bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Matthew 9
Matthew 9
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
1
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ባሕሩን በጀልባ ተሻግሮ ወደ ራሱ ከተማ መጣ።
2
በዚያም ሰዎች አንድ ሽባ ሰው በቃሬዛ ተሸክመው ወደ እርሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፣ “አይዞህ አንተ ልጅ፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው።
3
በዚህን ጊዜ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራን፣ “ይህማ እግዚአብሔርን መሳደብ ነው” በማለት በልባቸው አጕረመረሙ።
4
ኢየሱስ ሐሳባቸውን ተረድቶ እንዲህ አለ፤ “ክፉ ነገር በልባችሁ ለምን ታስባላችሁ?
5
ለመሆኑ፣ ‘ኀጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀልላል?
6
ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ነው” ብሎ፣ ሽባውን፣ “ተነሣ! ቃሬዛህን ይዘህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።
7
ሽባውም ተነሥቶ ወደ ቤቱ ሄደ።
8
ሕዝቡም ይህን ባዩ ጊዜ ተደነቁ፣ በፍርሀት ተሞልተው፣ እንደዚህ ያለ ሥልጣን ለሰው የሰጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
9
ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ሲሄድ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው በቀረጥ ማስከፈያ ኬላ ተቀምጦ አየ፤ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው።
10
ኢየሱስ በማቴዎስ ቤት በማእድ ላይ ሳለ፣ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኀጢአተኞች መጥተው ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ሊበሉ ተቀመጡ።
11
ፈሪሳውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፣ “መምህራችሁ ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኀጢአተኞች ጋር እንዴት አብሮ ይበላል?” ብለው ጠየቋቸው።
12
ኢየሱስም የተናገሩትን ሰምቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሐኪም የሚያስፈልገው ለሕመምተኞች እንጂ ለጤነኞች አይደለም፤
13
ሄዳችሁ፣ ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወድዳለሁ፤’ የሚለውን ቃል ትርጕም አጢኑ፤ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና።”
14
የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “እኛና ፈሪሳውያን ስንጾም፣ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ለምን አይጾሙም?” ብለው ጠየቁት።
15
ኢየሱስም እንዲህ አላችው፤ “ሙሽራው አብሯቸው እያለ ሚዜዎቹ እንዴት ሊያዝኑ ይችላሉ? ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ።
16
“በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ ዕራፊ የሚጥፍ ሰው የለም፤ ይህ ከሆነ አዲሱ ዕራፊ ካረጀው ልብስ ላይ ተቦጭቆ ቀዳዳውን የባሰ ያሰፋዋል።
17
በአሮጌ አቍማዳ አዲስ የወይን ጠጅ ማንም አይጨምርም፤ ይህ ከሆነ አቍማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቍማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ነገር ግን አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቍማዳ ይጨመራል፤ በዚህ ሁኔታ የወይን ጠጁና አቍማዳው በደኅና ተጠብቀው ይቈያሉ።”
18
ኢየሱስ ሰዎቹን በማናገር ላይ ሳለ፣ አንድ ሹም ከፊቱ ተደፍቶ፣ “ልጄ አሁን ሞተችብኝ፤ በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” አለው።
19
ኢየሱስም ተነሥቶ አብሮት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።
20
ከዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ ደም እየፈሰሳት ትሠቃይ የነበረች አንዲት ሴት ከኋላው መጥታ የልብሱን ጫፍ ነካች።
21
እርሷም በልቧ፣ “የልብሱን ጫፍ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” ብላ ነበር።
22
ኢየሱስም ወደ ኋላ ዘወር ብሎ ሴቲቱን አያትና፣ “አይዞሽ፤ ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል” አላት። ሴቲቱም ወዲያውኑ ተፈወሰች።
23
ኢየሱስ ወደ ምኵራብ አለቃው ቤት እንደ ደረሰ እንቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፣
24
“ዞር በሉ፤ ልጂቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው፤ እነርሱ ግን ሣቁበት።
25
ሕዝቡም ከወጣ በኋላ ወደ ውስጥ ገብቶ እጇን ያዘ፤ ልጂቱም ተነሥታ ቆመች።
26
ወሬውም በአካባቢው ሁሉ ተሠራጨ።
27
ኢየሱስም ከዚያ እንደ ሄደ ሁለት ዐይነ ስውሮች፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረን” በማለት እየጮኹ ተከተሉት።
28
ዐይነ ስውሮቹም ኢየሱስ ወደ ገባበት ቤት ተከትለው ገቡ፤ ኢየሱስም፣ “ዐይናችሁን ላበራላችሁ እንደምችል ታምናላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤” ብለው መለሱለት።
29
ከዚያም ኢየሱስ ዐይናቸውን ዳስሶ፣ “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” አላቸው።
30
ዐይናቸውም በራ፤ ኢየሱስም፣ “ይህን ማንም እንዳያውቅ” ብሎ በጥብቅ አስጠነቀቃቸው።
31
እነርሱ ግን ወጥተው በአካባቢው ሁሉ ስለ ኢየሱስ አወሩ።
32
ከዚያም ሲወጡ፣ በጋኔን የተያዘ ድዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ።
33
ጋኔኑ ከወጣለት በኋላ ድዳው መናገር ጀመረ፤ ሕዝቡም ተደንቀው፣ “እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ምድር ታይቶ አያውቅም” አሉ።
34
ፈሪሳውያን ግን፣ “አጋንንትን የሚያወጣው፣ በአጋንንት አለቃ ነው” አሉ።
35
ኢየሱስ በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች እየሰበከ፣ እንዲሁም ደዌንና ሕመምን ሁሉ እየፈወሰ በከተሞቹና በመንደሮቹ ዞረ።
36
ሕዝቡም እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ ዐዘነላቸው።
37
ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው፤ “መከሩ ብዙ ነው፤ የመከሩ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤
38
ስለዚህ የመከሩ ጌታ፣ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት።”
← Chapter 8
Chapter 10 →