bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Numbers 16
Numbers 16
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
የሌዊ ልጅ፣ የቀዓት ልጅ፣ የይስዓር ልጅ የሆነው ቆሬ፣ ከሮቤልም ነገድ የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን እንዲሁም የፍሌት ልጅ ኦን በክፋት ተነሣሥተው፣
2
ሙሴን ተቃወሙት። ከእነዚህም ጋር ታዋቂ የማኅበረ ሰቡ መሪዎች የሆኑና በጉባኤ አባልነት የተመረጡ ሁለት መቶ አምሳ እስራኤላውያን አብረው ነበሩ።
3
እነዚህም ሙሴንና አሮንን ለመቃወም ግንባር ፈጥረው በመምጣት፣ “ምነው ከልክ አላለፋችሁም? የማኅበረ ሰቡ አባላት ሁሉ እያንዳንዳቸው የተቀደሱ ናቸው፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ከእነርሱ ጋር ነው፤ ታዲያ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ማኅበር ላይ የምትታበዩት ለምንድን ነው?” አሏቸው።
4
ሙሴም ይህን ሲሰማ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤
5
ቆሬንና ተከታዮቹን በሙሉ እንዲህ አላቸው፤ “የእርሱ የሆነውና የተቀደሰው ማን መሆኑን እግዚአብሔር (ያህዌ) ነገ ጧት ይለያል፤ ወደ ራሱም ያመጣዋል፤ የሚመርጠውን ሰው ወደ ራሱ እንዲቀርብ ያደርገዋል።
6
ቆሬ፣ አንተና ተከታዮችህ ሁሉ እንዲህ አድርጉ፤ ጥናዎችን ውሰዱ፤
7
በማግስቱም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እሳትና ዕጣን ጨምሩባቸው፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚመርጠውም ያ ሰው ቅዱስ ይሆናል፤ እናንት የሌዊ ልጆች፤ ከልክ ያለፋችሁትስ እናንተ ናችሁ።”
8
ደግሞም ሙሴ ቆሬን እንዲህ አለው፤ “እናንት ሌዋውያን አድምጡ
9
የእስራኤል አምላክ (ኤሎሂም) እናንተን ከቀሩት እስራኤላውያን ማኅበረ ሰብ መለየቱና በእግዚአብሔር (ያህዌ) ማደሪያ አገልግሎት እንድትፈጽሙ ወደ ራሱ ማቅረቡ፣ እንድታገለግሏቸውም በማኅበረ ሰቡ ፊት እንድትቆሙ ማድረጉ አይበቃችሁምን?
10
አንተንና ከአንተም ጋር ወገኖችህ የሆኑትን ሌዋውያንን ሁሉ ወደ ራሱ አቅርቧችኋል፤ እናንተ ግን የክህነቱንም ሥራ ደርባችሁ ለመያዝ ይኸው ትሯሯጣላችሁ።
11
አንተና ተከታዮችህ ሁሉ አባሪ ተባባሪ ሆናችሁ የተነሣችሁት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ ነው፤ ለመሆኑ ታጕረመርሙበት ዘንድ አሮን ማነው?”
12
ከዚያም ሙሴ የኤልያብን ልጆች ዳታንና አቤሮንን አስጠራቸው፤ እነርሱ ግን እንዲህ አሉ፤ “እኛ አንመጣም!
13
በምድረ በዳ ልትገድለን ማርና ወተት ከምታፈሰው ምድር ያወጣኸን አይበቃህም? አሁን ደግሞ በእኛ ላይ ጌታ መሆን ያምርሃል?
14
ከዚህም በቀር አንተ ማርና ወተት ወደምታፈሰው ምድር አላመጣኸንም፤ ወይም ዕርሻዎችንና የወይን ተክል ቦታዎች አላወረስኸንም። ታዲያ የእነዚህን ሰዎች ዐይን ታወጣለህን? በጭራሽ አንመጣም!”
15
ሙሴም በጣም ተቈጣ፤ እግዚአብሔርንም (ያህዌ) “ቍርባናቸውን አትቀበል፤ እኔ ከእነዚህ ሰዎች የወሰድሁት አንድ አህያ እንኳ የለም፤ አንዳቸውንም አልበደልሁም” አለ።
16
ሙሴም ቆሬን እንዲህ አለው፤ “አንተና ተከታዮችህ እንዲሁም አሮን ነገ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ትቀርባላችሁ።
17
እያንዳንዱም ሰው ጥናውን ይወስዳል፤ በአጠቃላይ ሁለት መቶ አምሳ ጥናዎች ይሆናሉ፤ በዚያም ላይ ዕጣን ጨምሮ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቀርባል፤ አንተና አሮንም ጥናዎቻችሁን እንደዚሁ ታቀርባላችሁ።”
18
እያንዳንዱ ሰው ጥናውን በመያዝ ፍም አድርጎበት፣ ዕጣን ጨምሮበት ከሙሴና ከአሮን ጋር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቆመ።
19
ቆሬም እነርሱን በመቃወም ተከታዮቹን ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በሰበሰባቸው ጊዜ፣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር ለመላው ማኅበር ተገለጠ።
20
እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤
21
“ሁሉንም በአንድ ጊዜ እንዳጠፋቸው እናንተ ከዚህ ማኅበር ተለዩ።”
22
ሙሴና አሮን ግን በግንባራቸው ተደፍተው፣ “የሰብአዊ ፍጡር ሁሉ መንፈስ አምላክ (ኤሎሂም) የሆንህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ አንድ ሰው ኀጢአት በሠራ በመላው ማኅበር ላይ ትቈጣለህን?” ሲሉ ጮኹ።
23
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
24
“ማኅበሩን ‘ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች ራቁ’ በላቸው።”
25
ሙሴ ተነሥቶ ወደ ዳታንና አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ተከተሉት።
26
