይሆናል። በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ካላነጻ ግን ንጹሕ አይሆንም።
13
የሞተን ሰው በድን ነክቶ ራሱን ያላነጻ ማንኛውም ሰው የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ማደሪያ ያረክሳል፤ ያም ሰው ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ። የሚያነጻው ውሃ ስላልተረጨበት ርኩስ ነው፤ ከርኩሰቱም አልተላቀቀም።
14
“አንድ ሰው በድንኳን ውስጥ በሚሞትበት ጊዜ የሚፈጸመው ሥርዐት የሚከተለው ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባም ሆነ በዚያ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን ድረስ የረከሰ ይሆናል፤
15
እንዲሁም ያልተከደነ ማንኛውም ክፍት ዕቃ የረከሰ ይሆናል።
16
“ሜዳ ላይ በሰይፍ የተገደለውን ወይም እንዲሁ የሞተውን ወይም ደግሞ ዐፅም ወይም መቃብር የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን ድረስ የረከሰ ይሆናል።
17
“ለረከሰውም ሰው፣ ለማንጻት ከተቃጠለው የጊደር ዐመድ ላይ ማሰሮ ውስጥ በማድረግ በላዩ የምንጭ ውሃ ይጨምሩበት።
18
ከዚያም በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነ ሰው ሂሶጵ ወስዶ በውሃው ውስጥ ከነከረው በኋላ ድንኳኑን፣ በውስጡ ያሉትን ዕቃዎች ሁሉ፣ እዚያ የነበሩትንም ሰዎች ሁሉ ይርጫቸው። እንዲሁም የሰው ዐፅም ወይም መቃብር ወይም ደግሞ የተገደለውን ወይም እንዲሁ የሞተውን ሰው የነካው ማንኛውንም ሰው ይርጭ።
19
የነጻው ሰው ያልነጻውን ሰው በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ይርጨው፤ በሰባተኛው ቀን ያንጻው፤ የሚነጻውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ገላውንም በውሃ ይታጠብ፤ ማምሻውም ላይ የነጻ ይሆናል።
20
ይሁን እንጂ አንድ የረከሰ ሰው ራሱን ሳያነጻ ከቀረ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መቅደስ አርክሷልና ከማኅበረ ሰቡ ተለይቶ ይጥፋ፤ የሚያነጻው ውሃ ያልተረጨበት ስለሆነ ርኩስ ነው።
21
ይህም ለእነርሱ የዘላለም ሥርዐት ነው። “የሚያነጻውን ውሃ የሚረጨውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ የሚያነጻውንም ውሃ የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማምሻው ድረስ የረከሰ ይሆናል።
22
የረከሰ ሰው የሚነካው ማናቸውም ነገር ይረክሳል፤ ይህን የነካ ሰው ደግሞ እስከ ማምሻው ድረስ የረከሰ ይሆናል።”
← Chapter 18
Chapter 20 →