እርሱም፣ “ከእነዚህ ክፉ ሰዎች ድንኳን ራቁ የእነርሱ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትንኩ፤ ያለበለዚያ በእነርሱ ኀጢአት ሁሉ እናንተም ትጠፋላችሁ” ሲል ማኅበሩን አስጠነቀቀ።
27
ስለዚህ እነርሱ ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳን ራቁ። ዳታንና አቤሮን ወጥተው ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸውና ከሕፃናቶቻቸው ጋር በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ነበር።
28
ሙሴም እንዲህ አለ፤ “እነዚህን ነገሮች ሁሉ እንዳደርግ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ላከኝና ከራሴም እንዳይደለ በዚህ ታውቃላችሁ፤
29
እነዚህ ሰዎች እንደ ማንኛውም ሰው አሟሟት የሚሞቱ ቢሆኑና በሌሎች ሰዎች ላይ የሚደርሰው ብቻ የሚደርስባቸው ከሆነ፣ እኔን እግዚአብሔር (ያህዌ) አልላከኝም።
30
ይሁን እንጂ እግዚአብሔር (ያህዌ) ፈጽሞ አዲስ የሆነ ነገር አምጥቶ ምድር አፏን ከፍታ እነርሱንና የእነርሱ የሆነውን ሁሉ ብትውጥና በሕይወታቸው ወደ መቃብር ቢወርዱ፣ ሰዎቹ እግዚአብሔርን (ያህዌ) የናቁ መሆናቸውን የምታውቁት ያን ጊዜ ነው።”
31
ይህን ሁሉ ተናግሮ እንደ ጨረሰ የቆሙባት ምድር ተሰነጠቀች፤
32
አፏንም ከፍታ ሰዎቹን ከነቤተ ሰቦቻቸው እንዲሁም የቆሬን ሰዎች በሙሉ፣ ንብረታቸውንም ሁሉ ዋጠች።
33
እነርሱም ካላቸው ከማናቸውም ነገር ጋር ከነሕይወታቸው ወደ መቃብር ወረዱ፤ ምድሪቱም በላያቸው ተከደነችባቸው፤ ጠፉ፤ ከማኅበረ ሰቡም ተወገዱ።
34
ከጩኸታቸውም የተነሣ በአካባቢያቸው የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ፣ “ምድሪቱ እኛንም እኮ ልትውጠን ነው” ብለው ሸሹ።
35
እሳትም ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ወርዳ የሚያጥኑትን ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች በላቻቸው።
36
እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
37
“ጥናዎቹ የተቀደሱ ናቸውና ከተቃጠሉት ሰዎች ዘንድ ወስደህ በውስጣቸው ያለውን ፍም አርቆ እንዲደፋ ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአልዓዛር ንገረው፤
38
እነዚህም ሕይወታቸውን ለማጥፋት ኀጢአት የሠሩ ሰዎች ጥና ናቸው፤ ጥናዎቹም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የቀረቡና የተቀደሱ በመሆናቸው ለመሠዊያው መለበጫ እንዲሆኑ ቀጥቅጠህ አሣሣቸው፤ እነዚህም ለእስራኤላውያን ማስጠንቀቂያ ይሁኑ።”
39
ከዚህ የተነሣም ካህኑ አልዓዛር የተቃጠሉት ሰዎች አምጥተዋቸው የነበሩትን የናስ ጥናዎች ሰብስቦ የመሠዊያው መለበጫ እንዲሆኑ ቀጠቀጣቸው፤
40
ይህን ያደረገውም፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት ባዘዘው መሠረት ነው፤ ይህም ከአሮን ዘር በስተቀር ማንም ሰው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቀርቦ ዕጣን እንዳያጥን ያለበለዚያ ግን፣ እንደ ቆሬና እንደ ተከታዮቹ እንደሚሆን ለእስራኤላውያን የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነበር።
41
በማግስቱም መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ፣ “እናንተ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ሕዝብ ገድላችኋል” በማለት በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ።
42
ማኅበሩም ሙሴንና አሮንን ለመቃወም በተሰበሰቡ ጊዜ ወደ መገናኛው ድንኳን ዘወር ሲሉ ደመና ድንኳኑን በድንገት ሸፍኖት አዩ፤ የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር ተገለጠ።
43
ከዚያም ሙሴና አሮን ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ሄዱ።
44
እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
45
“በቅጽበት አጠፋቸዋለሁና ከዚህ ማኅበር ራቅ” እነርሱም በግንባራቸው ተደፉ።
46
ከዚያም ሙሴ አሮንን፣ “ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ቍጣ ወጥቶ መቅሠፍት ጀምሯልና ጥናውን ወስደህ ዕጣን በመጨመር ከመሠዊያው እሳት አድርግበት፤ ፈጥነህም ወደ ማኅበሩ ሄደህ አስተስርይላቸው” አለው።
47
ስለዚህ አሮን፣ ሙሴ በነገረው መሠረት ወደ ማኅበሩ መካከል ሮጦ ገባ፤ መቅሠፍቱም ቀደም ብሎ በሕዝቡ መካከል መስፋፋት ጀምሮ ነበር፤ ሆኖም አሮን ዕጣኑን ዐጥኖ አስተሰረየላቸው።
48
እርሱም በሕይወት ባሉትና በሞቱት መካከል ቆመ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ።
49
ይሁን እንጂ በቆሬ ምክንያት የሞቱትን ሳይጨምር ዐሥራ አራት ሺሕ ሰባት መቶ ሰዎች ተቀሥፈው ሞቱ።
50
ከዚያም መቅሠፍቱ ቆመ፤ አሮንም ሙሴ ወዳለበት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተመለሰ።
← Chapter 15
Chapter 17 →